ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስነምህዳርን የሚቀይሩ፣ ተቋማዊ አሠራርን የሚያዘምኑ እና የዜጎቻችንን የዕለት ተዕለት አኗኗር የሚያሻሽሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን በቁርጠኝነት በማቅረብ በሰፊው ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም የዲጂታል ሶሉሽኖችን ተደራሽነት ይበልጥ በማስፋት የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረግ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

 
በዚህ መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር የክልሉን ፍርድ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ለማገዝ እና ለዜጎች ይበልጥ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ እና ፈጣን ፍትህ ለመስጠት የሚያስችል በዲጂታል የታገዘ የስማርት ዳኝነት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት አድርጓል፡፡


በስምምነቱ መሠረት ኩባንያችን አስተማማኝ እና ደረጃውን የጠበቀ የኔትወርክ መሰረተ-ልማት፣ ደህንነቱን የጠበቀ አስተማማኝ የሞጁላር መረጃ ማዕከል፣ የክላውድ አገልግሎት፣ የኔትዎርክ ኦፕሬሽን መቆጣጠሪያ ማዕከል እና በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን የሚያስተሳስር ኔትወርክ በመገንባት የሚያስረክብ ሲሆን፣ ይህም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተግባራዊ በሚያደርገው የስማርት ፍርድ ቤት አሠራር (Smart Court) አማካኝነት የሚሰጡ የፍትህ አገልግሎቶች ለተገልጋዮች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡

 
ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ተቋማት መካከል የነበሩትን የቴሌኮም አገልግሎቶች እና የትብብር ሥራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ተፈጻሚ ለማድረግ በተለይም በሁለቱ ተቋማት መካከል የአቅም ግንባታ፣ ሥልጠና፣ የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያስችላል፡፡


የመሠረተ ልማቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአሁኑ ወቅት በክልሉ ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን የዳኝነት አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ፣ አስተማማኝ፣ ተደራሽ፣ ባለድርሻ አካላት በቀላሉ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ጊዜ እና ገንዘብን ለመቆጠብ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ግልጸኝነትን ለማስፈን እንዲሁም ዜጎች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

 
በሌላ በኩል የዚህ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ መጠናቀቅ ዜጎች የፍርድ ቤት ጉዳይ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ፣ የመረጃዎቻቸው ደህንነት የተጠበቀ እንዲሆን፣ ግልጽ የሆነ የፍትሕ አሰራርን ለማስፈን፣ የፍርድ ቤት ጉዳይ መረጃዎችን ለመመርመር፣ ውጤታማ እና ጥራት ያለው የፍትሕ አገልግሎት ለማግኘት እና ለመሳሰሉት ጉልህ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡

 
በቀጣይም ኩባንያችን በሊድ የዕድገት ስትራቴጂው መሠረት ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር እያከናወነው የሚገኘውን ሰፊ የዲጂታላይዜሽን ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን ማደረጉን እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡

                                                     ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም
                                                            ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives