ኢትዮ ቴሌኮም እና የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የዲጂታል ሎተሪ ለመጀመር ስምምነት ፈጸሙ!
ኢትዮ ቴሌኮም እና የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር በቴሌብር እና በ605 አጭር የጽሁፍ መልዕክት የዲጂታል ሎተሪ ለመጀመር በዛሬው ዕለት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ ይህም የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከዚህ በፊት ለህትመት እና ሌሎች ተያያዥነት ላላቸው ስራዎች ያወጣው የነበረውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ እና ለደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡
የዲጂታል ሎተሪ አገልግሎት መጀመር የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ቀደም ሲል በወረቀት ትኬት ብቻ ሲያካሂድ ከነበረው የሎተሪ ሽያጭ በተጨማሪ የዲጂታል ሎተሪ ሽያጭ አገልግሎትን እንደአማራጭነት በማቅረብ እና ከቴሌብር ሲስተም ጋር በማስተሳሰር የአገልግሎት ሽፋን እና ተደራሽነትን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም ባሻገር ደንበኞቹ ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብርን በመጠቀም በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሆነው የሎተሪ ትኬቶችን እንዲገዙ ያስችላቸዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ሎተሪ በቴሌብር ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ከብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር በዛሬው ዕለት የተፈራረመ ሲሆን፣ ይህም የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከዚህ በፊት ለህትመት እና ሌሎች ተያያዥነት ላላቸው ስራዎች ያወጣው የነበረውን ወጪ የሚቀንስ ይሆናል፡፡
ደንበኞች አድማስ ሎተሪ የተሰኘውን የዲጂታል ትኬቶች በቴሌብር አጭር ቁጥር *127# ላይ በመደወል እንዲሁም ወደ 605 ላይ A ብለው ወይም ማንኛውንም ፊደል በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ መግዛት ይችላሉ፡፡ ደንበኞች የትኬት ግዥውን እንደፈጸሙ ወዲያውኑ የሎተሪ ትኬት ቁጥር እና የኤሌክትሮኒክ ትኬት እጣው የሚጠናቀቅበት ቀን ትኬቱን በገዙበት የዲጂታል ሎተሪ አማራጭ ማለትም ከቴሌብር በ127 ወይም ከብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር በ605 የሚደርሳቸው ሲሆን፣ የሎተሪ ትኬት ዋጋም ደንበኞች ካላቸው የቴሌብር አካውንት ተቀማጭ ገንዘብ/አየር ሰዓት ላይ ተቀናሽ የሚደረግ ይሆናል፡፡
የቴሌብር የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ለዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስፋፋት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ዓለምአቀፍ ገንዘብን በቀላሉ ለመቀበል፣ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ክፍያ ገንዘብ ለማስተላለፍ እና ልዩ ልዩ ግብይቶችን በርቀት ወይም በየትኛው ጊዜ እና ቦታ ሆኖ ለማከናወን ክፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን፣ አገልግሎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ 21.14 ሚሊዮን ደንበኞች፣ 89 ዋና ወኪሎች፣ 74. 82 ሺህ ወኪሎች እና 21.65 ሺህ ነጋዴዎች ማፍራት ችሏል፡፡
በተጨማሪም በቴሌብር አማካኝነት የሚካሄደው የግብይት መጠን (transaction amount) 25.67 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከ13 ባንኮች ጋር ከባንክ ወደ ቴሌብር እና ከ10 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ ገንዘብ ለማስተላለፍ ትስስር መፍጠሩ ለዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ያለውን ከፍተኛ ተመራጭነት ያሳያል፡፡
ኩባንያችን በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬትን፣ የመብራት አገልግሎት፣ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን፣ የውሃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤቶች የወርሃዊ አገልግሎት ክፍያን፣ የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /ራይድ/ አገልግሎት ክፍያን፣ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ክፍያን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የገቢ ግብር ክፍያዎችን በቴሌብር ለማከናወን የሚያስችል የጋራ ስምምነትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች የአገልግሎት ክፍያዎቻቸውን በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችል ስምምነት አድርጓል፡፡
በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርአታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርአት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው መፈጸም እንዲችሉ ጥረት በማድረግ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም
ነሐሴ 8 ቀን 2014 ዓ.ም.