ኢትዮ ቴሌኮም በየጊዜው የአገልግሎት ተደራሽነትን እና ጥራትን የሚያሻሽሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከመተግበር እና ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ለመስጠት ማሻሻያዎችን ከማድረግ ባሻገር የደንበኞቹን የአገልግሎት እርካታ የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
በዛሬው ዕለትም ደንበኞች ከኩባንያው ጋር ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር፣ ለደንበኝነታቸው ምስጋና ለማቅረብ እንዲሁም በሚጠቀሟቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ማለትም የድምጽ ጥሪ፣ የዳታ/ኢንተርኔት እና የአጭር መልዕክት አገልግሎት እንዲሁም በቴሌብር ለሚከናወኑ ግብይቶች፣ የአገልግሎት ክፍያዎች እና የአየር ሰዓት በቴሌብር በሚሞሉበት ወቅት በሚሰበስቧቸው ነጥቦች ሽልማቶችን ለደንበኞች ለማበርከት የሚያስችል አሻምቴሌ የተሰኘ የደንበኞች ማበረታቻ መርሃ-ግብር ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ለአሻምቴሌ መርሃግብር የሚመዘገቡ ደንበኞች የቴሌኮም አገልግሎቶችን (የድምፅ፣ የዳታ እና የአጭር ጽሑፍ መልዕክት) ሲገዙ እና የተለያዩ ግብይቶችን በቴሌብር ሲያከናውኑ በሚሰበስቡት የነጥብ መጠን መሰረት /point/ የተለያዩ የስልክ ቀፎዎችን፣ ታብሌቶች እና ላፕቶፖችን ለመግዛት፣ የሞባይል ጥቅል ለመግዛት፣ የአየር ሰዓት ለመሙላት እና ወርሃዊ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመፈጸም የሚያስችሉ ማበረታቻዎችን ለማግኘት የሚያስችላቸው ይሆናል።
በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮ ቴሌኮም የቴሌገበያ ኦንላይን ሽያጭ (online sales channel) ያስጀመረ ሲሆን፣ ይህም ኩባንያው ካሉት የራሱ 615 የሽያጭ ማዕከላት እና በአጋር ድርጅቶች በኩል ለደንበኞች አገልግሎት በሚሰጡ 116 የፍራንቻይዝ የሽያጭ ማዕከላት በተጨማሪ አገልግሎቱን በስፋት ተደራሽ እንዲሆን ታሳቢ ያደረገ እና ደንበኞች ካሉበት ቦታ ሆነው የኢትዮ ቴሌኮም ምርቶችን በቀላሉ በቴሌብር ለመግዛት የሚያስችላቸው አዲስ የሽያጭ አማራጭ ነው፡፡
በዚህ የቴሌገበያ ኦንላይን ሽያጭ የተለያዩ ዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎችን፣ የኢንተርኔት መጠቀሚያ ሞደሞችን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተርሚናሎችን እና ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶችን አቅርቧል፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ የቴሌገበያ ኦንላይን ሽያጭ አገልግሎት የአዲስ አበባ ደንበኞች ከላይ የተዘረዘሩትን የቴሌኮም ምርቶች በቴሌገበያ ድረ ገጽ https://telegebeya.ethiotelecom.et/ አማካኝነት በማዘዝ እና ክፍያውን በቴሌብር በመፈጸም የገዙት አገልግሎት በፍጥነት ባሉበት ቦታ የሚደርሳቸው ይሆናል፡፡
እንዲሁም በቅርቡ በሁለተኛው ምዕራፍ የቴሌገበያ ኦንላይን የሽያጭ አገልግሎት ተደራሽነቱን በሌሎች የሃገራችን ከተሞች በማስፋት እና ተጨማሪ የቴሌኮም መገልገያ ምርቶችን በማካተት አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ይሆናል፡፡
ሚያዚያ 19 ቀን 2014 ዓ.ም