በቴሌኮም ዘርፍ ከአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነው እና ታላቅ ሃገር እና ሕዝብ በማገልገል 130 ዓመታትን ያስቆጠረው ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ለህብረተሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ትርጉም የሚያመጡ መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በርካታ አስቻይ የዲጂታል ሶሉሽኖችን በስፋት በማስተዋወቅ እና ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰባችንን የእለት ተእለት ሕይወት በዘላቂነት ማቅለልተቋማትን አሰራር ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን የዲጂታል ኢኮኖሚውን ግንባታ በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡   በዛሬው ዕለትም ቴሌብር ከሚያስገኘው የዲጂታል ግብይት፣ የገንዘብ ማስተላለፍ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች እንዲሁም በርካታ ጠቃሚ መተግበሪያዎችን በአንድ ቦታ ከማስገኘት ባሻገር ያለምንም ተጨማሪ የኢንተርኔት ክፍያ መረጃዎችን በመለዋወጥ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ፣ የዲጂታል ክፍያዎችንም ለመፈጸም እና ገንዘብ ለማስተላለፍ የሚያስችሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ያካተተ ቴሌብር ኢንጌጅ የተሰኘ አገልግሎት እልፍ ጉዳይ በአንድ መተግበሪያ መከወን ባስቻለው ቴሌብር ሱፐርአፕ በይፋ አስጀምሯል፡፡

የቴሌብር ኢንጌጅ አገልግሎት የግለሰብም ሆኑ የቢዝነስ ደንበኞች የተናጠል ወይም የቡድን የቀጥታ ውይይቶችን (online chat) ለማድረግ፣ የግብይት መረጃዎችን ለመለዋወጥ እንዲሁም በውይይቶች ወቅት ገንዘብ ለመጠየቅ፣ ለመላክ እና ለመቀበል እንዲሁም የሞባይል ጥቅል ወይም የአየር ሰዓት ለራስ እና ለሌሎች መግዛትን ጨምሮ ሌሎች የዲጂታል አገልግሎቶችን በአንድ መተግበሪያ ላይ በማካተት በቀላሉ ለማከናወን የሚያስችል እንዲሁም የቴሌብር ሱፐርአፕን ወደቀጣይ የእድገት ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው፡፡  በተጨማሪም ቴሌብር ኢንጌጅ ደንበኞች የተለያዩ በዓላትን ወይም ማህበራዊ ሁነቶችን ተከትሎ የተናጠል ወይም የቡድን መልካም ምኞት መልእክት ከገንዘብ ስጦታ ጋር መላክ የሚያስችላቸውን አዲስ ገጽታ ያካተተ ሲሆን ለቡድን በአንድ ጊዜ የሚላከው የገንዘብ ስጦታ እንደአስፈላጊነቱ እኩል እንዲከፋፈል ወይም እድልን መሰረት በማድረግ ለቡድኑ አባላት የተለያየ የብር መጠን እንዲከፋፈል ያደርጋል።

የቴሌብር ኢንጌጅ አገልግሎት ደንበኞች የቢዝነስ ወይም ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በጽሑፍ፣ በፎቶ፣ በድምጽ (audio)፣ በቪዲዮ (video) እና በሰነድ (file) ለማጋራት የሚያስችል ሲሆን የተናጠል እና ቡድን ውይይቶችን /group chat/ ለማድረግ፣ የጓደኝነት ጥያቄ (friend request) ለመላክና ለመቀበል፣ ኪው.አር ኮድ ለመላላክ፣ ክፍያ ለመጠየቅ (request money)፣ ያሉበትን አድራሻ ለመላክ (location sharing) የሚያስችል ሲሆን ደንበኞች የሞባይል ጥቅል ወይም የአየር ሰዓት ለራስ እና ለሌሎች መግዛትን ጨምሮ በርካታ የዲጂታል አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ ለማቅረብ ያስችላል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያችን የዲጂታል ስነ-ምህዳሩን ለማስፋት ከቴሌብር ሱፐርአፕ ጋር ሲስተሞቻቸውን በማስተሳሰር (integrate) ምርትና አገልግሎታቸውን ባጠረ ጊዜ እና በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ የሚፈልጉ አጋር ድርጅቶች የሲስተም ሙከራ የሚያከናውኑበት የዴቨሎፐርስ ፖርታል አዘጋጅቶ አስጀምሯል፡፡ የዴቨሎፐርስ ፖርታሉ በዋነኛነት የአጋር ድርጅቶች ሲስተም ከዋናው ቴሌብር ሲስተም ጋር ከመተሳሰሩ በፊት በተለየ የሙከራ ቦታ ላይ (sandbox environment) የኢንተግሬሽን ቅድመፍተሻ እና የሙከራ ሥራ ለማከናወን ያስችላል፡፡ አገልግሎቱ ከሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት (build environment)፣ የሲስተም መፈተሻ (test environment) እና የትግበራ ቦታ (runtime environment) በተጨማሪ ለዴቨሎፐሮች ዶክመንቴሽኖችን፣ መመሪያዎችን፣ የቪዲዮ ቱቶሪያሎችን፣ የኮድ ናሙናዎችን (sample codes)፣ የኤፒአይ ማጣቀሻዎችን (API references) እና ሌሎች አጋዥ መርጃ መሳሪያዎችን ያካተተ ነው፡፡ የዴቨሎፐር ፖርታሉ የሶፍትዌር ዴቨሎፐሮች ከኩባንያችን ሲስተሞች ጋር በፍጥነት ለማዋሀድ፣ የትብብር ባህል ለማጎልበት፣ ክህሎት ለመጋራት፣ የዴቨሎፐሮች ኦንላይን ማህበረሰብ በመፍጠር ደረጃቸውን የጠበቁ ችግር ፈቺ እና አካታች የፈጠራ ስራ ለማፍለቅ የሚያስችል ምህዳር ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡

ኩባንያችን በቴሌብር አማካይነት በተለይ የዲጂታል የግብይት ሥርዓት ለማስፋፋት እና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ የቢዝነስ እና የመንግስት ተቋማት አሰራራቸውን ለማዘመን፣ ምርታማነታቸው እንዲጨምር እና ወጪ ቆጣቢ አሰራር እንዲተገብሩ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ጥረት በማድረግ ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት መፋጠን የበኩሉን ስኬት ማስመዝገቡ የሚታወቅ ሲሆን በቀጣይም ለደንበኞቻችን ተጨማሪ ምቾት፣ ቅልጥፍና እና ውጤታማነትን በመጨመር ተሞክሮአቸውን ወደላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩበት አዳዲስ አገልግሎቶችን ይፋ የምናደርግ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም.

ኢትዮ ቴሌኮም 

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives