ኢትዮ ቴሌኮም ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማሕበረሰባችን ከማስተዋወቅ እና በሰፊው ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ሀገራችን በዲጂታል አገልግሎት በአለም አቀፍ ደረጃ  የሚኖራትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን በቁርጠኝነት በማከናወን ላይ ያለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የዘመናችንን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በፍጥነት እያቀረበ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን እያደረገ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኘውን የደንበኞቻችንን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እና የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉ፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽሉ እንዲሁም ዘመኑ ያፈራቸውን አስተማማኝና ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችሉ የቴሌኮም እና ዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በስፋትና በቁርጠኝነት በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የሚያስችለውን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥቂት ሀገሮች ብቻ ተግባራዊ የተደረገውን የዓለማችን የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የሆነውን የአምስተኛውን ትውልድ የሞባይል አገልግሎት ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂግጂጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ባህር ዳር ከተሞች እና አካባቢያቸው ተግባራዊ አድርጓል፡፡

በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን በደቡብ ሪጂን ሀዋሳ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ጣቢያዎችን ግንባታ በማጠናቀቅ በከተማዋ አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመረ መሆኑን በታላቅ ደስታ ያበስራል፡፡

በዚህ መሠረት ኩባንያችን በሀዋሳ ከተማ፡- ፒያሳ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ሕንጻ አካባቢ፣ በፍቅር ሀይቅ አካባቢ፣ በወልደአማኑኤል ዱባለ አደባባይ፣ በዋንዛ/ የቀድሞው አውቶቡስ መናኸሪያ፣ በቅዱስ ገብርኤል አደባባይ፣ በደቡብ ክልል የፋይናንስ ጽ/ ቤት፣ በቅዱስ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን እና በኃይሌ ሪዞርት አካባቢዎች የሚገኙ የድርጅት እና ግለሰብ ደንበኞቻችን የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ትሩፋት ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ አድርጓል፡፡

የ5ኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ እስከ 10 ጊ.ባ በሰከንድ (Gbs) የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ዓለማችን የደረሰበት ዘመናዊ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ (Ultra-low latency) ረገድ ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ አገልግሎቱ በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ተግባራዊ መሆን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የደንበኞች የዳታ እና ኢንተርኔት ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል፡፡

የኩባንያችን የ5ኛው ትውልድ ኔትወርክ ተግባራዊ ማድረግ የኔትዎርክ መጨናነቅን በእጅጉ በመቀነስ ደንበኞች ጥራት ያለውና ፈጣን የኮሙኒኬሽን፣ ዲጂታል ሶሉሽኖች እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ህይወታቸውን እንዲያቀሉ ከማስቻል ባሻገር የኦንላይን ትምህርት፣ ስልጠና፣ መረጃ እና የመዝናኛ አገልግሎት አቅርቦት እንዲሁም የይዘት ፈጠራ (content creation)፣ ለጀማሪ የሶፍትዌር አበልጻጊዎች ኢኖቬሽን እና የሥራ ፈጠራን በማበረታታት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያሳድጋል፡፡ እንዲሁም የስማርት ስልክ ስርጸትን ለመጨመር መደላድል በመፍጠር የዲጂታል ሊትሬሲን በማሳደግ እና የዲጂታል ክፍተትን (digital divide) በማጥበብ አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም 5ጂ ኔትወርክን በማስፋፋት ላይ ያለው ለስማርት የጤና አገልግሎት እና ለሆስፒታል አስተዳደር፣ ለስማርት ግብርና፣ ለስማርት ትምህርት፣ ለስማርት ማዕድን፣ ለስማርት ማኑፋክቸሪንግ፣ ለስማርት ኤርፖርትና የጉዞ አገልግሎት፣ ለስማርት ትራንስፖርት፣ ለዘመናዊ የመኖሪያ ቤት (Smart home)፣ ለብሮድካስቲንግና ለመዝናኛ፣ ጌምን ጨምሮ በክላውድ ላይ ለተመሰረቱ የዲጂታል አገልግሎቶች እንዲሁም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ትሩፋቶች ለመጠቀም የሚያስችል ዘመናዊ የመሰረተ ልማት አቅም ለመፍጠር በማለም ነው፡፡

አገልግሎቱ ኩባንያችንን ወደ ዘመናዊ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ከማሸጋገር ባሻገር የቢዝነስ እና ተቋማት አሠራር በማዘመን ቅልጥፍና ለማምጣት፣ ምርታማነትን በመጨመር ገቢን ለማሳደግ፣ ብክነትን በመቀነስ ትርፋማነት ለማሳደግ፣ ምርትና አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንዲሁም መረጃን መሰረት ያደረገ (data-driven) ውሳኔ ለመስጠት በማስቻል እንዲሁም አስተማማኝ እና ለተልዕኮ-ወሳኝ የሆነ (mission critical) ቀጥተኛ (real time) የዳታ ፍሰትን በማረጋገጥ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር እና ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

ክቡራን ደንበኞች ኩባንያችን ይፋ ባደረገው ፈጣን የ5ጂ ኔትወርክ አማካይነት ያልተገደበ ዳታ፣ የመደበኛ መኖሪያ ቤት አገልግሎት እንዲሁም የተለያዩ የ5ጂ ጥቅል አማራጮችን መጠቀም የሚችሉ ሲሆን አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስችሉ የቴሌኮም መሳሪያዎችና ቀፎዎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡ 

ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives