ኩባንያችን ዘመኑ ያፈራቸውን የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች በመገንባት እና ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ተቋማት የሚያስፈልጋቸውን የዲጂታል አገልግሎቶች በማቅረብ አስተማማኝ የቴክኖሎጂ አጋር ለመሆን እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት በርካታ ስትራቴጂያዊ ሥራዎችን ተግባራዊ የማድረግ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኩባንያችን የሀገራችን ቀደምት እና ታሪካዊ ከሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ቀደም ሲል የነበረውን የቢዝነስ አጋርነት ስምምነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሳድግ እና አለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ሶሉሽን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት በዛሬው ዕለት አድርጓል፡፡

ስምምነቱ 18 ካምፓሶችን ከፍተኛ ፍጥነት ባለው የኢንተርኔት አገልግሎት (Wavelength service) ማገናኘት፣ ስማርት ክፍሎችን መገንባት፣ የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ ከፍተኛ ባንድዊድዝ ያለው የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ከ24 ሰዓት ክትትልና የጥገና ዋስትና የሚያካትት ሲሆን፣ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ዲቫይሶችና ተርሚናሎችን በረጅም ጊዜ ክፍያ ለማቅረብ፣ የእውቀት ሽግግር እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም የምርምር እና ፈጠራ ስራዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን የሚያስችል ይሆናል፡፡

በተጨማሪም የቴሌብር የዲጂታል የክፍያ ሥርዓትን በመጠቀም ነባር ወይም አዲስ ተመዝጋቢ ተማሪዎች የምዝገባ፣ የፈተና፣ የማመልከቻ፣ የሰነድ ማረጋገጫ (document authentication) ፣ የትምህርት ክፍያዎችን፣ የትምህርት ማስረጃዎችን (Official Transcript & student copy)፣ የአልሙኒ እና መሰል የአገልግሎት ክፍያዎችን ካሉበት ሆነው በመፈጸም አገልግሎት ለማግኘት የሚያባክኑትን ጊዜ እና ገንዘብ ለመቆጠብ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እና አስተዳደራዊ ወጪዎች ለመቀነስ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኩባንያችን ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተም የሙያ መስኮች የጋራ ካሪኩለም በመቅረጽ በድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዙሮች 152 የኩባንያችን ባለሙያዎች በመስኩ ሰልጥነው የተመረቁና ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰው የተሻለ ሙያዊ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣

በ2023 የትምህርት ዘመንም ለ4ኛ ጊዜ 53 ተማሪዎችን በቴሌኮሙኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግ እና ኢንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት ዘርፎች ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል ስምምነት ተደርጓል፡፡

ከዚህም ባሻገር ኩባንያችን በዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስር (UNIVERSITY INDUSTRY LINKAGE) አጋርነት መሰረት በኮሙኒኬሽን ኢንጂነሪንግ እና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፎች ለሚማሩ ተማሪዎች ለአራት ወራት የሥራ ላይ ስልጠና እንዲያገኙ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ 578 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሁም በመላ ሃገሪቱ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች 3,321 ተማሪዎች የኪስ ገንዘብ እየተሰጣቸው የተግባር ላይ ስልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፤ በተጨማሪም ኩባንያችን ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚማሩ 5,500 የገንዘብ ድጋፍ ለሚያሻቸው ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ለማገዝ በወር የ400 ብር የኪስ ገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 150 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡

ኩባንያችን ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በርካታ ስትራቴጂያዊ ስራዎችን በአጋርነት በመከወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይም ኩባንያችን የዩኒቨርሲቲውን የአሰራር ስርዓት ለማዘመን እና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የሚያደርገውን የቴክኖሎጂ እና መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

 

ግንቦት 23 ቀን 2015 .

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives