ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የቴሌኮም ምርት እና አገልግሎቶችን ምቾታቸው ተጠብቆ ባሻቸው ጊዜ እና ቦታ ማግኘት እንዲችሉ እንዲሁም ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑ የግብይት መላ ቴሌብርን ተጠቅመው ክፍያ መፈጸም ይችሉ ዘንድ ከሃይብሪድ ዲዛይንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ፈጸመ፡፡
ይህ በዛሬው ዕለት የተደረገው የአጋርነት ስምምነት በዋናነት የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶችን ከራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰራር ጋር በማስተሳሰር በየጊዜው እያደገ የመጣውን የደንበኞች አማራጭ የአገልግሎት ፍላጎት በቀላሉ እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ምላሽ ለመስጠት፣ በተለይም የኩባንያውን ምርትና አገልግሎቶች ተደራሽነት ለማስፋት እና ለደንበኞች አማራጭ፣ ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለማቅረብ ያለመ ነው፡፡
ይህም ኩባንያው የቴሌገበያ የኦንላይን ግብይትን ጨምሮ ምርትና አገልግሎቶቹን በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 509 የራሱ የሽያጭ ማዕከላት እንዲሁም በ185 የአጋሮቹ የሽያጭ ማዕከላት አማካኝነት ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት ባሉት ከ40 ሺህ በላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች አማካኝነት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ደንበኞቹ ተደራሽ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የራይድ ትራንስፖርት የአገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ከመፈጸም በተጨማሪ የራይድ ትራንስፖርት የአገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች በወኪልነት (Agent) የቴሌኮም እና ሌሎች ወርሃዊ የአገልግሎት ክፍያዎችን፣ አዲስ ደንበኞችን ለመመዝገብ፣ የደንበኞችን የቴሌብር ደንበኝነት ደረጃ ለማሳደግ፣ የአየር ሰዓት እና የጥቅል አገልግሎቶችን ለመሸጥ፣ ገንዘብ የማስቀመጥና የማውጣት አገልግሎት፣ አዲስ ሲም ካርድ መሸጥ፣ ምትክ ሲም ካርዶችን ለደንበኞች ማድረስ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የዴሊቨሪ አገልግሎቶችን (Package Delivery) መስጠት እና ክፍያዎችን በቴሌብር መቀበል የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡
የቴሌብር አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ለዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስፋፋት ጉልህ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ19.4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ ከ82 በላይ ዋና ወኪሎች፣ 69 ሺ በላይ ወኪሎች እና ከ18 ሺ በላይ ነጋዴዎች ማፍራት ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከ18.7 ቢሊዮን ብር በላይ የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር የተደረገ ሲሆን ከ12 ባንኮች ጋር ከባንክ ወደ ቴሌብር እና ከ10 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ ገንዘብ ለማስተላለፍ ትስስር መፍጠሩ ለዲጂታል የክፍያ ስርዓት ያለውን ከፍተኛ ተመራጭነት ያሳያል፡
ኩባንያችን የህብረተሰቡን የተለያዩ የቴሌኮም ፍላጎቶችን ለማሟላት እና ዘመኑ ያፈራቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር በአጋርነት ከሚሰሩ ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር የማህበረሰባችንን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ለማሻሻል፣ ለማቅለል ብሎም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ እና የማህበረሰባችን የኑሮ ዘይቤ ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በቅርቡ ኩባንያችን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬትን፣ የመብራት አገልግሎት እና የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን እንዲሁም የውሃና ፍሳሽ መስሪያ ቤቶች የወርሃዊ አገልግሎት ክፍያን በቴሌብር ለማከናወን የሚያስችል የጋራ ስምምነትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች የአገልግሎት ክፍያዎቻቸውን በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችል ስምምነት አድርጓል፡፡
በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርአታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርአት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው መፈጸም እንዲችሉ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡
ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም