የኢትዮ ቴሌኮም የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት

የኢትዮ ቴሌኮም የ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት

ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ያለውን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ሲሆን አፈጻጸሙ በኢትዮ ቴሌኮም የሥራ አመራር ቦርድና በከፍተኛ ማኔጅመንት ተገምግሞ በሀገራችን ከነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር አፈጻጸሙ እጅግ አመርቂ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል እንዲሁም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፊ የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት እያደገ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ ደንበኞቹን በማርካት ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነው የቴሌኮም ገበያ ብቁና ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን በሀገራችን በአሁኑ ወቅት እያጋጠሙ ያሉትን የጸጥታና ተያያዥ ፈተናዎች በመቋቋም በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን ለቴሌኮም ውድድር ገበያው ብቁ፣ ተወዳዳሪና ተመራጭ መሆን የሚያስችለውን የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ነድፎ የትኩረት አቅጣጫና የስትራቴጂ መስኮችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር ስትራቴጂያዊ ግቦችን ቀርፆ ግቦቹን ሊያሳኩ የሚችሉ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችና ተግባራት በማቀድ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ስትራቴጂካዊ ግቦችን ለማሳካት፤ የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ማሻሻልና እርካታን ታሳቢ ያደረገ የኦፕሬሽን ልህቀት ማምጣት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ማሳደግ፣ እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል የኔትወርክ አቅም ማሳደግ፣ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ መናበብ በመፍጠር አዳዲስ አገልግሎቶች ማምጣት፣ የሀብት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የዓለም አቀፍ ቢዝነስን ማጠናከርና ገበያው በሚጠይቀው መሠረት አዳዲስ አሰራሮችን መከተል፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን በተለያዩ ስልቶች መከላከል እንዲሁም የተቋም ደህንነትን ማረጋገጥ ዋና ተግባራት በማድረግ የተለያዩ እቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በግማሽ ዓመቱ 28 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 86.4% አሳክቷል፡፡ ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ6.7% እድገት አለው፡፡ ይህም ውጤት፣ የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያዎችን፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 23 አዳዲስ እና 19 ነባር የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን አሻሽሎ ለደንበኞች በማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 74.8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማግኘትና የእቅዱን 89.3% በማሳካት የተመዘገበ ነው፡፡ የተመዘገበው ውጤት ፣በሀገራችን በወቅቱ ከነበረው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር ሲታይ የተመዘገበው ውጤት አመርቂ ነው፡፡

ኩባንያችን የገቢ አማራጮችን ከማስፋት በተጨማሪም የወጭ ቁጠባ ስትራቴጂ በመቅረጽ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በ6 ወራት ውስጥ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ መቆጠብ ተችሏል፡፡

በሀገራችን ከተከሰተው ችግር ጋር በተገናኘ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 3,473 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የአገልግሎት መስተጓጎል የተፈጠረ ሲሆን በዚህም ብር 3.67 ቢሊዮን ገቢ ሊያጣ ችሏል፡፡ በጦርነት የተጎዱና እስካሁን መድረስ በተቻለባቸው አካባቢዎች ላይ የወደሙ ንብረቶች እንዲሁም አገልግሎቱን ለማስጀመር ብር 328.9 ሚሊዮን ወጪ ተደርጓል፡፡ አሁንም በጸጥታ ምክንያት ትግራይ ክልልን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት መስጠት ያልተቻለባቸው ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ያሉበት ሁኔታም ማወቅ አልተቻለም፡፡ ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ የአገልግሎት መቋረጥ ያጋጠማችሁ ክቡራን ደንበኞቻችንን ይቅርታ እየጠየቅን የጸጥታው ሁኔታ ሲሻሻል አስፈላጊ የጥገናና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን አገልግሎታችንን በፍጥነት የምናስጀምር መሆኑን እንገልጻለን፡፡

የአገልግሎታችን ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 60.8 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከእቅድ አንጻር የ100% አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡ አፈፃፀሙ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ20% እድገት አሳይቷል፡፡ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 58.7 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞች (Fixed Broadband) 443 ሺህ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 923 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 23.8 ሚሊዮን ናቸው፡፡ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 58.5% ሆኗል፡፡

በተጨማሪም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው የኩባንያችን መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅም እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ ሰፊ የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ ሲሆን በዚህ ግማሽ ዓመት የ4G/LTE የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ በድምሩ 136 ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተደርገዋል፡፡ ደንበኞቻችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል 4G/LTE Advanced በተጀመረባቸው የክልል ዋና ከተሞች የ4G ቀፎ በቅናሸ የማቅረብና አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል፡፡ የቢዝነስ ሰፖርት ሲስተም (Next Generation Business Support System (NGBSS)) የማዘመን እና የማሳደግ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ይህም ከደንበኞች ምዝገባ ጀምሮ የቢሊንግና አዳዲስ ምርትና አገልግሎት ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ይህን አዲስ ሲስተም በመጠቀም በርካታ ምርትና አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡

የሀገራችንን የድጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትና ተያያዥ የድጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶች ለመስጠት “ቴሌብር” አገልግሎት ለህብረተሰቡ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ የቴሌብር አገልግሎት ከኢንዱስትሪው ልምድ በተለየ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ13 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ የግብይት መጠኑም (Transaction Value) 5.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያችን አጋሮችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እስካሁን ድረስ ከ46 ሺህ በላይ ኤጀንቶችና ከ11 ሺህ በላይ ነጋዴዎች /Merchants/ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ከ11 ባንኮች ጋር የኢንቴግሬሽን ሥራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከ8 ባንኮች ጋር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር እንዲቻል ተደርጓል፡፡

የኩባንያችንን ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን የማስፈፀምና የመፈጸም አቅምን በማጎልበት በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ ተከታታይነት ያለው ስልጠና በአካልና በዲጂታል አማራጭ በመጠቀም ከ18 ሺህ በላይ ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የሠራተኛውን ተነሳሽነትና የባለቤትነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል ሠራተኞችን በተቋሙ ስትራቴጂ ዝግጅትና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ግብዓት እንዲሰጡ የማድረግ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሻሻል፣ የሥራ ከባቢን አመቺና ደህነንቱን የማረጋገጥ እንዲሁም የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመተግበር የተሻለ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ በአይነት፣ በአገልግሎትና በገንዘብ በድምሩ 253.4 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በመላው ሃገራችን በትምህርት፣ በጤና፣ የሰብአዊነት ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ላይ ተሳትፏል፡፡ ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ
ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች 14.7 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን በግማሽ ዓመቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው የፀጥታ ችግር
ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥና የመሠረተ ልማት መውደም፣ በታቀደው መሠረት የማስፋፊያ ሥራዎች ለመሥራትና አገልግሎት ማስቀጠል አዳጋች መሆን፣ የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣
የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የሃይል አቅርቦት መዘግየት እና የኃይል መቆራረጥ፣ ለቴሌኮም ማስፋፊያ የመሬት አቅርቦት ችግር፣ አንዳንድ ክልሎች ላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ጥያቄና ከዚሁ ጋር በተገናኘ የኩባንያችንን የባንክ ሂሳብ የማገድ ተግባራት እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

ኩባንያችን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከነበሩት ፈታኝ የጸጥታ ችግሮች አኳያ በአንድ በኩል አመራሩና
ሠራተኛው በመቀናጀት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በአገልግሎቱ ላይ የጋረጠውን አደጋ በመቋቋምና የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ትኩረት አድርጎ በመሥራት በሌላ በኩል የኦፕሬሽን ሥራዎችና በበጀት ዓመቱ ሊሠሩ የታቀዱ በርካታ የፕሮጀክት ሥራዎችን በመምራት የተደረገው ርብርብና የተመዘገበው ውጤት እጅግ አበረታች ነው፡፡

በቀውሱ ወቅት ህብረተሰቡ የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ከአደጋና ከስርቆት ለመከላከል ላደረገው አስተዋጽኦ
እንዲሁም አገልግሎት ለማስጀመር በምናደርገው ጥረት ውስጥ ላደረገው ድጋፍና ማበረታታት የላቀ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ኩባንያችን የህዝብ ተቋም እንደመሆኑ አሁንም የህዝባችን ድጋፍ በተለይም የመሠረተ ልማቱን ከተለያዩ ሰው ሰራሽ ጥፋቶች በመጠበቅ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በአጠቃላይ ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ያስመዘገበው አበረታች አፈጻጸም ለበለጠ ስኬት የሚያነሳሳ ሲሆን በተለይም በአሁኑ ወቅት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሀገራችን በወቅቱ ከነበሩ እጅግ አስቸጋሪ ተግዳሮቶች እና የቴሌኮም አገልግሎትን ለመስጠትና ለማስፋፋት ካለው ፈታኝ ሁኔታ አንጻር አፈጻጸሙን እጅግ አመርቂ ያደርገዋል፡፡ ይህ ውጤት የተመዘገበው የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ተመራጭ ኩባንያ ለማድረግ ካላቸው ህልም፣ ለውጤታማነቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአግባቡ በመወጣት ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረት ነው፡፡

በመንፈቅ ዓመቱ ለተመዘገበው አበረታች ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ለነበራቸው የኩባንያችን አመራርና ሠራተኞች፣ የሥራ አጋሮቻችን እንዲሁም ለደንበኞቻችን ላቅ ያለ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ በቀጣዩ መንፈቅ ዓመትም ለበጀት ዓመቱ ያቀድናቸውን መጠነ ሰፊ ግቦች ለማሳካት የሚያስችሉን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ የኔትዎርክ ማስፋፊያ ሥራዎችን እንዲሁም አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን በማቅረብ የደንበኞቻችን ፍላጎት ለማርካት ሰፊ ዝግጅት ጨርሰን ትግበራ ላይ መሆናችንን በአክብሮት እንገልጻለን፡፡

                ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም

Ethio telecom 2014 EFY (2021/22) First Half Business Performance Summary Report

This report covers our company’s business performance for the period of 1st July 2021 to 31st December 2021. The performance has been reviewed by Ethio telecom Board and the Higher Management and was found to be outstanding given the challenges and crises our country was facing.

Cognizant of the relevance and multiple active role Ethio telecom has in our country’s overall progress and prosperity, our company has been undertaking a wide range of projects and operations to expand telecom infrastructures and systems, improve the quality of service and increase the outreach of benefits to the community. In particular, we have been resiliently working hard, enduring the challenges in the current crises to become a competent and preferred telecom service provider in the fast and dynamic telecom market to meet the growing demand for telecom services.

Ethio telecom commenced the budget year with the implementation of its three years BRIDGE growth strategy along with the 2020/21 yearly plan to realize its aspiration to become a preferred telecom operator among customers and partners. Our company has conducted vast reform activities and advancements to attain its set strategic objectives preparing for the upcoming competitive market, enhancing customer experience and
satisfaction through ensuring operational excellence; deploying new and enhancement of infrastructure and systems, service availability, quality and affordability; effective resource utilization and enhancing financial capacity. Leadership and staff capacity building and empowerment; building reputable brand were also among the priorities.

In this first half of the budget year, we have garnered a total of 28 Billion ETB revenue, which is 86.4% of the target and 6.7% increment from the previous budget year similar period. This achievement is realized through network optimization works to enhance
customer experience and satisfaction; offering 23 new and 19 revamped local and international products and services, generating 74.8 Million USD from international business and scoring 89.3% of the target. Given the current challenging environment in our country, this achievement can be considered remarkable.

In addition to expanding our revenue streams, our company has devised cost optimization strategy and managed to save over 1.2 Billion ETB within the six months.
However, due to the crises, 3,473 BTS were not functional resulting in a revenue loss of 3.67 Billion ETB. The restoration in those areas where recovery was possible cost us
328.9 Million Birr but there are still many woredas remaining including Tigray region where we cannot provide our services and nor can the conditions and status of our telecom infrastructures be known. In this regard, we would like to extend our sincere apologies to our customers who are suffering from service outage due to the security challenges and that we will promptly do the necessary work of restoration as soon as the security situations improves.

Our total subscribers reached 60.8 Million achieving 100% of the subscriber base target and an increase of 20% from the previous budget year similar period. Mobile voice subscribers reached 58.7 Million, Data and Internet users 23.8 Million, Fixed Services 923K and Fixed Broadband subscribers reached 443K. Telecom density has reached 58.5%.

Currently, we are running different projects on infrastructure and system capacity expansions and enhancements aiming to boost network coverage capacity and quality of services out of which the expansion of 4G/LTE was completed and the service is already launched in 136 cities. In order to enable our customers to use the 4G/LTE Advanced services, we have availed 4G enabled handsets at an affordable price in those areas where the services were launched. Following the enhancement we have done on our Next Generation Business Support System (NGBSS), we were able to boost our Billing and Customer Relation Management Systems enabling us to provide improved
customer services and to also release different new products and services within a short period.

Furthermore, it can be recalled that we have recently engaged in the Mobile Money business introducing our “telebirr” with the aim to meet the country’s growing demand for digital financial services. Our “telebirr”, surpassing the industrial trend, has reached over 13 million subscribers within such a short period and with a total transaction value of ETB 5.1 Billion.

In order to ensure service coverage as well as benefit our partners, more than 46,000 agents and over 11,000 merchants have been engaged so far. In addition, integration with Banks is completed enabling money transfer from Bank to telebirr in 11 Banks and
from telebirr to Bank in 8 Banks.

To ensure sustainable business growth, various capacity building interventions were made, including training 18,000 employees. Along with other interventions are employee engagement in strategy development & execution, work environment enhancement and safe & healthy working conditions, various compensation and benefits systems.

As part of Corporate Social Responsibility and our commitment for our societies overall progress, our interventions have continued to have a positive impact on society, environment, and all stakeholders. Our CSR projects focused in strengthening
communities by targeting the fundamental drivers of long-term development such as education, health, agriculture, environmental protection, greening and beautification of cities. In this first half-year, we have contributed more than 253.4 Million Birr in kind, in service and in cash to address pressing societal challenges.

This corporate spirit is also reflected by our staff across the country by voluntarily mobilizing more than 14.7 Million ETB for various humanitarian activities. Also, their material, blood donation and in-service support has been enormous.
Among the challenges we faced during the period, COVID- 19, the crisis in the North region as well as in some other parts of the country have resulted in service outage, infrastructure damage, compromised project execution, supply chain, increasing operational costs and revenue impacts. In addition, fiber and copper cable vandalism, commercial power acquisition delay and power interruption, many relocation requests,
and delay in land acquisition for new sites deployment were among the main challenges.

In this regard, we would like to extend our appreciation to the community in the security challenged areas who protected our infrastructures from theft and damages. As Ethio telecom is an Ethiopian institution belonging to the People, we extend our call to our society to play their role of protecting the infrastructures from damages to use our services.

In summary, our company’s semi- annual performance for the 2021/22 budget year is remarkable given the challenges posed by COVID-19 and the security issues in some part of our country. This achievement is only made possible because of the commitment of our company’s leadership and employees to make Ethio telecom a preferred operator
on top of running the business, the leadership team’s stamina and concerted effort in managing the operation and projects.
Finally, we would like to extend our most sincere gratitude to our customers, business partners and stakeholders for such remarkable performance. In order to realize the goals we have set for the budget year, all the necessary network expansions and new technology deployment are started and we are working to release products and services that can satisfy our customers’ needs.

                  31 January 2022

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives