“Enhanced Access to Digital Entertainment”
ኩባንያችን ዘመኑ የደረሰባቸውን አዳዲስ የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎች እና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በየጊዜው በስፋት ተግባራዊ በማድረግ የልዩ ልዩ ተቋማትንና የድርጅት ደንበኞችን አሰራር ስርዓት በማዘመን፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴ በማሳለጥ እንዲሁም የዜጎችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ በማሻሻል በሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኘውን የደንበኞቻችንን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እና የደንበኛ እርካታን እና ተሞክሮን የሚያሳድጉ እንዲሁም የዲጂታል አኗኗር ዘይቤን የሚያጎለብቱ ዘመኑ ያፈራቸውን የይዘት አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችሉ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡
በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን ከመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የመዝናኛውን ዘርፍ በእጅጉ ለማዘመን የሚያስችል የአጋርነት አገልግሎት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ደንበኞች ዘመናዊ የፋይበር ብሮድባንድ ኢንተርኔትና ሞባይል ዳታ ጥቅል አማካኝነት የተለያዩ የዲኤስቲቪ ኢትዮጵያ የመዝናኛ ቻናሎችን በጥቅል (package) አመራጭ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡
የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ለድርጅቶች እና ግለሰቦች ቨርቿል ስብሰባ፣ ክላውድ ጌም፣ የቀጥታ ትምህርት፣ የኦንላይን ግብይት፣ ኢኮሜርስ፣ ስማርት ሆም እንዲሁም የእለት ከእለት ሕይወትን በማዘመን እና ምርታማነትን በመጨመር ረገድ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
ኩባንያችን ከ4ጂ እና 5ጂ የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ በተጨማሪ የኮፐር መስመሮችን በፋይበር (Fiber to the home-FTTR/Fibere to the Home-FTTH) በመቀየር ለደንበኞች ፈጣን የኢንተርኔት መሰረተ ልማት እያዳረሰ ሲሆን ይህ እምቅ አቅም በዛሬው ዕለት ይፋ ላደረግነው በፋይበር ብሮድባንድ ኢንተርኔት እና በሞባይል ዳታ ጥቅሎች የሚሰሩ ልዩ ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ከዲኤስቲቪ ጋር በአጋርነት ለማቅረብ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡
አገልግሎቱ በተለይም የደንበኞችን ዲጂታል የአኗኗር ዘይቤ (Digital Lifestyle) በማሻሻል የመዝናኛ አገልግሎቶችን በቀላሉ ለማግኘት እንዲሁም በቴሌብር አማካኝነት በተቀላጠፈ ሁኔታ ሁለት አገልግሎቶችን በአንድ የቢል ክፍያ ለመፈጸም፣ የመዝናኛ አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ፣ በኢንተርኔት አማካኝነት የዲኤስቲቪ ስትሪም ይዘቶችን በቅናሽ ለማግኘት፣ ደንበኞች የቀጥታ ስርጭቶችን፣ ፊልሞችን፣ ድራማዎችን፣ ዜናዎችን እና የተለያዩ ፕሮግራሞችን እንደፍላጎቶቻቸው በማንኛውም ጊዜና ቦታ ስማርት በሆኑ እና ባልሆኑ ቴሌቪዥኖች፣ በስማርት ስልክና በኮምፒውተር አማካኝነት ለማግኘት የሚያስችል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም አገልግሎቱ የሳተላይት ዲሽ ሳህን እና ኬብል የማያስፈልገው በመሆኑ የከተሞችን ውበት ከመጨመር ባሻገር የብልሽት ጥገናን በቀላሉ ለማከናወን ያስችላል፡፡
አገልግሎቱ የተለያዩ ወርሃዊ የሞባይል ዳታ ጥቅል አማራጮችን የያዘ የዲኤስቲቪ ጎጆ፣ ቤተሰብ፣ ሜዳ፣ ሜዳ ፕላስ እና ፕሪሚየም ተወዳጅ ሀገርኛ ጥቅሎችን ጨምሮ የሀገር ውጪ ቻናሎችን እስከ 35 በመቶ ቅናሽ የተደረገባቸውን ጥቅሎች በቀላሉ በቴሌብር እና በኢትዮ ገበታ (*999#) በመግዛት እንዲሁም በፋይበር ብሮድባንድ ኢንተርኔት አማካኝነት እስከ 26.5 በመቶ ቅናሽ የተደረገባቸውን ጥቅሎችን በሽያጭ ማዕከሎቻችን በመግዛት በፈለጉት ቦታ ሆነው የመዝናኛ ፕሮግራሞችን መከታተል ያስችላል።
ኩባንያችን አካታችና ተደራሽ የዲጂታል አገልግሎቶችን፣ የደንበኞችን የዲጂታል አኗኗር ዘይቤ የሚያሟሉ መፍትሔዎችን (ሶሉሽኖችን) እንዲሁም አስቻይ መሰረተ ልማቶችን ለመዘርጋና አገልግሎቶችን ለማስጀመር በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህም በመላ አገሪቱ ሁሉን አቀፍ እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የዲጂታል አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረብን መሆናችንን ያረጋግጣል።
መጋቢት 19 ቀን 2017 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም