ኩባንያችን ለሃገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እድገት አስቻይ የሆኑ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ከመገንባት እና ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የተቋማትን አሰራር የሚያዘምን የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ አስተማማኝ የቴክኖሎጂ አጋር ለመሆን እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት መጠነሰፊ ስትራቴጂያዊ ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኩባንያችን በዛሬው ዕለት የሀገራችን ቀደምት እና ታሪካዊ ከሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር መስራታቸውን በመቀጠል በተጨማሪ ዘርፎች ማለትም ለስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ስማርት ካምፓስ ሶሉሽን ለማቅረብ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ፋኩሊቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት አድርጓል፡፡ የስማርት ካምፓስ ስምምነቱ ኩባንያችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስማርት መማሪያ ክፍሎችና የተለያዩ ዘመናዊ ሶሉሽኖች ለማቅረብ በማስቻል የትምህርት ጥራትን እና አካታችነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት የትምህርት ጥራትን እና አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ የትምህርት መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት፣ የቤተ ሙከራ ፍተሻዎችን በተሻለ ተሞክሮ ለማከናወን፣ የምዘና ፈተናዎችን ለመስጠት፣ ለማረም እና ውጤቶችን ወዲያውኑ ለማሳወቅ የሚያስችል ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን (SMART CLASS ROOM) ለመገንባት ከማስቻሉ ባሻገር የስድስት ኪሎ ካምፓስ ግቢ የመግቢያ በሮች፣ ዋና ዋና የአስተዳደር ህንጻዎችን፣ ሙዚየም፣ ካፊቴሪያዎች፣ የቤተመጽሐፍት፣ የተማሪዎች እና የውጪ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ህንጻ ሰላማዊ እንቅስቃሴና ደህንነት ለመከታተል፣ብቁ ዜጋን ለማፍራት፣ በአጠቃላይ ጤናማ የሆነ የመማር ማስተማር ከባቢን ለመፍጠር እና ለማረጋገጥ የሚያስችል የሲሲቲቪ ካሜራ፣ የመቆጣጠሪያ ማዕከል እና የካምፓስ ፋይበር ኔትወርክ ዝርጋታ እና ተዛማጅ የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያካትት ከመሆኑ ባሻገር በባዮሜትሪክስ፣ ኪው.አር.ኮድ ወይም አክሰስ ካርድ የሚሰሩ የተሽከርካሪ/ፓርኪንግ እና የባለጉዳይ አክሰስ ማኔጅመንት ዲጂታል ሶሉሽኖችን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን ይህም በሀገራችን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ሁሉንአቀፍ የስማርት ካምፓስ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን እውን በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከባቢ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡

በተጨማሪም በዛሬው እለት ኩባንያችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ፋኩሊቲ የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት ያደረገ ሲሆን፣ ይህም የድንገተኛ፣ ተመላላሽ እና ቋሚ ታካሚዎች የምርመራ፣ የላቦራቶሪ፣ የፋርማሲ፣ የቀዶህክምና እና ተዛማጅ የህክምና አገልግሎት ክፍያዎችን እንዲሁም እንዳስፈላጊነቱ የቅድመ ህክምና ገንዘብ ተቀማጭ (deposit) እና የድህረ ህክምና ቀሪ ገንዘብ ተመላሽ (refund) በቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን በቀላሉ ለመከወን በማስቻል ተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም ሆስፒታሉ አሰራሩን በማዘመን አስተዳደራዊ ወጪዎች ለመቀነስ እንዲችል ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡  

ቀደምሲል ኩባንያችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተለያየ ቦታ የሚገኙ ካምፓሶቹን ከፍተኛ ፍጥነት ባለው የኢንተርኔት አገልግሎት የማስተሳሰር፣ ስማርት ክፍሎችን የመገንባት እንዲሁም የተማሪዎች ምዝገባ፣ የመግቢያ ፈተና፣ የዶክመንት ማረጋገጥ አገልግሎት፣ የሙዚየም እና ሌሎች ክፍያዎችን በቴሌብር ማከናወን፣ በቴሌኮም ኔትወርክ ኢንጂነሪንግ እና የቴሌኮም ኢንፎርሜሽን ሲስተም የሙያ መስኮች የኩባንያችንን ባለሙያዎች ማሰልጠን፣ በዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስር፣ የምርምር እና ፈጠራ ስራዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማከናወን የሚያስችሉ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር በመንግስት እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የድህረ-ምረቃ መርሐ-ግብር ትምህርታቸውን ለመከታተል ብቁ የሆኑ አመልካቾችን ለመለየት ለሚሰጠው የመግቢያ ፈተና (GAT) ምዝገባ እና ክፍያ በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር ማድረጉ የሚታወስ  ሲሆን የዛሬው ስምምነትም የዚሁ ስምምነት አካል ሆኖ በተጨማሪ ዘርፎች አብሮ ለመስራት ያስችላል።

ኩባንያችን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚያደርገውን መጠነሰፊ ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ትብብር በተለይም በትምህርት ዘርፉ ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት፣ አሰራርን ለማዘመን የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ እየተከናወኑ የሚገኙ ሁለገብ ሀገራዊ ጥረቶች ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆኑ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

 

                                                 ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

                                                       ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives