ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ስነምህዳርን የሚቀይሩ፣ ተቋማዊ አሰራርን የሚያዘምኑ እና የዜጎቻችንን የዕለት ተዕለት አኗኗር የሚያሻሽሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን በቁርጠኝነት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በተለይም በሀገራችን የዲጂታል ሶሉሽኖችን ተደራሽነት በማስፋት አካታችነትን ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የዲጂታል አገልግሎት ማስፋፊያ በማከናወን የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረግ ጉዞውን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር የዲጂታል ሶሉሽኖችን እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲሁም የሸገር ስማርት ሲቲ ፕሮጀክትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጅያዊ የአጋርነት ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡

 በዛሬው ዕለትም የዚሁ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎትን በቴሌብር ዲጂታል ለማድረግ እንዲሁም የአገልግሎት ክፍያን በቀላሉ በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና አስተማማኝ የስማርት ፓርኪንግ ሲስተም በሸገር ከተማ በይፋ አስጀምሯል፡፡

 የስማርት ፓርኪንግ ሲስተሙ በአቅራቢያ የሚገኙ የፓርኪንግ ቦታዎችን ከማወቅ ባሻገር ያልተያዘ የማቆሚያ ቦታን በቀላሉ በመለየት ተሽከርካሪ ለማቆም የሚያጠፉትን ጊዜ እና ጉልበት ለመቀነስ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ አስተማማኝ አገልግሎት ለማግኘት፣ ትክክለኛ ተመን ያለው የአገልግሎት ክፍያ በቴሌብር በመፈጸም ከተጋነነ የአገልግሎት ክፍያ እና ከዚሁ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ አለመግባባቶች፣ ካልተገባ ወጪ እና እንግልት የሚጠብቃቸው ሲሆን በቴሌብር የክፍያ ደረሰኝ ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡

 የስማርት ፓርኪንግ ሲስተሙ የከተማው አስተዳደር ህጋዊ የፓርኪንግ አገልግሎት ሰጪዎችን በአግባቡ ለመለየት እና ወደህጋዊ ማእቀፍ ያልገቡትን ለማስገባት፣ ከመኪና ማቆሚያ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ህገወጥነቶችን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር፣ የአገልግሎት ሰጪዎችን መረጃ በቀላሉ በኦንላይን (dashboard) በማግኘት በመረጃ ላይ የተመሰረተ አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት፣ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ተጨማሪ የፓርኪንግ ቦታዎችን ለማስፋፋት፣ በማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች እና ሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ህጋዊ አገልግሎት ሰጪዎችን ለማበረታታት እንዲሁም አስተዳደሩን የአገልግሎቱ ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ከማስቻል ባሻገር ከተማዋን ለነዋሪዎች፣ ጎብኚዎች እና ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ ያስችላል።

 ሲስተሙ በፓርኪንግ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ስለሚያስተናግዱት ተሽከርካሪ ተገቢው መረጃ እንዲኖራቸው፣ የአገልግሎት ክፍያ ሳይፈጽሙ ሊሄዱ የሚችሉ ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር፣ ያልተያዘ የማቆሚያ ቦታ ባሉበት ሆነው በቀላሉ በመለየት ለማስተናገድ፣ ተሽከርካሪዎችን በአግባቡ ለመረከብ እና ለማስረከብ፣ የተሽከርካሪ ቆይታ በቀላሉ በቴሌብር ተሰልቶ ክፍያ በመቀበል ዘመናዊ እና ቀልጣፋ የፓርኪንግ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም የቴሌብር አገልግሎት ወኪል በመሆን ተጨማሪ ገቢ ከማግኘት ባሻገር በቴሌብር ፋይናንሻል አገልግሎቶች የቁጠባ እና አነስተኛ ብድር ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላቸዋል፡፡

 የስማርት ፓርኪንግ ሲስተሙ ለስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች በቴሌብር ሱፐርአፕ ሾፌር መተግበሪያ እንዲሁም ለመደበኛ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ባለሙያዎቹ የፓርኪንግ አገልግሎት ጥያቄን/ትእዛዝ ለመቀበል የሚያስችላቸው የባለሙያ ሲስተም አለው፡፡ ሲስተሙ ስማርት የሞባይል ቀፎ ወይም መተግበሪያ የሌላቸው ተገልጋዮች በአጭር ቁጥር መልዕክት አማካይነት አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻል አካታችነትን ከግምት ያስገባ ነው፡፡

 ኩባንያችን የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚያፋጥኑ ኢኒሼቲቮች በመቅረጽ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ጋር አጋርነትን በመፍጠር የተቋማትን የአሰራር ስርዓት ለማዘመን የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ሶሉሽኖችን በማቅረብ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና መጫወቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።

ኢትዮ ቴሌኮም

ኅዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives