ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር በሀገራችን ያለውን የፋይናንስ አካታችነት ክፍተት በማጥበብ፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣንና ቀላል በሆነ ዘዴ እንዲሁም በአነስተኛ የግብይት ወጪ የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታን ለማመቻቸት ታሳቢ በማድረግ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም “ቴሌብር” የተሰኘ አገልግሎት ያስጀመረ ሲሆን፣ አገልግሎቱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 32 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት የማህበረሰባችንን የዲጂታል ህይወት በማቅለል ላይ ይገኛል፡፡

ይህ በሀገራችን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና የማህበረሰባችንን የዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ ለማሻሻልና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት፣ ዘልማዳዊ የሃገራችን የክፍያ ሥርዓት ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ለማስቻል፣ ጤናማ የገንዘብ ፍሰት እንዲፈጠር፣ ሥራ ፈጣሪነትና ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ እና ተደራሽነቱን በማስፋት የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን በማድረግ ህዝባችንን ለማገልገል ካለን ጽኑ ፍላጎት በመነሳት የቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን የዛሬ ሁለት ዓመት በማስጀመር በአጭር ጊዜ ውስጥ ታላቅ እመርታን ለማስመዝገብ ችለናል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ስርዓት በሃገራችን የግብይት እና የገንዘብ ዝውውር ላይ ትልቅ መነቃቃት እና ከፍተኛ ለውጥ የፈጠረ ሲሆን፣ የፋይናንስ አካታችነት/Financial Inclusion/ ክፍተትን በማጥበብ ሁሉንም የፋይናንስ አገልግሎቶች ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው የተለያዩ የዲጂታል ግብይቶችን ፈጣንና ቀላል በሆነ ዘዴ እንዲሁም በአነስተኛ የግብይት ወጪ የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በተለይም በያዝነው የበጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ የቴሌብር አገልግሎት ለማህበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የቁጠባ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ከዳሸን ባንክ ጋር በመተባበር አገልግሎት መስጠት በመጀመራችን ባለፉት ዘጠኝ ወራት አመርቂ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ችለናል፡፡

ቴሌብር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ103.8 ሺ በላይ ወኪሎች፣ ከ41ሺህ በላይ ነጋዴዎች ፣ ከ44 ሃገራት ከ2.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ  ሃዋላ  እንዲሁም ከ20 ባንኮች ጋር ትስስርን የፈጠረ ሲሆን፣ በቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ስርዓት በ24 ወራት ውስጥ በአጠቃላይ 519.6 ቢሊዮን ብር ግብይት እና የገንዘብ ዝውውር ተፈጽሟል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ ባስጀመረው የዲጂታል ፋይናንስ የብድርና ቁጠባ አገልግሎት በቴሌብር መላ የብድር አገልግሎት ለ1.4 ሚሊዮን ተጠቃሚዎቹ 2.43 ቢሊዮን ብር ያበደረ ሲሆን፣ 540ሺ የቴሌብር ሳንዱቅ የቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ 2.46 ቢሊዮን ብር እንዲቆጥቡ ለማድረግ ተችሏል፡፡

ቴሌብርን በመጠቀም ገንዘብ ከማስተላለፍ፣ ከመቀበልና ከመክፈል በተጨማሪ ደንበኞች በአንድ መተግበሪያ ላይ እልፍ ጉዳዮችን እንዲያገኙ ለማስቻልና በየጊዜው እያደገ የመጣውን የዲጂታል ፍላጎት ለማርካት ቴሌብር ሱፐርአፕ ወደተሰኘ መተግበሪያ ማበልጸግ የቻልን ሲሆን፣ በቴሌብር ግብይት ለመፈጸም የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ከበርካታ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር አብረን እየሰራን እንገኛለን፡፡

ለአብነትም ወርሃዊ የአገልግሎት ክፍያዎችን፣ ዓመታዊ የገቢ ግብር ክፍያዎችን፣ የነዳጅ ክፍያን፣ በሱፐር ማርኬቶች፣ በካፌዎች፣ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች፣ ፋርማሲዎች እና ሆስፒታሎች፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና የበርካታ መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመቀበልና ለመፈጸም ቴሌብር ተማራጭ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መሆን ችሏል፡፡

በቀጣይም የቴሌብር ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶችን ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት የምንሰራ ሲሆን፣አገልግሎቱ ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈራና የሀገራችንን የዲጅታል ፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት እና ዲጅታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት ከግብ ለማድረስ በዘርፉ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጭ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት አብራችሁን እንድትሰሩ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡

ግንቦት 3 ቀን 2015 .

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives