ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የደንበኞቹን ሰፊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እና አሰራሮችን በመዘርጋት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም በመዝናኛውን ዘርፍ ዲጂታላይዝ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸውን መተግበሪያዎች ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ለደንበኞች አስተዋውቋል፡፡

ኩባንያችን ተደራሽ እና ጥራቱን የጠበቀ አስተማማኝ የቴሌኮም እና አካታች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ ለተጠቃሚዎች በስፋት ተደራሽ የሆኑ የዲጂታል መዝናኛ አገልግሎቶችን በማቅረብ የኪነ ጥበብና የፈጠራ ባለሙያዎች የሚያበረታቱና የኪነጥበብ ሥራዎች ለማህበረሰቡ በቀጥታ ተደራሽ በማድረግ ባለሙያዎች የድካማቸውን ፍሬ እንዲያገኙ የሚያስችል፣ ለደንበኞች ምቹ የክፍያ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታዎችን የሚፈጥር የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንደየዝንባሌያቸው እየተዝናኑ ቁምነገር የሚገበዩባቸውንና ክህሎቶቻቸውን የሚያዳብሩባቸውና መንፈሳቸውን የሚያድሱበቸውን የዲጂታል አገልግሎቶች ከአጋሮቹ ጋር በትብብር አቅርቧል፡፡

በዚህም መሰረት ዛሬ ይፋ ከተደረጉት አራት አገልግሎቶች መካከል በሐበሻ ቪው የሚቀርበው አይፒቲቪ ወይም ቪዲዮ ስትሪሚንግ አንዱ ሲሆን፣ ይህም ደንበኞች የቀጥታ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ድራማዎችን፣ ፊልሞችን እና ሌሎች የተመረጡ በርካታ አገልግሎቶችን ኢንተርኔትን በመጠቀም በሞባይል ስልካቸው፣ በቴሌቪዥናቸው እና በኮምፒዩተራቸው ለመመልከት ያስችላቸዋል፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች በሐበሻ ቪው መተግበሪያ ወይም ድረገፅ እንዲሁም አጭር የጽሁፍ መልዕክት ወደ 9433 A ወይም B በመላክ የሚፈልጉትን ፓኬጅ መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡

ሰዋሰው የሙዚቃ ስትሪሚንግ ሌላኛው የመዝናኛው ዘርፍ የዲጂታል የተጨማሪ እሴት አገልግሎት ሲሆን፣ የሙዚቃ ወዳጆች እና አድናቂዎች ጥራታቸውን የጠበቁ የሃገር ውስጥ እና የውጭ ሙዚቃዎችን በአንድ ቦታ የሚያገኙበት እና የሚያደምጡበት አማራጭ የዲጂታል አገልግሎት ነው፡፡ የሙዚቃ አፍቃሪዎች የሚወዷቸውን ወይም አዲስ የሚለቀቁ ሙዚቃዎችን ከማዳመጥ ባሻገር ለጥሪ ማሳመሪያም ለመጠቀም ያስችላቸዋል፡፡ አገልግሎቱም በቴሌብር ሱፐርአፕ መተግበሪያ፣ በሰዋሰው ድረገፅ፣ በፕሌይ እና አፕ ስቶር እንዲሁም ወደ 9107 ላይ A ወይም B ብለው በመላክ እለታዊ እና ሳምንታዊ ጥቅሎችን መመዝገብ ይችላሉ፡፡

ሌላው በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረጉት ቴሌጌም እና ቴሌ ዊን የተሰኙ የሞባይል ጌሞች በቴክኖላቭ ኃ.የተ.የግ.ማ እና አይኮኔክት ዲጂታል ሰርቪስ የቀረቡ ሲሆን፣ ቴሌጌም አዋቂዎችም ሆኑ ታዳጊ ልጆች የተመረጡ የሞባይል ጌሞችን በአነስተኛ ክፍያ ያለገደብ እንዲያወርዱ እንዲሁም ጌሞችን ያለምንም ጣልቃ ገብ ማስታወቂያዎች እንዲጫወቱ የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ የቴሌ ጌሞችን ለማግኘት ደንበኞች Ok የሚል አጭር መልዕክት ወደ 927 በመላክ ወይም የቴሌጌም የሞባይል ፖርታል ላይ በመግባት መመዝገብ እና እንደምርጫቸው ጌሞችን በማውረድ መጠቀም ይችላሉ፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች በአይይኮኔክት የቀረቡትን የቴሌዊን ጌሞችን በቴሌ ዊን ድረገፅ ወይም በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ወደ *985# በመደወል የሚፈልጉትን ዕለታዊ ወይም ሳምንታዊ ጥቅሎችን መመዝገብ፣ የተለያዩ የመዝናኛ ጌሞችን በመጫወት ሲያሸንፉ እና ጥያቄዎችን ሲመልሱ አጓጊ ሽልማቶችን የሚያገኙ ሲሆን፣ ሎያል የሆኑ ደንበኞች ደግሞ ተጨማሪ ጌሞችን መጫወት የሚያስችል የቲኬት ሽልማቶችን ያገኛሉ፡፡

ኩባንያችን የዲጂታል አገልግሎት አማራጮችን አካታችነት እና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተለይም   የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት እና በኑሮ ዘይቤያቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረቡን እንዲሁም አስቻይ አሰራሮችን መዘርጋቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

           ሚያዝያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም

             ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives