ኩባንያችን በሚሰጠው አገልግሎት የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለመደገፍና የአስቻይነት ሚናውን ለመጫወት በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን በተለይም ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ያሉ የዲጂታል ሶሉሽንስ ላይ ትኩረት በማድረግ ግለሰቦችና ድርጅቶች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲሁም ቢዝነሶቻቸውን የበለጠ ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና በኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች መካከል ከዚህ ቀደም ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ለማሳደግና ውስጣዊ አቅሞችን ለአገራዊ ተልዕኮ አቀናጅቶ ለመጠቀም የጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ፣ ኩባንያችን ወደውጭ ሃገራት ዜጎችን የሚልኩ ህጋዊ ኤጀንሲዎች ፍቃድ ለማውጣት እና ተዛማጅ ክፍያዎችን በቴሌብር አማካኝነት ለመፈጸም የሚያስችላቸው ሥራ ተግባራዊ ከማድረጉ ባሻገር ወደ ውጭ ሃገራት ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች በተዘጋጀላቸው የሮሚንግ አገልግሎት አማካኝነት በያዙት የሃገር ቤት ሲም ካርድ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም ደህንነቱን አስተማማኝ በሆነው የቴሌብር ሃዋላ አማካይነት ገንዘብ ወደ ሃገር ቤት ለሚልኩ የማበረታቻ ልዩ ጥቅሎች ዝግጅት አጠናቋል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያችን የሚኒስቴር መ/ቤቱን አሰራር ለማዘመን የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን ለማቅረብ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ያከናወነ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የሚኒስቴር መ/ቤቱን የዳታ ሴንተር ማዕከላት የማዘመን፣ ቅርንጫፎችን ከማዕከል እና እርስበርስ በፈጣን ኢንተርኔት የማስተሳሰር፣ የጥሪ- የግንኙነት ማዕከል አገልግሎት ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች በማከናወን በቀጣይም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሶሉሽኖችን በስፋት ለማቅረብ እና የስራ ፈጠራን ለማበረታታት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ የዜጎችን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የፊርማ ሥነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት አከናውኗል፡፡

በቀጣይም በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚከናወኑ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የስራ ፈጠራ ሀሳቦች እንዲያጎለብቱ በወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የተመረቱ የፈጠራ ሥራዎችን በስፋት በመጠቀም፣ ኢንተርፕርነርና ኢንቨስትመንት እንዲሳለጥና እንዲበረታታ በማገዝ እና ለአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች አስፈላጊ የቴክኖሎጂና ድጋፎች በማድረግ በሀገር ውስጥም ሆነ ባህር ማዶ ያሉ ዜጎች እኩል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የአስቻይነት ሚናውን የሚጫወት ይሆናል፡፡

ኩባንያችን የሀገራችን የዲጂታል ስነምህዳር ዕድገት ላይ መልካም አሻራ ከማሳረፍ ባሻገር የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱና ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን በአቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂና ሌሎች መሰል ድጋፎችን የማድረጉን ተግባር አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

ታህሳስ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives