ትሩፋት ላለው ሕይወት መኖርና መምራት

ትሩፋት ላለው ሕይወት መኖርና መምራት 

ኢትዮ ቴሌኮም በቢሾፍቱ ከተማ ባደረገው የሥልጠናና የምክክር መድረክ ‘Living and Leading for Lasting Legacy’ እና ‘Embracing Change’ በሚሉ ሁለት ርዕሶች ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት በሚሰራው MindSet አማካሪ ድርጅት መስራችና ዳይሬክተር ዶ/ር ምህረት ደበበ አማካኝነት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከዚሁ አማካሪ ድርጅት በመጡ የአመራር ክህሎት አሰልጣኞች ‘Top Leader Alignment & Employee Engagement, Corporate Vision & Goal እና Measurable Performance’ በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ተጨማሪ ስልጠናዎች  ተሰጥተዋል፡፡

የተቋሙ አመራር በኃላፊነት ቦታው ላይ ለራሱም ሆነ ለኩባንያው ጥሎት የሚያልፍ አሻራና ዘላቂ ትሩፋት /Lasting Legacy/ እንዲኖረው የሚስችለውን አነቃቂ ንግግር /Motivational Speech/ ያቀረቡት ዶ/ር ምህረት፣ ባለራዕይ መሪ ለመሆንና ዘላቂ ትሩፋትን ለመፍጠር የብቃት (Competence)፣ የመሰጠት (Commitment) እና የባህሪ (Character) ቅንጅት አስፈላጊነትን አስረድተዋል፡፡ 

በኩባንያው ራዕይ፣ ተልዕኮና እሴቶች ላይ የጋራ ግንዛቤና ጥምረት /Leadership Alignment/ መፍጠር፣ የባለቤትነት ስሜት ማዳበር፣ ውጤታማ የለውጥ አመራርና ተቋሙ በለውጥ ሂደት ላይ በመሆኑ ለውጡን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የአመራሩ ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ተገንዝቦ የአመራርነት ሚናውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችሉ ቁልፍ ጉዳዮችን ማዕከል ያደረገ ውይይት አካሂዷል፡፡

በተጨማሪም የተቋሙ ሠራተኛና አመራር የቡድን ስሜት በማጠናከር፣ የትብብር የመደጋገፍና የመተጋገዝ ባህል በማዳበር እንዲሁም Emotional Engagement እንዲኖረው በማድረግ ሥራውንና መስሪያ ቤቱን የሚወድና ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በቀናነትና በፍጹም አገልጋይነት መንፈስ ማከናወን እንደሚገባ ተብራርቷል፡፡
የተቋሙን እቅድ በሚፈለገው ደረጃ ለማሳካት የሚያስችሉ አሰራሮችን ከመተግበር አኳያም የሥራ መሳሪያዎችን ማሟላት፣ ትክክለኛና የሚለካ ግብና ዒላማ ቀርጾ ለፈጻሚው ቆጥሮ መስጠትና ቆጥሮ መቀበል፣ ፈጠራንና አዳዲስ ሀሳቦችን ማበራታታት፣ ሠራተኛን ማነቃቃትና ውጤታማነትን ለማጎልበት አፈጻጸምን መሠረት ያደረገ የእውቅናና የሽልማት ስርዓት መቅረጽና መተግበር እንዲሁም ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡

ስልጠናውና የምክክር መድረኩ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የስልጠና ሂደቶች የተለየ የሚያደርገው አመራሩ ሚዛኑን የጠበቀ የሥራና የህይወት /Life Work Balance/ እንዲኖረው ለማስቻል የሚረዳ ክህሎት ያካተተ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አመራሩ ጤናማ የህይወት ዘይቤን በመከተል ሁለንተናዊ ደህንነቱ የተጠበቀ በማድረግ የመፈጸም አቅሙን ማጎልበት የሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ስልጠናና ምክክር የተካሄደ ሲሆን ይህንኑ አመራሩ ወደ ተቀረው አመራርና መላው የተቋሙ ማህበረሰብ ውስጥ ለማስረጽና የተቋሙ ባህል ለማድረግ የዕለት ተዕለት ተግባሩ በማድረግ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡

በስልጠናው ላይ የተካፈሉ አመራሮችም የስልጠናውን አስፈላጊነት በመጠቆም ለሌሎች የተቋሙ አመራር አካላት ተመሳሳይ መድረክ መዘጋጀት እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ ከስልጠናው ዝግጅት ጀምሮ የነበረው ቅንጅትና አዲስ አሰራር እንዳስደሰታቸው በመግለጽ፣ ያገኙትን ግንዛቤና ተነሳሽነት ወደ የሥራ ክፍላቸው በመውሰድና ወደ ተግባር በመቀየር የማህበረሰቡን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት በተሻለ ብቃት ለማሟላትና ተቋሙንም ለበለጠ ስኬት ለማድረስ በሀገሪቱ ካሉ ተቋማት በጥራትና በልህቀት መሪ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ 

በመጨረሻም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ አሰልጣኞችንና በስልጠናው ላይ በንቃት የተሳተፉ አካላትን በማመስገን ሀገሪቱ በተያዘችው ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ የቴሌኮም ድርሻ እጅግ ወሳኝና አስቻይ ሚና ያለው ከመሆኑ አንጻር የተቋሙ ሠራተኛና አመራር በተለወጠና በይቻላል መንፈስ በመተባበር፣ በመተጋገዝና በመደጋገፍ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም አመራሩ ያለበትን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በመረዳት ራሱን በቀጣይነት እያበቃ ተቋሙን በሳይንሳዊ የአመራር ጥበብ በመምራት በልህቀት የሚታወቅና ለሌሎች ኩባንያዎች አርዓያ እንዲሆን ማስቻል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበው ተመሳሳይ ስልጠናዎችና የምክክር መድረኮች በተከታታይ እንደሚሰጡና ሌሎች የአመራር አካላትንም እንደሚያካትት ገልጸዋል፡፡

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives