በሃገራችን ሁለንተናዊ የልማት እና የዕድገት ጉዞ ውስጥ ቀዳሚ የአስቻይነት ሚና የሚጫወቱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም፤ የባንክ እና የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የዲጂታል ብድር እና ቁጠባ አገልግሎቶችን በትብብር በማቅረብ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣንና ቀላል በሆነ አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በቴሌብር እንዲያገኙ የሚያስችል አገልግሎት በዛሬው እለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ሁለቱ ተቋማት የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ፤ ለግለሰብ እና በንግድ ስራ ለተሰማሩ ተቋማት እንዲሁም ህጋዊ ወኪሎች የአነስተኛ ቁጠባ እና ብድር አገልግሎቶችን በቴሌብር አስጀምረዋል፡፡ የግለሰብ ደንበኞች እና ተቋማት በቴሌብር የሚያከናውኗቸውን ግብይቶች መሰረት አድርጎ በሚሰራ የብድር ቀመር ስሌት (Credit Score) እንዲሁም በቴሌብር የደሞዝ ተከፋይ መሆናቸውን መነሻ በማድረግ ያለ ማስያዥያ (non-Collateral) በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ ብድሮችን ማግኘት ይችላሉ፡፡ አገልግሎቶቹም፡ –
ስንቅ፡– ደንበኞች ከወለድ ነጻ ወይም የተለያየ የወለድ ምጣኔ የሚታሰብባቸው የተንቀሳቃሽ እና የጊዜ ገደብ ተቀማጭ የቁጠባ አገልግሎት፣
እንደራስ፡- የግለሰብ ደንበኞች በቴሌብር እንደሚያከናውኑት የግብይት መጠን እስከ ብር 15,000 ድረስ የአነስተኛ ብድር አገልግሎት፣
ድልድይ፡- ለነጋዴዎች/ወኪሎች አነስተኛ ንግድ/ቢዝነስ እንዲጀምሩ ወይም እንዲያስፋፉ እስከ ብር 50,000 የሚደርስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል አገልግሎት እንዲሁም፤
አድራሽ፡- ወርሃዊ ደመወዛቸው በቴሌብር ለሚከፈላቸው የግል እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች ለደሞዝ መዳረሻ እስከ 50,000 ብር ድረስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችሉ የብድር አማራጮች ናቸው፡፡
ይህ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ የሚሰጥ አነስተኛ የብድር አገልግሎትን ልዩ የሚያደርገው በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ደንበኞች ተያዥ ሳያስፈልጋቸው ያለዋስትና (non-Collateral) የቴሌብር እና የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመሆናቸው ብቻ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሚታገዝ የብድር ቀመር ስሌት (Credit Score) የብድር አገልግሎት ማግኘት መቻላቸው ሲሆን፣ የተበደሩትን ብድር በወቅቱ በመመለስና የተለያዩ ግብይቶችን በመፈጸም የክሬዲት ስኮር ነጥባቸውን ወይም መበደር የሚችሉት የገንዘብ መጠን ማሳደግ ይችላሉ፡፡
በሃገራችን በባንኩ ዘርፍ ቀዳሚ የሆነውና ላለፉት 82 ዓመታት ሰፊ የባንክ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር አብሮ እየተራመደ እና አሠራሩን እያዘመነ በቴክኖሎጂ የተደገፉ የባንክ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ባንክ ሲሆን፣ በተለይ “የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሴክተር የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የንግድ ባንክ መሆን” የሚለውን ራዕዩን ደረጃ በደረጃ በማሳካት በቅርቡ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ከ1 ትሪሊየን ብር በላይ መሻገሩ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ80 ዓመታት የፋይናንስ ዘርፍ ቆይታው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት በመሆን የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው እንዲጎለብት ጉልህ አስተዋፅዎ ያበረከተ አንጋፋ የፋይናንስ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ ዘርፍ ተደራሽነትን በማስፋት፣ የህብረተሰቡን የቁጠባ ባህል በማበረታታት፣ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና አገራዊ ገቢና ወጪ ንግድን በማሳለጥ ፣ አዳዲስ እና ዘመኑን የዋጁ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ፣ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት በማገዝ እና የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ እንዲሆን በማገዝ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ያሳረፈው አሻራ እጅግ የጎላ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ ያለቸውን የመንግሥት፣ የግበረሰናይ እና የሌሎች ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን በገንዘብ በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ደረጃ እየተወጣ ያለ የህዝብ ባንክ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በግንባር ቀደምትነት የተለያዩ የዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ የሀገሪቱን የክፍያ ሥርዓት የማዘመን ተግባሩን በበላይነት እየመራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የዲጂታል የገንዘብ ዝውውርን ማሳደግ እንደ አንድ ስትራቴጂክ ምሰሶ በመውሰድ በርካታ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የፋይናንስ አካታችነትን ማሳደግ ያለውን ጉልህ አስተፅዎ በመረዳት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን ማሳደግ ይቻል ዘንድ ከአንጋፋው ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በብድር አቅራቢነት ይሰራል፡፡ በቀጣይነት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ማሳካት ይቻል ዘንድ ባንኩ መሰል ስራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በአፍሪካ የቴሌኮም አገልግሎትን በማቅረብ ፈር ቀዳጅ የሆነውና ላለፉት 129 ዓመታት በሃገራችን የቴሌኮም አገልግሎት በማቅረብ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ቴሌኮም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ የመሆን ራዕዩ አካል የሆነውን ቴሌብር የሞባይል ክፍያ ሥርዓት ባስጀመረ በ2 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ34.05 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እና የዜጎች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እየሠራ ይገኛል፡፡
የቴሌብር የክፍያ ስርአትን የተቋማትን የቢዝነስ እንቅስቃሴ በማዘመን እና የማህበረሰባችንን የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴ እያቀለለ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይም መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ላልሆነው የማህበረሰብ ክፍል ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸውን እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የኦቨርድራፍት እና የቁጠባ አገልግሎቶች ማስጀመሩና በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በቀጣይም ሁለቱ አንጋፋ የሀገራችን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀደምት አጋርነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር የማህበረተሰባችንን የአኗኗር ዘይቤ ሊያሻሽሉ እና ሊያሳድጉ በሚችሉ የተለያዩ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች እንዲሁም በሌሎች መስኮች ላይ በጋራ የሚሰሩ ይሆናል፡፡
ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ