የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ኢትዮ ቴሌኮም የ 100 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን ተግባራዊ አደረገ

ኩባንያችን የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ በአገራችን ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ያለውን የቴክኖሎጂ አቅም በመጠቀም በአገር አቀፍ ደረጃ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና በመጫወት ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ከዚሁ አንፃር ኩባንያችን ህብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ እንዲኖረው እና ያለመዘናጋት እራሱን ከቫይረሱ አንዲጠብቅ ሰፊና ተደራሽ የሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በተከታታይ በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን ለአብነት ያህልም በመላው አገሪቱ የሚገኙ  የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች ጥሪ በሚደርጉበት ጊዜ ጥሪያቸው ከመነሳቱ በፊት የተቀረፀ የድምፅ መልዕክት እንዲያደምጡ በማድረግ፤ በ444 አጭር ቁጥር እንዲሁም በቀን ከአራት መቶ ሺህ በላይ ደንበኞች በሚስተናገዱበት 994 ነፃ የጥሪ ማዕከል አማካኝነት በአማርኛ፣ በኦሮምኛ ፣ በሶማልኛ ፣ በትግሪኛ እና በአፋርኛ ቋንቋዎች የተቀረፁ የድምፅ መልዕክቶችን በማስደመጥ፤ ለሞባይል ደንበኞች የድምፅ እና የፅሁፍ መልዕክቶችን በመላክ፤ አንዲሁም በማህበራዊ ትስስር ገፆች እና ሰፊ ተመልካች ባላቸው የተቋሙ የአደባባይ እስክሪኖች ስለቫይረሱ ጠቃሚ መረጃ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያችን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ የሚገኙትን የ8335 እና 952 አጭር ቁጥሮችን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በነፃ ያቀረበ ከመሆኑም በተጨማሪ የጤና ሚኒሰቴር የህክምና ባለሞያዎች የሚጠቀሙበትንና 1,500 የሚደርሱ ያልተገደበ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎቶች ላይ የ50% ቅናሽ አድርጓል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቫይረሱን ሰርጭት ለመከላከል እንዲረዳ  በአገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ መቋቋሙን ተከትሎ መጋቢት  16 ቀን 2012 ክቡር የኢፌዲሪ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) ባቀረቡት ጥሪ መሠረት  ህብረተሰቡ በቀላሉ ድጋፍ ማድረግ እንዲችል  ኩባንያችን በ444  አጭር ቁጥር አማካኝነት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ያዘጋጀ ሲሆን እስካሁን 3,752,405  ብር እንዲሁም  ውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆችም ካሉበት ቦታ ሆነው ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ በ ethioremit.com አማካኝነት  የድጋፍ ማሰባቢያ አሰራር የዘረጋ ሲሆን እስካሁን 676,929 ብር በድምሩ 4,429,334  ተሰብስቧል፡፡  ኩባንያችንም በዛሬው ዕለት የ100 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል ፡፡

የኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በአገራችን በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎት ፍላጎት መጨመርን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ኩባንያችን አስቀድሞ የተለያዩ ጥናቶችን ሲያደርግ የነበረ ከመሆኑም በተጨማሪ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ደንበኞቻችንም የኢንተርኔት አገልግሎት አጠቃቀማቸው መጨመርን ተከትሎ ለአገልግሎቱ የሚያወጡት የገንዘብ መጠን መጨመሩን በመግለፅ ኩባንያችን ማሻሻያዎችን እንዲያደርግላቸው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ ፡፡

በመሆኑም  የክቡራን ደንበኞቻችን ፍላጎት ለማርካት እና መንግስት ዜጎች እንቅስቃሴያቸውን በመገደብ እና በቤታቸው እንዲቆዩ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ  እያደረገ ያለውን ጥረት ከመደገፍ  አንፃር በአገልግሎት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅኖ በማይፈጥር መልኩ ኩባንያችን  አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ አቅርቧል፡፡

በዚህ መሠረት ኩባንያችን ከሚያዚያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ጀመሮ ለሁለት ወር የሚቆይ ‘’በቤትዎ ይቆዩ’’ የሞባይል ጥቅል አገልግሎት (Stay @ Home Mobile Package Service) ፤ የተለያዩ ድረ-ገፆችን በነፃ መጎብኘት የሚያስችል አገልግሎት (Stay Connected Service) ፤ እንዲሁም የቅድመ ክፍያ ሞባይል አየር ሰዓት የቆይታ ጊዜን የሚያራዝም አገልግሎት (Stay Active Service ) ተግባራዊ አድርጓል፡፡

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives