ኢትዮ ቴሌኮም ሁለተኛውን እጅግ ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያ በአዲስ አበባ ከተማ ገንብቶ ሥራ አስጀመረ!

Bringing New Possibilities: Ethio telecom Powers Ethiopia’s EV Future with Ultra-Fast Charging!
ኩባንያችን እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ መኪና ስነ-ምህዳር በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ባለው ከፍተኛ ቁርጠኝነት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ከመገናኛ ወደቦሌ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ እጅግ ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ሁለተኛውን ጣቢያ ገንብቶ በይፋ ወደሥራ አስገብቷል።

ይህ ኢኒሼቲቭ መሪ ዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢ ከሚለው የኩባንያችን ራዕይ እና “አዳዲስ ዕድሎችን ማቅረብ” ከሚለው የኩባንያችን መርህ ጋር የሚጣጣምና የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዟችን አንዱ አካል ነው። ከሀገራች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እድገት እና መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የተደረገው ይህ እጅግ ዘመናዊ ኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያ በየጊዜው እያደገ የመጣውን ፈጣንና ቀልጣፋ የኃይል መሙያ ሶሉሽኖችን ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው።

ከዚህ ቀደም ኩባንያችን ከቦሌ ወደመገናኛ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ 16 መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል የኤሌክትሪክ መኪና መሙያዎችን የያዘ ጣቢያ ገንብቶ ወደስራ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ከየካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለ14,280 የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት መስጠት የተቻለ ሲሆን፣ ለዚህም 376,574.72 ኪሎዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በተጨማሪም 521,074.23 ኪሎግራም ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቅ መከላከል የተቻለ ሲሆን፣ ይህም ከ2,622 በላይ ዛፎችን ከመትከል ጋር ይነፃፀራል።

ዛሬ በምዕራፍ ሁለት ወደስራ የገባው ሁለተኛው ጣቢያ በልዩ ሁኔታ የአውሮፓ ስሪት የሆኑ የኤሌክትሪክ መኪኖችን (European EV Cars) ኃይል የመሙላት አቅም ያለውና ከተሽከርካሪዎቹ ጋር የተጣጣመ ኃይል መሙያ (EU Altra Fast) ቻርጀር ያለው ነው።

የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያው በአንድ ጊዜ እስከ 16 የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቻርጅ በማድረግ ለአሽከርካሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሲሆን፣ በዚህም በአንድ ጊዜ በአጠቃላይ ለ32 የኤሌክትሪክ መኪኖች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት ተችሏል። በተለይም አሽከርካሪዎች የቦታ ጥበት ሳያሳስባቸው ወደጣቢያው ገብተው አገልግሎታቸውን አግኝተው እንዲወጡ የሚያስችል ሰፊና ምቹ ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ይህም ከዚህ ቀደም ከቦሌ ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ ላይ በተገነባው የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያዎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው በቀላሉ አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ በተጨማሪም እነዚህ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያዎችን በቀላል ወጪና በፍጥነት ተጨማሪ ማስፋፊያ (scalable) ለማከናወን በሚያስችል ቴክኖሎጂ የተገነቡ በመሆኑ እንደ አስፈላጊነቱ በማንኛውም ጊዜ ማስፋፊያ ወይም ማሻሻያ ለማድረግ ያስችላል፡፡

ስማርት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈ የላቀ አገልግሎት
የኤሌክትሪክ መኪና ኃይል መሙያዎቹ እንደ መኪናው ሞዴል እና የባትሪ አቅም በሰከንድ 1 ኪ.ሜ የሚያስኬዳቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ቻርጅ ማድረግ የሚችሉ ሲሆን፣ ሲስተሙ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ የባትሪ መስፈርቶች እና የደንበኛን ትዕዝዝ ተቀብሎ በመመርመር በተፈለገው መጠን ቻርጅ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ይህም ፈጣን፣ ስማርት እና የላቀ ኃይል ቆጣቢ የቻርጂንግ ሂደትን በማረጋገጥ የተጠቃሚውን አጠቃላይ ተሞክሮ ያሻሽላል።
አዲሱ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያው የሚከተሉትን አማራጮች ያካትታል፡-
1. አራት እጅግ በጣም ፈጣን የሆኑ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያዎች (እስከ 600 kW ድረስ ቻርጅ የማድረግ አቅም ያላቸው)፣ እንደ መኪናው አቅም በ15 ደቂቃ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ (100%) የኤሌክትሪክ ኃይል መሙላት የሚያስችል ሲሆን፣ በተለይም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ለተሰማሩ የከተማ አውቶብሶች በፍጥነት በመሙላት ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ እና ወደ አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል፡፡
2. አስራ ሁለት በጣም ፈጣን የሆኑ የኤሌክትሪክ መኪና መሙያዎች (እስከ 500 kW ድረስ) – የተሽከርካሪ ባትሪን በከፍተኛ ፍጥነት ለመሙላት የሚያስችል የላቀ ፍጥነት ያላቸው ሲሆን፣ ይህም አሽከርካሪዎች በፍጥነት ተመልሰው ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል፡፡
ወጥና ተጣጥሞ የሚሄድ የዲጂታል ቻርጂንግ ተሞክሮ በቴሌብር
የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያው 24/7 አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ የሚሰራው በቴሌብር ሱፐርአፕ ላይ በሚገኝ መተግበሪያ ነው፡፡
የአገልግሎት ክፍያ ተገልጋዮች ፈጣን፣ ቀላል፣ ምቹና አስተማማኝ በሆነው ቴሌብር መፈጸም ይችላሉ፡፡
ያለማንም አጋዥነት (Self-service) አሽከርካሪዎች አገልግሎቱን በራሳቸው ማግኘት እና ክፍያቸውንም በቴሌብር ሱፐርአፕ መፈጸም ይችላሉ።
የስማርት ኦንላይን ክትትል ስርዓቱ በቴሌብር ሱፐርአፕ አማካኝነት መረጃዎችን ለማግኘት እና የመሙላት ሂደቱን ለማስተዳደር የሚያስችል ሲሆን፣ ሲስተሙ ከክላውድ ሰርቨሮች ጋር በፋይበር ኬብል እንዲሁም በ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ የተገናኘ በመሆኑ እጅግ አስተማማኝ ነው፡፡
ኤን. ኤፍ. ሲ (Near Field Communication – NFC) በእጅ በመንካት ቻርጅ ማድረግ (tap to charge) ወይም ስማርት የማንነት ማረጋገጫ (smart authentication) ያላቸው ሲሆን፣ ይህም በቀላሉ ቻርጅ ማድረግን ለማስጀመር እና ክፍያዎችን እንዲያጠናቅቁ በማስቻል ተጠቃሚዎች የላቀ ተሞክሮ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያን ዲጂታል እና አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን ማጠናከር

ሀገራችን ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እና ሞቢሊቲ እየገሰገሰች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ኩባንያችን አስተማማኝ፣ ቀልጣፋ እና ቀጣይነት ያላቸው (future-ready) መሠረተ ልማቶችን በመገንባት እና የዲጂታል ፈጠራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል። በመሆኑም ይህ እጅግ ዘመናዊ እና ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ጣቢያ ኢትዮ ቴሌኮም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል መፍትሄዎች የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ገጽታ ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

                                                    ኢትዮ ቴሌኮም
                                            መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives