ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2013 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም ያለውን የኢትዮ ቴሌኮም የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡

የቴሌኮም መሠረተ ልማትና አገልግሎት የሀገራችንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማረጋገጥ እና ለማሳለጥ አይነተኛ የአስቻይነት ሚና ይጫወታል፡፡ ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል፣የማህበረሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ የታሪፍ ማሻሻያዎች በማድረግ፣  የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፊ የፕሮጀክትና የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት እያደገ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ ደንበኞቹን በማርካት ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነው የቴሌኮም ገበያ ብቁና ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን በትጋት እየሰራ ያለ ሀገራዊ የልማት ተቋም ነው፡፡

ኩባንያችን በሦስት ዓመቱ የእድገት ስትራቴጂ ላይ የነደፈውን የትኩረት አቅጣጫና የስትራቴጂ መስኮችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር ስትራቴጂያዊ ግቦችን በመቅረጽና ግቦችን ሊያሳኩ የሚችሉ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችና ተግባራት በማቀድ ወደ ሥራ መግባቱን ለህዝብ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ስትራቴጂካዊ ግቦችን ለማሳካት፤ የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ማሻሻልንና እርካታን ታሳቢ ያደረገ የኦፕሬሽን ልህቀት ማምጣት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ማሳደግ፣ እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል የኔትወርክ አቅም ማሳደግ፣ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ መናበብ በመፍጠር አዳዲስ አገልግሎቶች ማምጣት፣ የሀብት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የዓለም አቀፍ ቢዝነስን ማጠናከርና ገበያው በሚጠይቀው መሠረት አዳዲስ አሰራሮችን መከተል፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን በተለያዩ ስልቶች መከላከል እንዲሁም የተቋም ደህንነትን ማረጋገጥ ዋና ተግባራት በማድረግ እና የተጋረጡ ዘርፈብዙ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በበጀት ዓመቱ ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል፤ ጉልህ ውጤቶችም አስመዝግቧል፡፡

ኩባንያችን በበጀት አመቱ 61.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 87.6 % አሳክቷል፡፡ ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር 8.5% እድገት ያለው ሲሆን በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት 3,473 የሞባይል ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ከታቀደው የገቢ እቅድ አኳያ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የጸጥታ ችግሩን በወቅቱ መቅረፍ ቢቻልና አገልግሎቱን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል መስጠት ቢቻል ኖሮ ግቡን ሙሉ በሙሉ ማሳካት የሚቻል እንደነበር ያሳያል፡፡ ሆኖም ካሉት ተግዳሮቶች አንጻር የተመዘገበው የገቢ አፈጻጸም እጅግ አበረታች ሲሆን ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው የደንበኞች የቴሌኮም አጠቃቀምን ለማሳደግና ተሞክሯቸውን ለማሻሻል የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 67 አዳዲስ እና 77 ነባር የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች ለማቅረብ በመንቀሳቀሱ ነው፡፡

የተገኘው የገቢ ድርሻ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 51% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 27%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 10%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 5.7% እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 6.6% ድርሻ አላቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 146.6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 82.3% ያሳካ ነው፡፡

ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ የገቢ አማራጮችን ለማስፋት ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት በተጨማሪ ወጪን በአግባቡ የመጠቀም እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስወገድ እና በአጠቃላይ ኩባንያውን ውጤታማና ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል የወጪ መቆጠብ ስትራቴጂ (DO2SAVE & cost optimization strategy) በመቅረጽና ተግባራዊ በማድረግ 5.4 ቢሊዮን ብር ወጪ በመቀነስ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት የተቻለበት ነው፡፡

የአገልግሎታችን ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 66.59 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን የበጀት አመቱ አፈፃፀም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር 18.4% እድገት እንዲሁም ከእቅድ አንጻር 104% አፈጻጸም አስመዝግቧል፡፡ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 64.5 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ (Fixed Broadband) 506.8 ሺህ ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 885.3 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 26.1 ሚሊዮን ናቸው፡፡

ኩባንያችን የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይን ዕውን ለማድረግ ባለው ቁርጠኝነት የቴሌኮም አገልግሎቶችን የማዘመንና የማሻሻል ጥረቱ ቀጣይ እርምጃ የሆነውን የ5G የሞባይል ቴክኖሎጂ የሙከራ አገልግሎትን በአዲስ አበባ ከተማ በስድስት ጣቢያዎች አስጀምሯል፡፡ በተጨማሪም የኩባንያችን መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና በማጠናከር የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማከራየት ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት እና የአገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አጠቃላይ 217 የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ ሲሆን የ4G/LTE እና 4G/LTE Advanced ማስፋፊያዎች፣ የሞባይል ጣቢያዎች ማስፋፊያ፣ ስማርት ፖሎች ተከላ ፣የሞባይል መኒ ሲሰተም ማስፋፊያ በዋናነት የሚጠቀሱና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቀጣይ ትውልድ የቢዝነስ ሰፖርት ሲስተምን (Next Generation Business Support System (NGBSS)) የማዘመን እና የማሳደግ ስራዎች በመስራት ከደንበኞች ምዝገባ ጀምሮ የቢሊንግና አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

 

የሀገራችንን የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ የሚያስችለው የቴሌብር አገልግሎት ከኢንዱስትሪው ልምድ በተለየ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ 21.8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የግብይት መጠኑም (Transaction Value) 30.3 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቅሷል፡፡ የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያችን አጋሮችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እስካሁን ድረስ 353 የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ ማዕከሎች፣ 93 ማስተር ኤጀንቶች፣ ከ76 ሺህ በላይ ኤጀንቶችና ከ21 ሺህ 600 በላይ ነጋዴዎች /Merchants/ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ከ13 ባንኮች ጋር የኢንቴግሬሽን ሥራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከ11 ባንኮች ጋር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር እንዲቻል ተደርጓል፡፡ የቴሌብር ሃዋላ አገልግሎት በማስጀመርና ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ጋር በማገናኘት በ37 ሀገራት የሚገኙ ዜጎች በቀላሉ ወደ ሀገርቤት ገንዘብ ማስተላለፍ የሚችሉበት አማራጭ የተፈጠረላቸው ሲሆን ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 974.3 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለመቀበል ተችሏል፡፡ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በቴሌብር እየተሰጠ ሲሆን ከበርካታ የመንግስትና የግል አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር የኢንቴግሬሽን ሥረ በመሥራት ሰፊ የኢኮሲስተም የማስፋት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ለሁለንተናዊ ሀገራዊ እድገት ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለመንግስት በተለያየ መልክ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገባ ተቋም እንደመሆኑ በበጀት ዓመቱ ወር 18.8 ቢሊዮን ብር ታክስና 500 ሚሊዮን ብር ዲቪደንድ ገቢ በማድረግ የሚጠበቅበትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽዖ ለመወጣት ችሏል፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ከፍተኛ ግብር በመክፈል በተከታታይ የፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ሊሆን ችሏል፡፡

ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከ 360 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የገቢ እንዲሁም የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ የተፈጠረው የስራና የገቢ ዕድል የኢትዮ ቴሌኮምን ምርትና አገልግሎት ለደንበኞች በማዳረስ (ዋና አከፋፋዮች፣ ንዑስ አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎች፣ ይሙሉና ካርድ አከፋፋዮች፣ ኢቪዲ አከፋፋዮች)፣ በመስመር ዝርጋታ፣ በመሳሰሉት የሙያ ዘርፍ ነው፡፡ የአገልግሎት ተደራሽነት ከማረጋገጥ አኳያ የሽያጭ ማዕከላት ከማሳደግና አጋሮችን ከማፍራት በተጨማሪ ዲጅታል ተደረሽነትን እውን ለማድረግ ሰፊ ጥረቶች የተከናወኑበት እንዲሁም ደንበኞችን የበለጠ ለመቅረብ ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ አሰራሮችን በመተግበር የሜትር ታክሲዎችም በቴሌኮም ምርትና አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን ለደንበኞቹ ከሚሰጠው የቴሌኮም አገልግሎት በተጨማሪ ለማህበረሰባችን ፋይዳ ባላቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰራ ይታወቃል፡፡ በዚህ በጀት ዓመትም በአይነት፣ በአገልግሎትና በገንዘብ በድምሩ 422.6 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ በመላው ሃገራችን በትምህርት፣ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ ላይ ተሳትፏል፡፡ ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች 16.5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

የኩባንያችንን የማስፈፀምና የመፈጸም አቅምን በማጎልበት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ ተከታታይነት ያለው ስልጠና በአካል ከ15ሺህ በላይ እና በዲጂታል አማራጭ ከ20 ሺህ በላይ ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የሠራተኛውን ተነሳሽነትና የባለቤትነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል ሠራተኞችን በተቋሙ ስትራቴጂ ዝግጅትና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ግብዓት እንዲሰጡ የማድረግ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሻሻል፣ የሥራ ከባቢን አመቺና ደህነንቱን የማረጋገጥ እንዲሁም የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመተግበር የተሻለ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን በበጀት አመቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ በኔትዎርክ ሀብት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ ቴሌኮም ማጭበርበር፣ የኮረና ወረርሽኝ በተቋም ንብረት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ የገበያ አለመረጋጋት እንዲሁም የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበው አበረታች አፈጻጸም ለበለጠ ስኬት የሚያነሳሳ ሲሆን በተለይም በወቅቱ ከነበሩ ተግዳሮቶች እና የቴሌኮም አገልግሎትን ለመስጠትና ለማስፋፋት ካለው ፈታኝ ሁኔታ አንጻር አፈጻጸሙን እጅግ አመርቂ ያደርገዋል፡፡ ይህ ውጤት የተመዘገበው የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ከኩባንያው አመራር ጋር በመናበብና በመደጋገፍ እንዲሁም የኩባንያችን አመራርና ሠራተኞች የኩባንያችንን ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥና ተመራጭ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ እንዲሆን ለማድረግ ካላቸው ህልም፣ ለውጤታማነቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአግባቡ በመወጣት ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረትና ሰፊ ርብርብ ነው፡፡

ባጠቃላይ ኩባንያችን ላስመዘገበው አበረታች ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ ደንበኞቻችን፣ የኩባንያችን የስራ አጋሮች፤ የምርትና አገልግሎቶቻችን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮቻችን እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡

                                 ሐምሌ 21 ቀን 2014 .

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives