ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የማህበረሰባችንን የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከዘርጋው የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ጋር የክላውድ ሶሉሽን አገልግሎቶችን፣ ከኩሉ ኔትወርክ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር እልፍ የሙዚቃ ስትሪሚንግ አገልግሎትን እንዲሁም ከሸድሊ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር የቴሌድራይቭ የሞባይል መረጃ ማስቀመጫ አገልግሎትን በአጋርነት ለደንበኞቻችን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ዛሬ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም ፈጽሟል፡፡
ኩባንያችን በያዝነው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ ይፋ ባደረገው የሦስት ዓመት መሪ (LEAD) የዕድገት ስትራቴጂ መሰረት ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር (Beyond Connectivity) መሪ የዲጂታል አገልግሎት አቅራቢ በመሆን የደንበኞቹን የዕለት ተዕለት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ለማዘመን እና ለማሳለጥ የሚያስችሉ አገልግሎቶችን እንደሚያቀርብ ቃል በገባው መሠረት በተከታታይ የተለያዩ ለግለሰብ እንዲሁም ለድርጅት ደንበኞቻችን አስተማማኝና ደህንነታቸው የተጠበቁ የዲጂታል አገልግሎቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ዛሬ ይፋ ከተደረጉት አገልግሎቶች መካከል ቴሌድራይቭ አንዱ ሲሆን በዚህ አገልግሎት ደንበኞች በሞባይል ስልኮቻቸው የሚገኙ እንደ ፎቶ፣ ቪዲዮና የመሳሰሉ ከፍ ያለ መጠን ያላቸውን ፋይሎች አስተማማኝ በሆነ የክላውድ መረጃ ቋት በማስቀመጥ በፈለጉ ጊዜ ሁሉ ማግኘት እና መጠቀም የሚችሉበት መፍትሄ ሲሆን የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሞባይል ስልካቸው ቢጠፋ ወይም ቢበላሽ ፋይሎቻቻውን ያለሃሳብ መልሰው ማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የስልክ አድራሻዎችን እና የፅሁፍ መልዕክት መረጃዎችንም እንዲሁ ማስቀመጥ የሚያስችል ሲሆን አገልግሎቱን ለማግኘት የቴሌድራይቭ መተግበሪያን ከጎግል ፕሌይስቶር እና አፕ ስቶር በማውረድ መጠቀም እና የአገልግሎት ክፍያውን በቴሌብር በቀላሉ መክፈል ይቻላል፡፡
ሌላው በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው የእልፍ ሙዚቃ መተግበሪያ ሲሆን፣ ይኸው አገልግሎትም ሙዚቃዎችን በመተግበሪያው በመግዛት የሞባይል ዳታ ሳይጠቀሙ በፈለጉ ጊዜ ማዳመጥ እንዲችሉ እንዲሁም በአምስት ቋንቋዎች የሚተላለፍ የቀጥታ ስርጭት (online) ሬዲዮ ፕሮግራም ያለው እና አገልግሎቱ በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርቧል፡፡
ኩባንያችንም በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችት እና አጠቃቀም እንዲሁም ተዛማጅ የክላውድ አገልግሎት ፍላጎትን መሠረት በማድረግ እጅግ አስተማማኝ የክላውድ ማዕከላት መሠረተ ልማትን እና አስፈላጊ ግብአቶችን ሁሉ በማሟላት ቴሌክላውድ አገልግሎትን በይፋ ለደንበኞቹ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ከዘርጋው የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ጋር በመተባበር የክላውድ ሶሉሽን አገልግሎቶችን በተለያዩ አማራጮች አቅርቧል፡፡
ለአብነትም፡- የ Infrastructure as a Service (IaaS) ተጠቃሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ ካሉበት ሆነው የግል መረጃዎቻቸውን ማስቀመጥ፣ መቀመር፣ ለደንበኞቻቸው የተለያዩ አገልግሎችን መስጠት የሚያስችል የክላውድ አገልግሎት እንዲሁም Software as a Service (SaaS)- ደንበኞች የተለያዩ በውጭ ምንዛሪ የፈቃድ ክፍያ በመክፈል ያገኟቸው የነበሩ ሶፍትዌሮችን በተመጣጣኝ ክፍያ በብር ማግኘት የሚችሉበት አገልግሎት ሲሆን፣ እንደ ኢ.አር.ፒ የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽን፣ የፋይል ማኔጅመነት ሲስተም፣ በቴሌብር የተደገፈ ኤሌክትሮኒክ ግብይት እና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ቀርበዋል፡፡
ኩባንያችን ከሚያቀርበው ተደራሽ እና ጥራቱን የጠበቀ አስተማማኝ የቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር አካታች የፋይናንስ አገልግሎትንና በርካታ የዲጂታል አገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ የማሕበረሰባችንን ሕይወት በማቅለል እና የተቋማትን አሰራር በማሻሻል የተያያዘውን ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጉዞ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡
ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም