ኩባንያችን ዘመኑ የደረሰባቸውን አዳዲስ የቴሌኮም ቴክኖሎጂዎች እና የዲጂታል ሶሉሽኖች በየጊዜው በስፋት ተግባራዊ በማድረግ የልዩ ልዩ ተቋማትንና የድርጅት ደንበኞችን አሰራር ስርዓት በማዘመን፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴ በማሳለጥ እንዲሁም የዜጎችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ በማሻሻል በሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኘውን የደንበኞቻችንን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እና የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉ፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽሉ እንዲሁም ዘመኑ ያፈራቸውን አስተማማኝና ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችሉ የቴሌኮም እና ዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡

በዚህም መሰረት ኩባንያችን በዛሬው ዕለት በቴሌኮም ኢንደስትሪው ከ150 ዓመታት እንዲሁም በሀገራችንም ለ130 አመታት ለደንበኞች የባለገመድ መደበኛ ስልክና ላለፉት 20 ዓመታት ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ ያገለግል የነበረውን የኮፐር መስመር ከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት ወደሚያስችለው የፋይበር መስመር ለመቀየር የሚያስችለውን ሀገር አቀፍ ኢኒሼቲቭ በይፋ ማስጀመሩን ሲያበስር ታላቅ ደስታ ይሰመዋል፡፡

ይህ ኢኒሼቲቭ የባለገመድ የቴሌኮም አገልግሎት ደንበኞችን ከነባሩ የኮፐር መስመር የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ወደሚያስችለው የፋይበር መስመር ያለምንም ክፍያ በነጻ ለመቀየር ያስችላል፡፡ ፕሮጀክቱ በበጀት ዓመቱ በአዲስ አበባ 60ሺህ በክልል ከተሞች ደግሞ 40 ሺህ በድምሩ 100 ሺህ ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምእራፍ የ31ሺህ ደንበኞችን መስመር ለመቀየር ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የኮፐር ኔትወርክ በፋይበር በመተካት የ10,000 ደንበኞችን አገልግሎት ወደ ፋይበር ኔትወርክ ለመቀየር እቅድ ተይዟል፡፡

ነባሩ የኮፐር ኔትወርክ ቴክኖሎጂ አሁን ያለውን እና ወደፊት የሚኖረውን የብሮድባንድ ደንበኞች የፍጥነት እና ጥራት ፍላጎት የማሟላት አቅሙ ውስን ሲሆን፣ በአዲሱ የፋይበር ኔትወርክ መስመር ደንበኞች አሰራራቸውን ለማቀላጠፍ እና ለማዘመን እንዲሁም የእለት ከእለት ስራቸውን ለማቅለል የሚጠቀሙባቸው ሲስተሞች/አፕልኬሽኖች የሚፈልጉትን ከፍተኛ ፍጥነት በላቀ ሁኔታ ማሟላት ከመቻሉም ባለፈ አሁን የተዘረጋው የፋይበር ኔትወርክ ሳይቀየር የደንበኛው ፍላጎት ሲያድግ የፋይበር ሞጁል በመቀየር ብቻ አቅሙን ከ1ጂ ወደ 10ጂ ብሎም ወደ 50ጂ ለማሳደግ ያስችላል፡፡ ኩባንያችን ለዚህ መጠነ ሰፊ የመሠረተ ልማት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የመደበ ሲሆን፣ ደንበኞች ተጨማሪ ወጪ ሳያወጡ አገልግሎታቸውን ከፍተኛ አቅም ወዳለው የፋይበር ኔትወርክ የማዘዋወር ስራ ያከናውናል።

የፋይበር ኔትዎርክ በተፈለገው ፍጥነትና ጥራት አዳዲስ የቴሌኮምና ዲጂታል አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የነበሩ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት በመቅረፍ በቀጣይ የምናቀርባቸውን ፈጣን ዳታ የሚፈልጉ (Ultra-low latency) ፣ ለወሳኝ ተልዕኮ አገልግሎቶች እጅግ አስተማማኝ አገልግሎት ለማቅረብ ለአብነትም እንደ ክላውድ እና ኤጅ ኮምፒውቲንግ (cloud and edge computing) ፣ አይኦቲ (IoT)፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ ኢንተርቴይንመንት፣ የዲጂታል ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ በርካታ ስማርት ሆም (smart home) እና ሌሎችም የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡

ይህ ኢኒሼቲቭ ለባለገመድ ብሮድባንድ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ከፍተኛ ጥራት ያለው ኢንተርኔት በማቅረብ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማዘመንና ምርታማነታቸውን ለመጨመር፣ በነባሩ ኮፐር መስመር ያጋጥሙ የነበሩ የብልሽት ድግግሞሽን በመቀነስ ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት በማቅረብ ከፍተኛ ፋይዳ የሚያመጣ ከመሆኑም ባሻገር ፋይበር ለስርቆት እና አደጋ ተጋላጭ አለመሆኑ፣ ለአካባቢ ተስማሚ መሆኑ (Environmentally Friendly) እንዲሁም ቦታ (Space saving)፣ ኃይል ቆጣቢ (Energy efficiency) እና ወጪ ቆጣቢ (Cost efficiency) መሆኑ ቴክኖሎጂውን እጅግ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

ይህ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ እና በመላው ሃገሪቱ የሚተገበር ግዙፍ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ የአዲስ አበባ ኮፐር ኔትወርክን በቀጣይ 3 አመታት፣ የክልል ዋና ዋና ከተሞችን ደግሞ በቀጣይ 5 ዓመታት ከዚያም የዞን እና ወረዳ ከተሞችን ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ታቅዶ ትግበራ ተጀምሯል፡፡

ኩባንያችን በዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ኢኒሼቲቭ ግለሰቦች፣ የንግድ እና የመንግስት ተቋማትን በፈጣን እና ዘመናዊ የፋይበር ኔትወርክ በማስተሳሰር የላቀ የቴሌኮም እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን/ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን የበኩሉን ቁልፍ ሚና በብቃት ለመጫወት የሚያግዝ ግዙፍ አቅም ይፈጥራል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ በአዲስ አበባ ከተማ ኔትዎርክ የሚቀየርላቸው (Optical Access networks /ODN) አካባቢዎች በደቡብ ምዕራብ አ.አ ዞን፡ ብስራተ ገብርኤል፣ ካርል፣ መካኒሳ እና ጦር ሀይሎች፤ በማዕከላዊ አ.አ ዞን፡ መስቀል ፍላወር፤ በምዕራብ አ.አ ዞን፡ ኮልፌ፣ ሸጐሌ እና አስኮ፤ በደቡብ አ.አ ዞን፡ ቃሊቲ፣ ሳሪስ፣ አቃቂ፣ ቦሌ ቡልቡላ፣ ጎፋ፣ ጐተራ እና ቂርቆስ፤ በምስራቅ አ.አ ዞን፡ ሲ.ኤም.ሲ፣ ጃክሮስ፣ጐሮ፣ አያት፣ ጉርድ ሾላ እና ገርጂ፣ በሰሜን አ.አ ዞን፡ ሽሮ ሜዳ፣ ኮተቤ፣ ስድስት ኪሎ፣ ላምበረት፣ አራት ኪሎ እና ሾላ ገበያ ይገኙበታል፡፡

ክቡራን የባለገመድ መስመር ደንበኞቻችን፣ ለዚህ ፈጣን፣ ከፍተኛ ጥራት እና አስተማማኝ የመደበኛ የብሮድባንድ ኢንተርኔት እና ስልክ አገልግሎትን ለማቅረብ የሚያስችል ኢኒሼቲቭ ስኬታማነት ቀና ትብብራችሁ እንዳይለየን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

 

መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም