ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በኃይል አቅርቦት ዙሪያ የጋራ ምክክር አደረገ፡፡
የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎችን ባሳተፈው በዚህ የምክክር መድረክ በሀገሪቱ ላይ ባሉ የኃይል አቅርቦት ችግሮች እና በዚህም የተነሳ በሚከሰቱ የኔትወርክ ጥራት (መቆራረጥና አለመገኘት) የችግር ምንጭ እና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የጋራ መድረኩ ያስፈለገው የቴሌኮም አገልግሎት ላይ የሚስተዋለው የኔትወርክ መቆራረጥና ጥራት ችግር በዋናነት ከኃይል አቅርቦት ጋር የተገናኘ በመሆኑና ይህም በአገልግሎት ተጠቃሚው ዘንድ የቅሬታ ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር በእለት ተእለት እንቅስቃሴና በማህበራዊ መስተጋብሮች ላይ ጫና አየፈጠረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ወቅት እንደተገለጸው ኢትዮ ቴሌኮም ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የኃይል ፍላጎት የሚያሟላው ከመብራት ኃይል /commercial power/፣ ከጄኔሬተርና ከሶላር የኃይል ምንጮች ሲሆን መብራት ኃይል 72 በመቶ ሳይቶችን ሲሸፍን ቀሪዎቹ በሶላርና በጄኔሬተር የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የመብራት ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ባለመሆኑ 4ዐ በመቶ ጣቢያዎች ላይ ጄኔሬተር እንደ አማራጭና መጠባበቂያ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሆን ቀሪ 24 በመቶ ጣቢያዎቸ በሶላር ኃይል አማራጭ የተሸፈኑ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዥ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቅ በመሆኑ ሀገሪቱን ለተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እንደሚዳርግ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው በጀት ዓመት ማግኘት ይገባው የነበረውን 2.1 ቢሊዮን ብር በኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት እንዳላገኘ የተጠቀሰ ሲሆን ከገቢ ማጣት በተጨማሪ ህብረተሰቡ ላይ አገልግሎቱ ባለመኖሩ ምክንያት የሚደርሰው መጉላላት ተገቢ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኤለክትሪክ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ የኃይል አቅርቦትን ለማሻሻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ያደረገ ቢሆንም ተቋሙ ባለው የበጀትና የመለዋወጫ እቃ አቅርቦት ውስንነቶች ምክንያት የኃይል አቅርቦት ችግሮችን በመፈለገው ፍጥነትና መጠን መፍታት ያለመቻሉ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ከዚህ ቀደሞ ከነበረው አሠራር በተለየ መልኩ ሁለቱ ተቋማት እነዚህን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ስምምነት ለመፈራረም እና ከዚህም ባለፈ በሁለቱ ተቋማት ውስጥ ያሉትን ሀብቶች በጋራ በመጠቀም የኃይል አቅርቦቱን በማሻሻል የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን ከፍ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ሁለቱም ተቋማት የሚያገለግሉት የአንድ ሀገር ህዝቦችን መሆኑን ጠቅሰው ጣት ከመጠቋቆም ይልቅ ችግሮችን የጋራ በማድረግ ተጋግዞና ተባብሮ በመስራት እንዲሁም በኢትዮ ቴሌኮም ያለውን ሐብት በጋራ ለመጠቀም የሚያስችሉ አሠራሮችን በመፍጠር የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ልንፈታ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎት ልማትን የመደገፍና የማቀላጠፍ ሚና መጫወት ያለባቸው መሆኑና በምንም አይነት ሁኔታ የልማት አደናቃፊ መሆን የለባቸውም ብለዋል፡፡
የሁለቱም ተቋማት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች የተጠቀሱትን ሥራዎች የሚተገብር ከሁለቱም ተቋሟት የተውጣጣ ግብረ ኃይል በማቋቋም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንዲገባ መመሪያ ያስተላለፉ ሲሆን በዚህም መሠረት በመጀመሪያው ዙር በአዲስ አበባ እና አዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የሚታዩ ችግሮችን ቅድሚያ በመስጠት እንደሚቀረፍ ገልጸዋል፡፡ ሁለቱም የሥራ ኃላፊዎች በተገልጋዩ ላይ ለደረሰው የአገልግሎት ጥራት መጓደል ይቅርታ ጠይቀው በተከታታይም አገልግሎቱን ለማሻሻል በጋራ በማቀድና በመቀናጀት እንዲሁም ሀብትን በጋራ በመጠቀም የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻልና ከህብረተሰቡ የሚነሱ የአገልግሎት ቅሬታዎችን ለመፍታት ቃል ገብተዋል፡፡