ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ዘመን እየተሸጋገረች ከመሆኗ አንፃር የመንግስት እና የግሉ ሴክተር አገልግሎቶች በዲጂታል እንዲተኩ መደረጋቸው እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም በሰፊው ጥቅም ላይ ከመዋላቸው ጋር ተያይዞ አብዛኛው አገልግሎቶች የሳይበር ምህዳሩ ጥገኛ እየሆኑ በመምጣታቸው ለሳይበር ጥቃት እና ለቴሌኮም ማጭበርበር ተጋላጭነት ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑ ይታመናል፡፡

በዚህም መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም ለ4ኛ ጊዜ በኦክቶበር ወር የሚከበረውን የሳይበር ደህንነት ወር/መርሃግብር ሳይበር ጥቃትን የሚቋቋም ዲጂታል ሥነ ምህዳር መገንባት”/BUILDING CYBER RESILIENT DIGITAL ECOSYSTEM” በሚል መሪ ሀሳብ በተቋማችን ደረጃ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ5ኛ ጊዜ “የቁልፍ መሠረተ-ልማት ደህንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት/ Critical Infrastructure Security for Digital sovereignty” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደውን የሳይበር ደህንነት ወር/ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡  የሳይበር ደህንነት ወር/ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማዎች በባለድርሻ አካላት መካከል የሳይበር ጥቃትን የሚቋቋም የዲጂታል ስነ-ምህዳርን ለመገንባት ትብብርን ለመፍጠር፣ የሴክተሩ ተዋንያን በማጭበርበር /fraud/ ድርጊቶች እና በሳይበር ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሁለንተናዊ ትስስር በማሳደግ በዲጂታል አገልግሎት ዙሪያ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ ለመገንባት ነው። በተጨማሪም ይህ መርሃ ግብር ኩባንያችን ዓለም አቀፍ የመረጃ ደህንነት ሥርዓት ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚያደርገውን የትግበራ ፕሮግራሞችን (information security compliance certification programs) ይፋ ለማድረግ ወይም ለማስተዋወቅ እንዲሁም የመረጃ ደህንነትን እንደ ተቋማዊ ባህል በማካተት/በማጎልበት የክላውድ አገልግሎት እና እንደ ደህንነት አገልግሎት አቅርቦት (managed security service Provider – MSSP) የመሳሰሉ ሌሎች የዲጂታል አገልግሎቶችን ለሚፈልጉ ድርጅቶች ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።   ይህን የሳይበር ደህንነት ወር/ የግንዛቤ ማስጨበጫ የጋራ ፎረም ኩባንያችን ያካሄደው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንደ ፓሎ አልቶ፣ሲስኮ፣ ሁዋዌ፣ ዌል ክላውድ፣ ኬኔራ ዓለምአቀፍ ንግድ ድርጅት አይ.ኢ ሶሉሽን እና ጀማሪ የሥራ ፈጣሪዎች (start-ups) እንዲሁም የፋይናሺያል ተቋማት፣ የሬጉላቶሪ/የተቆጣጣሪ አካላት፣ የመንግስት እና የትምህርት ተቋማት እና ሚዲያዎች ጋር በመቀናጀት ሲሆን፣ ይህም ፎረም የዲጂታል ማህበረሰቡን ለማንቃትና የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል መርሃግብር ነው፡፡  

የዚህ ፕሮግራም ዓበይት አጀንዳዎች የወቅቱ የሳይበር ደህንነት ስነምህዳር (Current Cybersecurity Landscape) ፣ የተለመዱ የሳይበር ስጋቶች (Common Cyber Threats) ፣ የሳይበር ደህንነት ቁልፍ ጉዳዮች (Pillars of Cybersecurity) እና ምርጥ የባለድርሻ አካላትን ተሞክሮዎች ማጋራት የሚሉት አርዕስተ ጉዳዮች ይገኙበታል።

በተለይ ይህ መርሃግብር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር የፋይናንሺያል ሳይበር ማጭበርበርን /financial cyber-fraud/ ለመከላከል፣ ደንበኞች ለዲጂታል አገልግሎት ያላቸው እምነት /a digital trust/ እንዲያድግ ለማድረግ፣ የደህንነት እና የቁጥጥር ስራዎች ተገዢነት/ ተናባቢነት (compliance) ባህልን ለማጎልበት ትልቅ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ እንደ መለያ መውሰድ /account takeover፣ የተቋማት የውስጥ ማጭበርበር /internal fraud/ መከላከል፣ የደንበኝነት ምዝገባን መሰረት ያደረገ ማጭበርበር /subscription-based fraud/ ፣ የማንነት ስርቆት /identity theft/፣ የሲም መቀያየር ማጭበርበር /SIM swap fraud/፣ በህገወጥ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ የማስመሰል ድርጊት /money laundry/፣ ማህበራዊ ምህንድስና / social engineering /እና በመሳሰሉት የሳይበር ጥቃቶች ወይም የማጭበርበር ድርጊቶች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል፡፡

የሳይበር ደህንነት ከአሁን በኋላ የግለሰቦች እና የተቋማት ስጋት ብቻ አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከቴክሎጂው እድገት ጋር እየተወሳሰበ እና እየተራቀቀ በመምጣቱ እና እያደረሰ የሚገኘውም ጉዳት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳዩ ከተቋማት እና ግለሰቦች አልፎ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ሆኗል። ስለዚህ የሳይበር ምህዳር ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሁሉም በጋራ ሊረባረብ ይገባል። 

በአጠቃላይ ድርጅቶችን ከሳይበር ስጋት ለመጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እና ቅንጅትን ከማጠናከር ባሻገር መደበኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮችን ማካሄድ፣ የመረጃ ደህንነት ፖሊሲዎችን፣ሂደቶችንና መመሪያዎችን ሥራ ላይ ማዋል እንዲሁም ትክክለኛ የመረጃ ደህንነት ቁጥጥርን መስፈን፣ ሁሉንም የደህንነት መቆጣጠሪያ ገጽታዎችን ማዘመን፣ መደበኛ የመጠባበቂያ ዘዴ እና አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን የመከታተል ስርዓቶችን ለመተግበር ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል፡፡

                                                         ኢትዮ ቴሌኮም 

                                              ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives