ውድ ደንበኞቻችን
የ2017 በጀት አመት እቅዳችንን ይፋ ባደረግንበት ወቅት የቴሌኮም የመሰረተ ልማት ማስፋፊያዎች የውጭ ምንዛሬ የሚፈልጉ እንደመሆናቸው በቅርቡ የተደረጉ የገንዘብ ስርአት እና የውጭ ምንዛሪ ለውጦችን ተከትሎ የምናደርገው የታሪፍ ማሻሻያ መኖሩን እንዲሁም ማሻሻያ ባናደርግ ሊኖርብን የሚችለውን ተጽዕኖ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበልን ጥያቄ በቅርቡ በተወሰኑ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የታሪፍ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ የምናደርግ መሆኑን መግለጻችን ይታወሳል።
እንደሚታወቀው ኩባንያችን ሁሉን አካታች የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚ የመገንባት ትልም ያለው በመሆኑ ላለፉት ስድስት አመታት ከ40-86% ቅናሾችን በምርትና አገልግሎቶቹ ላይ ተግባራዊ በማድረግ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ከሚገኙ ሌሎች የቴሌኮም አቅራቢዎች በድምጽ እና በዳታ አገልግሎት ዝቅተኛ ዋጋ አቅራቢነቱ ተረጋግጧል።
አሁንም የምናደርገው የታሪፍ ማሻሻያ አገልግሎቶቻችንን በቅናሽ የማቅረብ (affordability) መርህን የጠበቀ አጠቃላይ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ከምንሰራው ስራ ጋር የሚጣጣም፣ አገልግሎቶቻችንን በጥራት ለመስጠት የምናደርጋቸውን ማስፋፊያዎችና ማሻሻያዎች የሚያስቀጥል፣ የደንበኞቻችንን የመክፈል አቅም ያገናዘበ እና አካታች የቴሌኮም እና የዲጂታል ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል በሚያስችል መልኩ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የዋጋ ማሻሻያው ተግባራዊ የሚሆነውም በተወሰኑ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ ብቻ ይሆናል።
የአለም አቀፉ የቴሌኮም ዩኒየን (ITU) ሪፖርት ተንተርሰን ያደረግነው የውስጥ ትንተናም እንደሚያመለክተው ከምናደርገው የዋጋ ማሻሻያ በኋላም ኩባንያችን በአፍሪካም ሆነ በዓለም ከሚገኙ የቴሌኮም አቅራቢዎች በድምጽ እና በዳታ ዝቅተኛ ዋጋ አቅራቢ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን ያሳያል።
በመሆኑም ከመስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ማሻሻያውን በሂደት ተግባራዊ የምናደርግ ሲሆን አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል በሚጠቀምባቸው እና እጅግ ተመጣጣኝ በሆኑ 22 ጥቅሎች ላይ የዋጋ ተመጣጣኝነትን እና የዲጂታል አካታችነትን ለማረጋገጥ (to ensure affordability and digital inclusion) ምንም አይነት የዋጋ ማስተካከያ የማናደርግ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን።
ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ድረ-ገጻችንን https://www.ethiotelecom.et ይጎብኙ!
ኢትዮ ቴሌኮም