በኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል መካከል የሆራይዘን ፋይበር
ኢኒሼቲቭ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ይፋ ተደረገ
አፍሪካን ከአውሮፓ እና እስያ ጋር ከፍተኛ አቅም ባለው (መልቲ-ቴራቢት) የየብስ ፋይበር መስመር ያስተሳስራል
ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ቴሌኮሙኒኬሽን ግሩፕ አፍሪካን ከአውሮፓ እና እስያ እንዲሁም ከተቀረው ዓለም ጋር ከፍተኛ አቅም ባለው (መልቲ-ቴራቢት) የፋይበር ኮኔክቲቪቲ ለማስተሳሰር የሚያስችል የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ የአጋርነት ስምምነት መፈራረማቸውን በታላቅ ደስታ እናበስራለን። ይህ ስትራቴጂያዊ አጋርነት የቀጠናውን የዲጂታል መሠረተ ልማት ስብጥር የሚቀይር እጅግ አስተማማኝ እና የላቀ ኮኔክቲቪቲ መፍጠር የሚያስችል ከፍተኛ አቅም ያለው የመሬት ውስጥ ፋይበር ኦፕቲክ መሰረተ ልማት በመዘርጋት የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ነው፡፡
ድንበር ተሻጋሪ የኮኔክቲቪቲ ልህቀት
ከሶስቱም ኦፕሬተሮች የተውጣጡ ተወካዮችን ያካተተ የቴክኒክ ቡድን እ.ኤ.አ. ከሰኔ 2024 ጀምሮ የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት እውን በሚሆነበት ዙሪያ ውይይት ሲደረግ ቆይቷል። የቴክኒክ ቡድኑ አጠቃላይ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ፣ ወቅታዊ ተግዳሮቶችን በመተንተን እና ለቀጣይ አቅጣጫ ምክረሐሳቦችን በማቅረብ ጥር 2024 መጨረሻ ላይ የውል ስምምነቱን ለማጠናቀቅ እና እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2025 አገልግሎት ለማስጀመር በማቀድ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
ኢኒሼቲቩ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጂቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል የጋራ መሠረተ ልማትና ዕውቀታቸውን በመጠቀም አስተማማኝነቱ የተረጋገጠ እጅግ ከፍተኛ አቅም (መልቲ ቴራቢት) ያለው አማራጭ የፋይበር መስመር እንዲዘረጉ ያስችላል። ይህ ኮኔክቲቪቲ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ተቋማት እና ግለሰቦች አማራጭ እና አስተማማኝ ኮኔክቲቪቲ እንዲኖራቸው፣ የኢንተርኔት መዘግየት ችግርን ለመቀነስ እና ከፍተኛ ፍጥነት የሚሹ የላቁ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያስችላቸዋል።
የስምምነቱ ወሳኝ ፋይዳዎች
አማራጮችን ማስፋት (Route Diversification): አሁን ባሉት የቴሌኮም አገልግሎት መስመሮች ላይ አስተማማኝ አማራጭን በማስተዋወቅ መጠባበቂያ ያለው ጠንካራ የኔትወርክ አቅምን ማጎልበት፣
ዝቅተኛ የኢንተርኔት መዘግየት (Low Latency): ዳታ ለማስተላለፍ የሚረዱ ቀጥተኛ እና ውጤታማ መስመሮችን ማቅረብ፤ የከፍተኛ የዳታ ማዕከላት (hyperscalers) ተሞክሮን፣ ለይዘት ዝግጅት አቅራቢዎች እና ለተጠቃሚዎች (end-users) የሚረዱ አገልግሎቶችን ማሻሻል፤
ለኢኮኖሚ ዕድገት፡ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በማፋጠን፣ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ እና ይበልጥ ውጤታማ የሆነ ዓለም አቀፍ ንግድን በማሳለጥ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማስቀጠል፤
ለገበያ ማስፋፊያ (Market Expansion): ለከፍተኛ ዳታ ማዕከላት (hyperscalers)፣ ለይዘት ዝግጅት አቅራቢዎች እና ለጅምላ ነጋዴዎች በመላው አውሮፓ፣ እስያ እና ከዚያም ባሻገር የሚገኙ አዳዲስ የኮኔክቲቪቲ አማራጮችን በማቅረብ እድገትን ማቀላጠፍ ናቸው፡፡
አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ትብብሮችን ማጠናከር
የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ምሥራቅ አፍሪካን ከዋና ዋና የዓለም ገበያዎች ጋር የሚያገናኝ ከፍተኛ አቅም እና ዝቅተኛ መዘግየት ያለው ኔትወርክ በማቅረብ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው፡፡ ይህ ኢኒሼቲቭ ቀጠናዊ ትብብር እና የፈጠራ ውጤትን በማሳደግ እየጨመረ የመጣውን የከፍተኛ ዳታ ማዕከላትን (Hyperscalers) እና የይዘት አቅራቢዎችን ፍላጎት በማሟላት በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ የቀጠናውን ሚና በአዲስ መልክ ለመቅረፅ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
ይህ ትብብር ኢትዮ ቴሌኮም፣ ጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል የቴክኖሎጂ ፈጠራን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ የፋይበር ኦፕቲክ መስመሩ የኔትወርክን ከአደጋ የመቋቋም አቅምን (network resilience) በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ እድገትን እንደሚያሳድግ የሚጠበቅ ከመሆኑም ባሻገር በቀጠናው አገራት ውስጥ ያሉ ቢዝነሶችን እና ማህበረሰቦችን አቅም ለማሳደግ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።
የቀይ ባህር ፋይበር ኬብል ውስንነቶች መቅረፍ
በቀይ ባህር ውስጥ የተዘረጋው ባህር ጠለቅ የፋይበር መስመር በመርከብ መልህቅ፣ በእርጅና፣ በተፈጥሮአዊ አደጋዎች እና በግጭት ምክንያት ተደጋጋሚ ጉዳት የሚደርስበት ሲሆን በዚህ ጊዜ አካባቢው ባለው ውስብስብነት እና የባህር ውስጥ መስመር ለጥገና ከፍተኛ ወጪ እና ረዥም ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ጉልህ የኮኔክቲቪቲ ተግዳሮት በመፍጠር ላይ ይገኛል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ በሶስቱ ሀገራት የሚያልፍ አማራጭ ባለከፍተኛ አቅም የመሬት ውስጥ የፋይበር ኔትወርክ በመዘርጋት በቀይ ባህር መስመሮች ላይ የሚያጋጥመው አደጋ የአህጉር አቀፍ ግንኙነቶች መቋረጥ እንዳያስከትል ለማድረግ ያለመ የየብስ ፋይበር መስመር ነው፡፡ ከሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ የየብስ ፋይበር መስመር ጠቀሜታዎች መካከል፡-
• ወጪ ቆጣቢ፡ በመሬት ውስጥ የሚቀበር ፋይበር በባህር ውስጥ ከሚቀበር መስመር አንጻር ዋጋው ዝቅተኛ መሆን፣
• ቀልጣፋ ጥገና፡- በመሬት ውስጥ የሚቀበሩ ፋይበር መስመሮች ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ ጥገና ለማድረግ አመቺ መሆናቸው፤
• አስተማማኝ ኮኔክቲቪቲ፡ በቀይ ባህር መስመሮች ተገድቦ የነበረውን ግንኙነት በማስቀረት ለቀጠናው ችግር ፈቺ አማራጭ ኮኔክቲቪቲ ማቅረብ፤
• ቀጠናዊ ትብብር፡ ሀብት እና ክህሎትን በማስተባበር ዘላቂ የጋራ መሠረተ ልማት በመፍጠር በሀገራት መካከል ትብብርን ማጎልበት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የአጋር ኦፕሬተሮቹ መልዕክት
• ኢትዮ ቴሌኮም፡ “የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ከአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ 2030 ጋር የተጣጣመ የለውጥ ፕሮጀክት ሲሆን፣ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ እድገት እና ቀጠናዊ ትብብርን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ኢኒሼቲቩ አፍሪካን ከዋና ዋና የዓለም ገበያዎች ጋር የሚያገናኝ ከፍተኛ አቅምና ዝቅተኛ የዳታ መዘግየት ያለው የኮኔክቲቪቲ አገልግሎት በማቅረብ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚያጠናክር ከመሆኑም ባሻገር የላቀ የተቀናጀና በዲጂታል መሰረተ-ልማት የዳበረች አፍሪካን ለመገንባት መሠረት የሚጥል ነው፡፡”
• የጅቡቲ ቴሌኮም፡ ” ይህ ፕሮጀክት ዲጂታል ግንኙነትን እና ክልላዊ ውህደትን ለማሻሻል በምናደርገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው። “ፕሮጀክቱ ለትብብር፣ ፈጠራ እና ለደንበኞቻችን እና ማህበረሰባችን ልዩ የግንኙነት መፍትሄዎችን ለማቅረብ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።”
• ሱዳቴል፡ “የሱዳን በአፍሪካ እምብርት ላይ መገኘት እና ስትራተጂካዊ አቀማመጥ ሱዳቴል በኮኔክቲቪቲ ቀጣናዊ መሪ የመሆን ራዕዩን ይደግፋል። በምስራቅ፣ መካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ ሰፊ የፋይበር መሰረተ ልማት ያለው፣ በፖርት ሱዳን በኩል በቀይ ባህር ካለው የባህር ጠለቅ ኬብሎች መዳረሻ ጋር ተጨምሮ ሱዳቴል ለቀጠናዊው ኢኒሼቲቪቲ ጉልህ ሚና በማበርከት አፍሪካን ከዓለም ጋር ለማገናኘት ልዩ ቦታ አለው።”
አካታች የዲጂታል ዘመን
ይህ አጋርነት ሦስቱ የቴሌኮም ኩባንያዎች የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነት ስብጥር ክፍተትን (the digital divide) ለማጥበብ እና የአፍሪካን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን ያላቸውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ስምምነቱ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ሊያድግ የሚችል ኮኔክቲቪቲ እንዲኖር በማድረግ የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሸቲቭ ምሥራቅ አፍሪካን በዓለም አቀፍ ዲጂታል ሥነ-ምህዳር ውስጥ ቁልፍ ሚና እንድትጫወት የሚያስችላት ይሆናል።
ኢትዮ ቴሌኮም፣
ኀዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም