ኢትዮ ቴሌኮም እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የገቢ ግብር ክፍያን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ሥርዓትን ተግባራዊ አደረጉ!

ኩባንያችን ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ጉዞ እየገፋበት የሚገኝ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብር በቴሌብር መክፈል የሚያስችላቸውን አሰራር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ጋር ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረጃ ሐ ግብርካፋዮች ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ የሆነውን የዘመኑን የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሆነው የግብር ክፍያቸውን መፈጸም ይችላሉ፡፡

በዚህ ተግባራዊ በሆነው የግብር ክፍያ ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት ግብራቸውን የሚከፍሉ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ያለምንም እንግልት እና ውጣውረድ በወቅቱ ግብራቸውን እንዲከፍሉ፣ ለከፈሉት የአገልግሎት ክፍያ ማስረጃው በቅርብ እንዲኖራቸው፣ ግብር ለመክፈል የግብር መክፈያ ጣቢያ በአካል ሲሄዱ የሚደርሰውን የገንዘብና የጊዜ ብክነት፣ የትራንስፖርት እና ሰነዶችን ኮፒ ለማድረግ የሚያደርጉትን ወጪ በማስቀረት በየትኛውም ቦታ እና ሰዓት በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር *127# በመጠቀም ግብራቸውን በወቅቱ ለመክፈል ያስችላቸዋል፡፡

ይህ የግብር ክፍያ ሥርዓት ከሐምሌ 1 ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለ እና ከ300 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች በክፍያ ሥረዓቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን እስካሁን ድረስ 679 ግብር ከፋዮች 4 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በቴሌብር አማካኝነት መክፈል ችለዋል፡፡

ግብር ከፋዮች በሞባይል ስልካቸው ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በ7075 በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በሚደርሳቸው የክፍያ ማዘዣ ቁጥርን በመጠቀም ክፍያቸውን ሲፈጽሙ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ከ7075 እንዲሁም ከ127 የክፍያ ማረጋገጫ መልዕክት የሚደርሳቸው ሲሆን ለቴሌብር አገልግሎት ያልተመዘገቡ ከሆነ መመዝብ እና አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ደንበኞች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከላት እንዲሁም የቴሌብር ህጋዊ ወኪሎች በአካል በመሄድ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ ገንዘብ ተቀማጭ በማድረግ የግብር ክፍያቸውን በቀላሉ በቴሌብር መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፣ የባንክ አካውንት ያላቸው ደንበኞች ከቴሌብር ጋር ትስስር ባደረጉ ባንኮች በኩል ወደ ቴሌብር አካውንታቸው ገንዘብ በማስተላለፍ እንዲሁም የቴሌብር አካውንት ያላቸው ነገር ግን የባንክ አካውንት የሌላቸው ግብር ከፋዮች ደግሞ ምንም አይነት የባንክ አካውንት ሳያስፈልጋቸው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ አቢሲንያባንክ፣ ዳሽን ባንክ፣ እናት ባንክ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ ወጋገን ባንክ እና ንብ ባንክ ቅርንጫፎች በአካል በመሄድ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ ይቸላሉ፡፡

የቴሌብር የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ለዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስፋፋት ጉልህ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ21 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ 89 ዋና ወኪሎች፣ 73 ሺህ ወኪሎች እና 21ሺህ ነጋዴዎች ማፍራት የቻለ ሲሆን 25 ቢሊዮን ብር በላይ የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውርም ተደርጎበታል ከ13 ባንኮች ጋር ከባንክ ወደ ቴሌብር እና ከ11 ባንኮች ጋር ደግሞ ከቴሌብር ወደ ባንክ ገንዘብ ለማስተላለፍ ትስስርም መፈጠሩ ለዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ያለውን ከፍተኛ ተመራጭነት ያሳያል፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬትን፣ የመብራት አገልግሎት፣ የትራፊክ ደንብ መተላለፍ ቅጣትን፣ የውሃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤቶች የወርሃዊ አገልግሎት፣ የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /ራይድ/ አገልግሎት ክፍያን፣   የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ክፍያን እንዲሁም የዲጂታል ሎተሪ ሽያጭ በቴሌብር ለማከናወን የሚያስችል የጋራ ስምምነትን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች የአገልግሎት ክፍያዎቻቸውን በቴሌብር እንዲፈጽሙ የሚያስችል አሰራርን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርአታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርአት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

                                                                               ኢትዮ ቴሌኮም

                                                                         ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives