ኩባንያችን ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችና ሥራ ፈጠራን ለማበረታታትና ለመደገፍ ያለመ ኢትዮቴል ኢኖቬሽን ፕሮግራም በመቅረጽ ለሀገራችን ጀማሪ የዲጂታል እና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ቢዝነሶችና ባለሙያዎች እንዲሁም በክላውድ ላይ የተመሰረተ ዲጂታል ሶሉሽን እና በሞባይል ፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ የፈጠራ ሀሳብ አመንጪዎች በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለ የፈጠራ ውድድሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በመጨረሻው ዙር የፈጠራ ውድድር የተሸጋገሩ 10 ተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን በዝርዝር አቅርበው ከኩባንያችን እና አጋሮች በተውጣጡ ዳኞች ተገምግመው ደረጃ የተሰጣቸው እንዲሁም የተለዩ ሦስት ምርጥ የፈጠራ ሀሳብ አሸናፊዎች ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ ወደ ቻይና ተጉዘው ልምድና ተሞክሮ እንዲካፈሉ ከሚያስችል ሽልማት በተጨማሪ ጨምሮ ከአንደኛ እስከ ሃያኛ ደረጃ ለወጡ ጀማሪ የፈጠራ ተወዳዳሪዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ገንዘብ፣ ላፕቶፕ፣ ዘመናዊ የስልክ ቀፎ፣ እንዲሁም ነጸ የቴሌክላውድ አገልግሎት በአጠቃላይ ከ5.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የማበረታቻ ስጦታ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ በተዘጋጀ የሽልማት መርሐ ግብር ላይ ተበርክቶላቸዋል፡፡

በዚህ የፈጠራ ውድድር አዮቴክ ሶሉሽን፣ ዊኬር እና አፍሮ ሪድ ስታርትአፕ ድርጅቶች የፈጠራ ሀሳቦች ያሸነፉ ሲሆን፣ አዮቴክ ሶሉሽን የተወዳዳረበት የፈጠራ ስራ ዘበኛ ሶሉሽን የተሽከርካሪ የደኅንነት እና የስምሪት ማስተዳደሪያ መሣሪያ፣ በጂፒኤስ መከታተያ በማንኛውም ሰዓት የነዳጅ ቁጥጥር እና የላቀ የስምሪት አስተዳደር ገጽታ ያለው፣ ለመኪና ጉዞ፣ ለራይድ እና ሎጅስቲክስ አገልግሎቶች ሁሉን በአንድ መፍትሄ የሚሰጥ ሶሉሽን ነው፡፡ በተጨማሪም ዘበኛ ሶሉሽን ተሽከርካሪን በስልክ ላይ በመከታተል እና በመቆጣጠር ደህንነትን የሚጠብቅ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው።

ዊኬር ስታርትአፕ ድርጅት የኦንላየን የምክክር አፕልኬሽን የፈጠራ ሥራ (startup idea) ያቀረበ ሲሆን፣ ታካሚዎች  የምክክር ፈቃድ ካላቸው የጤና እንክብካቤ ባለሙያዎች ጋር የሚገናኙበት፣ በአካል የመገኘትን ችግር የሚቀንስ እና የህክምና ምክሮችን ለማግኘት ምቹ የሆነ መተግበሪያ እና ድረ ገጽ የያዘ ሶሉሽን ነው፡፡

ግዙፍ ዲጅታል ያቀረበው የፈጠራ ስራ አፍሮ ሪድ የሞባይል ዲጂታል መጽሐፍ እና ኦዲዮ መጽሐፍ የፈጠራ ሥራ (startup idea) ሲሆን፣ አፕልኬሽኑ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ ተደራሽነት ለመጨመር፣ ደራሲዎች ለሀገር ውስጥም ሆነ ለዓለምአቀፍ አንባቢዎች ሥራቸው በስፋት ለተጠቃሚዎች መድረሱን በማረጋገጥ ቀላል በሆነ የዲጂታል ህትመት እና ስርጭት የደራሲዎችን ስራ ለአንባቢዎች ለማቅረብ ያስችላል፡፡

ለዚህ የፈጠራ ውድድር አመልክተው ከነበሩ 439 ተወዳዳሪዎች መካከል ብቁ ሆነው ለተገኙ 44 ተወዳዳሪዎች ጥሪ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 21 ተወዳዳሪዎች ተገኝተው ኩባንያችን ያዘጋጀውን ስልጠና ወስደዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የተሸጋገሩት 21 ተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን በዝርዝር አቅርበው በዳኞች ተገምግሞ እንደየደረጃቸው ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል፡፡ ኩባንያችን ከሽልማቶች ባሻገርም ኩባንያችን ከአሸናፊዎች ጋር በመተባበር እና ሥራዎቻቸው ላይ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ (investment) ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር፣ ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ፣ ለማስተዋወቅ እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችሉ ድጋፎችን የሚያደርግ ይሆናል፡፡

በቀጣይም ኩባንያችን መሰል ፕሮግራሞችን በመቅረጽ እና በማዘጋጀት ከዘርፉ ስነምህዳር ቁልፍ ተዋናይ አጋሮች ጋር በመተባበር ተወዳዳሪ የሆነ አገርአቀፍ አቅምን ለመገንባት፣ ፈጠራ እና ቅንጅታዊ ስራን ለማጎልበት፣ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች የተለያዩ ፋሲሊቲዎችን በማቅረብ፣ የስልጠና እና ሌሎች አቅም ማጎልበቻ ድጋፎችን በማድረግ፣ በሀገራችን የዲጂታል ስነምህዳር ዕድገት ላይ መልካም አሻራ በማሳረፍ እና የማህበረሰቡ ችግሮችን የሚቀርፉ ምርትና አገልግሎቶችን በማልማት በአህጉሪቱ የጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የስበት ማዕከል ለማድረግ በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናል፡፡

                                                 ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም

                                                       ኢትዮ ቴሌኮም