ኢትዮ ቴሌኮም ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር (beyond connectivity) የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ እና የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ሀገራችን እ.ኤ.አ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የያዘችውን ራዕይ ለማሳካት በከፍተኛ ቁርጠኝነት መጠነ ሰፊ ስራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የሚኒስቴር መ/ቤቱን የኦፕሬሽንና አገልግሎት አሠጣጥን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በማስቻል የውሃ እና ኢነርጂ ሃብቶች እና መሠረተ ልማቶች በዘመናዊ እና ቀልጣፋ ቴክኖሎጂ በማገዝ ውጤታማነትን የሚያሳድግ አሰራር በጋራ ለመተግበር የሚያስችል የስማርት አገልግሎት ሶሉሽንስ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። ይህ ስትራተጂያዊ ስምምነት በዋናነት የኢትዮ ቴሌኮምን ዘመናዊ የክላውድ መሠረተ ልማትን በመጠቀም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን እና በሥሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማትን መረጃ ዲጂታል ለማድረግ የሚያስችል ነው። በተጨማሪ በፌዴራል እና በክልል ደረጃ የሚገኙ መሥሪያ ቤቶችን ማለትም በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የውሃ ጽ/ቤቶችን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የዳታ እና የመረጃ ልውውጥ በወቅቱ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ስምምነቱ የስማርት አገልግሎት ሶሉሽኑን ከመረጃ ማዕከላት ጋር በማስተሳሰር ወደ ውስጥ እና ወደ ውጭ የሚፈሱ እንዲሁም የውሃ ሙሊት ደረጃዎችን በተፈለገው ቅጽበት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሶሉሽንስ መተግበርን የሚያካትት ሲሆን፣ የተቋማት፣ የንግድ እና የግል ደንበኞች የውሃ ቆጣሪዎችን ዲጂታል ማድረግ ላይም ያለመ ነው።የአጋርነት ስምምነቱ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርን እና በስሩ የሚገኙ የተጠሪ ተቋማትን የአሰራር ጥራት፣ ፍጥነትና ውጤታማነት ለማሳደግ፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲኖር ለማስቻል፣ የአገልግሎት አሰጣጡን አስተማማኝና ዘላቂነት ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ ስምምነቱ የደንበኞችን የክፍያ ሥርዓት ዲጂታል ማድረግን ጨምሮ በሁሉም የፕሮጀክቱ ዘርፎች ላይ ሁለገብ ሙያዊ ድጋፍ መስጠትን ያካትታል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለኢትዮ ቴሌኮም አስፈላጊ የሆኑ ዳታዎችን፣ መረጃዎችን እና ሰነዶችን የሚያቀርብ ሲሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ በስምምነት ማዕቀፉ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብ፣ ዲጂታል ሶሉሽኖችን መትከል እና ማስፋፋት፣ አስፈላጊውን ዳታና መረጃ ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ማጋራት፣ የቴክኒክ ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እና አመቺ የክፍያ ዘዴዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውና ቀልጣፋ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን የሚያቀርብ ይሆናል።

ኩባንያችን የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ባለው ጽኑ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ከተለያዩ መንግሥታዊና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በርካታ ስትራቴጂካዊ ስምምነቶችን የተፈራረመ ሲሆን፣ ይህም በዋናነት የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና ዘልማዳዊ አሰራሮች ላይ ሥርነቀል ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ፣ ለማህበረሰባችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ መሻሻል፣ የቢዝነስ አጋሮቻችን የአሰራር ሥርዓት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ ምርታማነታቸውን ለመጨመር እንዲሁም ሁሉም ደንበኞቻችን ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

                                                             ኢትዮ ቴሌኮም

ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም  

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives