ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ እጅግ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ መሙያ ጣቢያ ገንብቶ ሥራ አስጀመረ

Bringing New Possibilities: Ethio telecom Powers Ethiopia’s EV Future with Ultra-Fast Charging!

ኩባንያችን እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን የኤሌትሪክ ተሽከርካሪ ስነ-ምህዳር በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ባለው ከፍተኛ ቁርጠኝነት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ከቦሌ መገናኛ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ በሁለቱም አቅጣጫ እጅግ ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ መሙያ ጣቢያን ገንብቶ በይፋ ወደሥራ አስገብቷል። ይህ ኢኒሼቲቭ መሪ ዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢ ከሚለው የኩባንያችን ራዕይ እና “አዳዲስ ዕድሎችን ማቅረብ” ከሚለው የኩባንያችን መርህ ጋር የሚጣጣምና የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዟችን አንዱ አካል ነው።

ከሀገራች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እድገት እና መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተግባራዊ የተደረገው ይህ እጅግ ዘመናዊ የመኪና ኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያ በየጊዜው እያደገ የመጣውን ፈጣን እና ቀልጣፋ የኃይል መሙያ ሶሉሽኖችን ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው። ይህ ሶስት አማራጮችን የያዘው የኤሌክትሪክ ኃይል መሙያ ጣቢያ፣ በአንድ ጊዜ እስከ 32 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ በማድረግ ለአሽከርካሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል። 

ስማርት እና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተደገፈ የላቀ አገልግሎት  

የአሌክትሪክ መኪና ቻርጀሮቹ እንደ ተሽከርካሪውን ሞዴል እና የባትሪ አቅም በሰከንድ 1 . የሚያስኬዳቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ቻርጅ ማድረግ የሚችሉ ሲሆን፣ ሲስተሙ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ የባትሪ መስፈርቶች እና የደንበኛን ትዕዝዝ ተቀብሎ በመመርመር በተፈለገው መጠን ቻርጅ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ይህም ፈጣን፣ ስማርት እና የላቀ ኃይል ቆጣቢ የቻርጂንግ ሂደትን በማረጋገጥ የተጠቃሚውን አጠቃላይ ተሞክሮ ያሻሽላል።

አዲሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ ጣቢያ የሚከተሉትን አማራጮች ያካትታል፡-

  1. ስምንት እጅግ በጣም ፈጣን የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያዎች ( እስከ 600 kW ድረስ ቻርጅ የማድረግ አቅም ያላቸው)፣ እንደ ተሸከርካሪው አቅም በ15 ደቂቃ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ (100%) የኤሌክትሪክ ኃይል መሙላት የሚያስችል ሲሆን፣ በጉዞ ላይ በተለይም በትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ለተሰማሩ አሽከርካሪዎች በፍጥነት በመሙላት ጊዜያቸውን ለመቆጠብ ያስችላቸዋል፡፡
  2. አስራ ሁለት በጣም ፈጣን የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያዎች (እስከ 500 kW ድረስ) – የተሽከርካሪ ባትሪን በከፍተኛ ፍጥነት ለመሙላት የሚያስችል የላቀ ፍጥነት ያላቸው ሲሆን፣ ይህም አሽከርካሪዎች በፍጥነት ተመልሰው ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል፡፡
  3. የስማርት ምሰሶ ቻርጀሮች – በስማርት ሲቲ መሠረተ ልማት የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት በተለያዩ ቦታዎች ከሚገኙ ዘመናዊ ፖሎች ላይ የሚገጠሙ ደረጃ ሁለት ባትሪ መሙያዎች ሲሆኑ፣ አሽከርካሪዎች በድንገት ባትሪ ቢያልቅባቸው ለኤሌክትሪክ መሙያ በአማራጭነት የቀረቡ ናቸው፡፡

ወጥና ተጣጥሞ የሚሄድ የዲጂታል ቻርጂንግ ተሞክሮ በቴሌብር 

  • የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያው 24/7 አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ የሚሰራው በቴሌብር ሱፐርአፕ ላይ በሚገኝ መተግበሪያ ነው፡፡
  • የአገልግሎት ክፍያ ተገልጋዮች ፈጣን፣ ቀላል፣ ምቹ እና አስተማማኝ በሆነው ቴሌብር መፈጸም ይችላሉ፡፡
  • ያለማንም አጋዥነት (Self service) አሽከርካሪዎች አገልግሎቱን በራሳቸው ማግኘት እና ክፍያቸውንም በቴሌብር ሱአፐርአፕ መፈጸም ይችላሉ።
  • የስማርት ኦንላይን ክትትል ስርዓቱ በቴሌብር ሱፐርአፕ አማካኝነት መረጃዎችን ለማግኘት እና የመሙላት ሂደቱን ለማስተዳደር የሚያስችል ሲሆን፣ ሲስተሙ ከክላውድ ሰርቨሮች ጋር በፋይበር ኬብል እንዲሁም በ4ጂ እና 5ጂ ኔትወርክ የተገናኘ በመሆኑ እጅግ አስተማማኝ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ዲጂታል እና አረንጓዴ ትራንስፎርሜሽን ማጠናከር

ሀገራችን ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እና ሞቢሊቲ እየገሰገሰች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ኩባንያችን አስተማማኝ፣ ቀልጣፋ እና ቀጣይነት ያላቸው (future-ready) መሠረተ ልማቶችን በመገንባት እና የዲጂታል ፈጠራዎችን ተግባራዊ በማድግ ረገድ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል። በመሆኑም ይህ እጅግ ዘመናዊ እና ፈጣን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ ጣቢያ ኢትዮ ቴሌኮም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል መፍትሄዎች የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ገጽታ ለመለወጥ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

 

                                                    ኢትዮ ቴሌኮም

                                              የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives