ኩባንያችን ለደንበኞች በይበልጥ ተደራሽ ለመሆን ደቡብ ደቡብ ምስራቅ የተሰኘ አዲስ ሪጅን በማቋቋም በይፋ ሥራ አስጀመረ!

ኩባንያችን መሪ የቴሌኮም እና ዲጂታል መፍትሄዎች አቅራቢ የመሆን ራዕዩን ከማሳካት በሻገር፣ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የዜጎች የኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ሶሉሽኖች የመጠቀም ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ፣ የማህበረሰባችንን ዘላቂ እድገት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ እንዲሁም የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እውን ለማድረግ አስቻይ መደላድል የሚፈጥር መጠነ ሰፊ የዲጂታል መሰረተ ልማት በማስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን ከመሰረተ ልማት ግንባታ በተጨማሪ ደንበኞችን በቅርበት በማገልገል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን በማሻሻል፣ የደንበኞችን ተሞክሮ በማሳደግ እንዲሁም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን ለመጨመር በጥናት ላይ የተመሰረተ የሪጅን አደረጃጀት ማስተካከያ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የደቡብ ምስራቅ ሪጅን ያለውን እምቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም እና የገበያ ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ ለሪጅኑም ሆነ ለሀገራችን ጉልህ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ለማምጣት አቅዷል፡፡

ቀደም ሲል የደቡብ ምስራቅ ሪጅን ጽ/ቤት መቀመጫውን አዳማ በማድረግ፣ ከቢሾፍቱ ጀምሮ እስከ ምስራቅ ባሌ ጫፍ ሰፊ መልክዓ ምድር በመሸፈን ለበርካታ ከተሞች፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎች እና ለብዙ ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን በመሰረተ ልማት ረገድ ደግሞ በርካታ የሞባይል ጣቢያዎችን፣ ግዙፍ የቴሌኮም መሰረተ ልማት እና 128 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በስሩ ይገኙ የነበረ ነው፡፡ በተጨማሪም በመሰረተ ልማት ረገድ በቅርቡ መጠነ ሰፊ የኔትዎርክ ማስፋፊያ እና የማዘመን ስራዎች መከናወን ተጨማሪ የ4G ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ ኔትወርክ ጣቢያዎች መገንባታቸው ተጨማሪ ሪጅን ለማደራጀት አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

በመሆኑም ኩባንያችን በነባሩ ሪጅን የተፈጠረውን ግዙፍ የቴሌኮም እና ዲጂታል መሰረተ ልማት አሟጦ በመጠቀም አካታችነት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አዲስ ደቡብ ደቡብ ምስራቅ የተሰኘ ሪጅን በማቋቋም በዛሬው ዕለት ሥራ ማስጀሩን ሲያበስር በታላቅ ደስታ ነው፡፡
የደቡብ ደቡብ ምስራቅ ሪጅን ጽ/ቤት መቀመጫውን ባሌ ሮቤ ከተማ ያደረገ ሲሆን 3 የአስተዳደር ዞኖችን (ባሌ ዞን፣ ምስራቅ ባሌ ዞን እና ምዕራብ አርሲ ዞን በከፊል)፣ 29 ወረዳዎችን፣ 38 ከተሞችን እና 471 የገጠር ቀበሌዎችን ያካትታል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ በተከናወኑ ሰፊ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የተዘረጉ በርካታ የሞባይልና የመደበኛ አገልግሎት ጣቢያዎች፣ ተደራሽነትን ታሳቢ ያደረጉ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት እና አስፈላጊው የሰው ኃይል የተደራጀ ነው፡፡

አዲሱ ሪጅን የሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ሰፋፊ የሰብልና የአበባ እርሻዎች፣ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ከፍተኛ የእንሰሳት ሀብት ልማት፣ በፈጣን እድገት ላይ ያሉ ከተሞች እንዲሁም የተለያዩ ውብ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገኙበት በመሆኑ አካባቢውን በቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ሶሉሽን ቴክኖሎጂዎች ማስታጠቅ ከአካባቢው ባሻገር የሀገራችንን የዲጂታል ኢኮኖሚ በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡

የደቡብ ደቡብ ምስራቅ ሪጅን ጽ/ቤት በይፋ ስራ መጀመር ኩባንያችን ደንበኞችንና ተቋማትን በቅርበት በማገልገል የላቀ ተሞክሮ እንዲኖራቸው ከማስቻል ባሻገር፣ ፈጣን አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለመስጠትና የኦፕሬሽናል ስራዎችን ለማቀላጠፍ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ጽ/ቤቱ ከአጋሮችና ከጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ጋር በመተባበር ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺና የአኗኗር ዘይቤን የሚያዘምኑ የዲጂታል መፍትሄዎችን እንዲሁም የቴሌብር አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማፋጠን ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

                                                    ሚያዚያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም.
                                                            ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives