የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሀገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ ከወሰዳቸው ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች መካከል የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ሰፋ ያለ ሚና እንዲኖረው የማድረግ በተለይም የቴሌኮም እና የፋይናንስ ዘርፎች ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ የሚያስችል የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻሉ ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የካፒታል ገበያን በማቋቋም ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን እና ኢንቨስተሮችን ለመሳብ፣ ጠንካራ የካፒታል ገበያ ስርዓት እንዲኖር፣ ገበያው ፍትሃዊ፣ ግልጽ እና ደህንነቱ የተጠበቀ  እንዲሆን በማቀድ ተግባራዊ አድርጓል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ከአፍሪካ ቀደምትና ፈር ቀዳጅ የቴሌኮም ኩባንያ ሲሆን ባለፉት 130 ዓመታት የቴሌኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል አገልግሎቶችን በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግ ታላቅ ሀገርና ህዝብን በማገልገል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ማንነትን የገነባ ተቋም ነው። ኩባንያው ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ከዘመኑ ጋር አብሮ እየዘመነ ዘመን ያፈራቸውን እና ከጊዜው ጋር አብረው የሚራመዱ ቴክኖሎጂዎችን በየጊዜው ተግባራዊ በማድረግ የተቋማትን አሰራር በማዘመን፣ የዜጎችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ በማሻሻል እንዲሁም ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ የህዝብ ተቋም ነው፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ሰዓት 79 ሚሊዮን የቴሌኮም ደንበኞችን ከማፍራት ባሻገር በሀገር አቀፍ ደረጃ ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት እንዲሁም ከብዙ ዓለም አቀፍ እና ሀገር ውስጥ ድርጅቶች/ተቋማት ጋር ስትራቴጂያዊ አጋርነቶችን በመመስረትና በቴሌኮም ሥነ-ምህዳሩ በኃላፊነትና በባለቤትነት ስሜት በመስራት እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ጀማሪ ቢዝነሶችን በመደገፍ፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣትና አጠቃላይ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ባለፉት ዓመታት ኩባንያው የአገልግሎት ጥራቱን ከማሻሻል ባሻገር የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ሀገራዊ የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነት እቅዶቻችንን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሰፊ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ያደረገ ሲሆን እ.ኤ.አ ሜይ 2021 ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደረገ ፋናወጊ የቴሌብር ዲጂታል ክፍያ እና ሞባይል ገንዘብ አገልግሎት አስጀምሯል፡፡ በዚህም 50 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት በዘርፉ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ እና አማራጮችን በማቅረብ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በማፋጠን ላይ ይገኛል።

መንግስት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ባለቤትነት ድርሻን ለኢትዮጵያውያን በመሸጥ ሥራ እንደሚጀምር በገለጸው መሰረት የመደበኛ አክሲዮን ሽያጭ ለማከናወን ኩባንያው ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማኀበርነት የተቀየረ ሲሆን፣ ጁን 21 ቀን 2024 በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት በአክሲዮን ማኅበርነት ተመዝግቧል፡፡

ይህ በሀገራችን የካፒታል ገበያ የአክሲዮን ሽያጭ ፈርቀዳጅ የሆነው እና የሀገሪቱን ግዙፍ የቴሌኮም እና ዲጂታል ፋይናንሽያል አገልግሎቶች አቅራቢ ኩባንያ ለመላው ኢትዮጵያውያን የባለቤትነት ድርሻ ማቅረብ በዋናነት ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ሚና የበለጠ እንዲሰፋ ለማድረግ፣ የኩባንያውን ውጤታማነት ለማሻሻል፣ ካፒታል የሚያገኝበትን እድል ለማስፋት እና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ጥራትና ተደራሽነት ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

በዚህ የካፒታል ገበያ የመጀመሪያ ዙር ሽያጭ የኩባንያው እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸው 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት ለመሆን ፍላጎት ያለው እንዲሁም ይህን አክሲዮን ለህዝብ ለማቅረብ በተዘጋጀው እና በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በጸደቀው የደንበኛ ሳቢ መግለጫ (Prospectus) የወጡ መስፈርቶችን የሚያሟላ ማንኛውም ኢትጵያዊ ዜግነት ያለው ግለሰብ/ባለሀብት (Investor) መደበኛ አክሲዮኖችን ከዝቅተኛው ብር 9,900 ወይም 33 አክሲዮኖች ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ብር 999,900 ወይም 3,333 አክሲዮኖች መግዛት ይችላል፡፡

አንድ አክሲዮን ገዢ ባለሀብት/ግለሰብ አክሲዮን ሲገዛ ከአክስዮኑ ዋጋ በተጨማሪ 1.5% የአገልግሎት ክፍያ እና ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፍል ሲሆን ከላይ ከተጠቀሰው ከፍተኛው መጠን አክሲዮን በላይ መግዛት አይችልም፡፡

የአክሲዮን ሽያጩ ከጥቅምት 06 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እሰከ ታህሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን በአክስዮን ሽያጩ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ለሽያጩ ከማመልከታቸው በፊት ሊያሟሏቸው የሚገቡ ቅደመ-ሁኔታዎች መካከል፤ ኢትየጵያዊ ዜጋ መሆን፣ መመዝገቢያ መተግበሪያው ላይ መመዝገብና አካውንት መክፈት፤ማንነታቸውን የሚገልጽ ህጋዊ ሰነድ ማቅረብ የሚችሉ መሆን፣ የግዢውን ማመልከቻ የሚያቀርቡት ለሌላ ሰው ከሆነ መወከላቸውን የሚያረጋግጥ ህጋዊ የውክልና ማረጋገጫ ሰነድ መያዝ፤ የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንዲሁም ከማመልከታቸው በፊት በደንበኛ ሳቢ መግለጫ ሰነድ (Prospectus) ላይ የተዘርዘሩትን ስለኩባንያው የቀረቡ መግለጫዎች እና ስጋት ትንተናዎች በሚገባ ማንበብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚያም በቴሌብር ሱፐርአፕ ላይ ለአክሲዮን ግዥ የቀረበውን ማመልከቻ በጥንቃቄ መሙላት እና ክፍያውን በ48 ሰዓት ውስጥ ከፍለው ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡

የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ሰነዱን (Prospectus) ይህን ማስፈንጠሪያ  www.teleshares.ethiotelecom.et በመጫን በኩባንያችን ድረ-ገጽ ወይም በቴሌብር ሱርአፕ ላይ ማግኘት የሚቻል ሲሆን ሰነዱ ሲዘጋጅ ባጠናቀቅነው በ2016 በጀት አመት የነበረውን ኦዲት የተደረገ የፋይናንስ ሪፖርት መሰረት በማድረግ የተዘጋጀ በመሆኑ በሰነዱ ውስጥ የተጠቀሱት ቁጥሮች ሁሉ የኩባንያውን የ2016 በጀት አመት ቁመና የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

የተገዙ መደበኛ አክሲዮኖች የመሸጥ፣ የመተላለፍና ከማንኛውም መደበኛ አክሲዮን ወደ ሌላ ባለቤትነትን ማስተላለፍ የሚቻለው ኩባንያው በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ የመካተቱ ሂደት ሲጠናቀቅ ይሆናል፡፡  በተጨማሪም ኩባንያው አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው እና ሂደቱን አጠናቀው ለተመዘገቡ አክሲዮን ገዥዎች የፈለጉትን የአክሲዮን ድርሻ እንደሚያገኙ መተማመኛ አይሰጥም ማለትም የህብረተሰቡን የኩባንያው ባለቤትነት ፍትሃዊነት ለማረጋገጥና ተሳትፎውን ከፍ ለማድረግ የቀረቡትን የአክሲዮን ግዢ ጥያቄዎች የመደልደል ኃላፊነት የኩባንያው ይሆናል፡፡

የኩባንያችን አክሲዮን ሽያጭ በቴሌብር ብቻ የሚከናወን በመሆኑ፣ የቴሌብር ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎች የቴሌብር መተግበሪያን ከአፕስቶር፣ ፕሌይስቶር፣ ጋለሪአፕ በማውረድ መመዝገብ  እና አክሲዮን በመግዛት በዚህ ታሪካዊ ዕድል በመካፈል የአንጋፋው ኩባንያ የባለቤትነት ድርሻ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንጋብዛለን፡፡

ጥቅምት 06 ቀን 2017 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives