ኩባንያችን፣ በራዕዩና በተልዕኮው እንዲሁም በሦስት ዓመት ሊድ (LEAD) የዕድገት ስትራቴጂው ላይ እንደተመለከተው ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር (Beyond Connectivity) መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ በመሆን የደንበኞቹን የዕለት ተዕለት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ለማዘመን እና ለማሳለጥ (Empowering Businesses with Cloud Service) የሚያስችለውን የቴሌክላውድ አገልግሎቱን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል፡፡
የክላውድ ኮምፒውቲንግ አገልግሎት ተቋማት የራሳቸው የመረጃ ማዕከል እንዲሁም ለማዕከሉ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ሳያስፈልጋቸው ካሉበት ሆነው (virtually) የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢዎች ዓለም የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መሠረት አድርገው በገነቧቸውና ደህንነታቸው በተጠበቁ የመረጃ ማዕከላት መረጃዎቻቸውን ማከማቸት፣ መቀመር ብሎም የተለያዩ አገልግሎቶች ማግኘት የሚያስችል የዲጂታል ሶሉሽን ነው፡፡
ኩባንያችንም በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችት እና አጠቃቀም እንዲሁም ተዛማች የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሠረት በማድረግ እጅግ አስተማማኝ የክላውድ ማዕከላትን መሠረተ ልማት እና አስፈላጊ ግብአቶችን ሁሉ በማሟላት ቴሌክላውድ አገልግሎትን በይፋ ለደንበኞቹ ማቅረብ መጀመሩን በደስታ ይገልጻል፡፡
ኩባንያችን የክላውድ አገልግሎቶቹን በሶስት አማራጭ ያቀረበ ሲሆን፤
- Infrastructure as a Service (IaaS) ተጠቃሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ ካሉበት ሆነው የግል መረጃዎቻቸውን ማስቀመጥ፣ መቀመር፣ ለደንበኞቻቸው የተለያዩ አገልግሎችን መስጠት የሚያስችል የክላውድ አገልግሎት
- Platform as a Service (PaaS)- በዋነኛነት የሶፍትዌር አልሚዎች ካሉበት ሆነው ላበለፀጓቸው ሶፍትዌሮች የተሟላ የዳታቤዝ ማኔጅመንት ሲስተም (MySQL DB) መጠቀም ያስችላቸዋል፡፡
- Software as a Service (SaaS)- ደንበኞች የተለያዩ በውጭ ምንዛሪ የላይሰንስ ክፍያ በመክፈል ያገኟቸው የነበሩ ሶፍትዌሮችን ከቴሌክላውድ በተመጣጣኝ ክፍያ በብር ማግኘት የሚችሉበት አገልግሎት ነው፡፡ ኩባንያችን ለመነሻነት የሚከተሉትን ሶስት አገልግሎቶች ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ የተለያዩ ተጨማሪ ሶፍትዌሮችን የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
- Oneoffice productivity and collaboration solution ደንበኞች በቢሮዎቻችው የጽሁፍና ሌሎች የቢሮ አገልግሎቶች የሚያከናውኑበት የኦፊስ መተግበሪያ (Application) ነው፡፡
- Video Management System (VMS) ደንበኞች ይህን አገልግሎት በመጠቀም የደህንነት የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን በማገናኘት የቪዲዮ ማስተዳደሪያ ሲስተም እና የሚፈልጉትን ያህል የዳታ ቋት ማግኘት ይችላሉ፡፡
- Smart Education productivity /Ulearning የትምህርት ተቋማት በስማርት ትምህርት በመታገዝ የርቀት እና የገጽ-ለገጽ ትምህርትን በቪዲዮ ጭምር በመታገዝ በዘመናዊ መልኩ በመስጠት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያገኙበት ሲሆን ለተማሪዎቻቸው የተሟላ ቤተ-ሙከራ፣ ማስታወሻ አያያዝ የትምሕርት ግብአቶችን ማጋራት፣ የትምህርት መርጃ እና ምዘና ማካሄድ ይችላሉ፡፡
የቴሌክላውድ አገልግሎትን በመጠቀም ድርጅቶች እና ተቋማት ለቴክኖሎጂ መረጣ፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ፣ ስልጠና እና ጥገና የሚወስደውን ጊዜ እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ ክፍያ በማስቀረት ተቋማት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው እና የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ ላይ ብቻ እንዲየያተኩሩ በማድረግ ተወዳዳሪነታቸው እና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላይ ፍላጎትን ተከትሎ ሊስፋፋ የሚችል የሪሶርስ አጠቃቀም ተግባራዊ የሆነበት በመሆኑ በመሆኑ አላስፈላጊ ወጪን ያስቀራል፡፡
በዚህ አስተማማኝና ደሀንነቱ በተጠበቀ የክላውድ አገልግሎት ለመጠቀም የሚሹ ደንበኞቻችን በድህረ ገጻችን telecloud.ethiotelecom.et ተጠቅመው አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉና ክፍያቸውንም ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ በሆነው ቴሌብር ባሉበት በመክፈል ማግኘት የሚችሉ ሲሆን ፍላጎታቸውን በኦንላይን ማከናወን በማይችሉበት ወቅት ወይም የቴክኒክ ድጋፍ እና ምክር በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የአገልግሎት መስጫ ማዕከሎቻችንን በመጎብኘት ድጋፍ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን በአክብሮት እየገለጽን፣ በቀጣይም ዓለማችን የደረሰበትን ዘመን አፈራሽ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለውድ ደንበኞቻችን ተደራሽ በማድረግ ሕይወትን የማቅለል፣ ቢዝነስን የማሳለጥ እና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ተግባራችንን የምንቀጥል መሆኑን እንገልጻለን፡፡
ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም