ኩባንያችን ከተቋቋመለት የቢዝነስ ዓላማ በተጨማሪ ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፈ ብዙ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን መልካም አሻራ እያሳረፈ ሲሆን፣ በተለይም የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ተጠቃሚነት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት እና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፍ፣ ደም ልገሳና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ በስፋት እና በንቃት የሚሳተፍባቸው አበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በእነዚህ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ በድምሩ 439.9 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሰረት “በጎነት” በተሰኘው መርሃ ግብር በመላው የሀገራችን ክፍሎች በ26 የበጎ አድራጎት ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ 7,112 አረጋዊያን እና ሴቶች አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለምገባ መርሃ ግብር ከ8.89 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ኩባንያችን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ቀን በመላው የሀገራችን ክፍሎች ከ19 በላይ በሚሆኑ የበጎ አድራጎት ማዕከላት ውስጥ ለሚገኙ 6,850 ነዋሪዎች ለአዲስ ዓመት መዋያ ወጪ የሚሆን የ5.2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያችን “ለነገ ተስፋዎች” በሚል መርህ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ 430 በላይ ት/ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ ከ70,000 በላይ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን የመማሪያ ደብተር ከ72.9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በስጦታ አበርክቷል፡፡ ኩባንያችን እንደ አንድ ሀገራዊ ተቋም የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ በዋናነትም የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ጫና ለመጋራት፣ ተማሪዎች መሰረታዊ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው እና በትምህርት ገበታቸው እንዲገኙ ለማስቻል እንዲሁም ነገ የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን ከመሰረታዊ ግንኙነት ባሻገር የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ የአስቻይነት ሚና ከመጫወቱ ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል እና የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የበኩሉን አስተዋፅዖ

እያበረከተ የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በማህበር ለተደራጁ 99 ወጣቶች 30 ተንቀሳቃሽ ሱቆችን ከ8.6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አስረክቧል፡፡

ይህም ለወጣቶቹ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የቴሌብር ህጋዊ ወኪል ሆነው በመስራት ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙ ሲሆን፣ በሚያካሄዱት የንግድ እንቅስቃሴ አማካኝነትም ያለዋስትና ብድር በማግኘት ንግዳቸውን ለማስፋፋት የሚያስችላቸው እድል የሚመቻች ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ ቀንም ኩባንያችን በጎነት ለሰብዓዊነት በሚል መርህ ከብሔራዊ የደም ባንክ ጋር በመተባበር በተቋሙ ዋና መ/ቤት፣ በዞን እና በሪጅን ጽ/ቤቶች በአጠቃላይ በ21 ቦታዎች የኩባንያችን ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች ደም በመለገስ የወገኖቻቸውን ውድ ሕይወት የሚታደጉበት መርሃግብር አዘጋጅቶ የወገን አለኝታነቱን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡

በ5ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመላው ሀገሪቱ ከ361 ሺህ በላይ ችግኞችን በ95 አካባቢዎች ላይ የተከለ ሲሆን፤ ከ1700 በላይ ወጣቶች በጉድጓድ ቁፋሮ እና ችግኝ ተከላ ተሰማርተው የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ የችግኝ ተከላው የተሳካ እንዲሆን ተቋሙ ከ16.64 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡

እንዲሁም በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎችን ለመመገብ እና መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል “ተንቀሳቃሽ የምገባ መርሃ ግብር ፕሮጀክት” በመቅረፅ ከ2,300 በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኤሌክትሪክ ምጣድ ስጦታ አድርጓል፡፡ በድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ለረሃብ የተጋለጡ ዜጎችን በተንቀሳቃሽ የምገባ አገልግሎት መመገብ እንዲችሉ በመጀመሪያው ምዕራፍ የ200 ምጣዶች ርክክብ ተደርጓል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ከ9.6 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

ኩባንያችን በደንበኞቹ የአኗኗር ዘይቤ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የዲጂታል መፍትሔዎችን፣ ዘመኑ የደረሰበትን የቴሌኮም አገልግሎቶች ከመተግበር እና የአሰራር ሥርዓቶችን ከመዘርጋት እንዲሁም አዳዲስ የቴሌኮም ምርት እና አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባሻገር ለህብረተሰባችን አስፈላጊ በሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች ሁሉ ድጋፎችን በማድረግ እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ሀገራዊ አለኝታነቱን እያረጋገጠ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives