ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2015 እስከ ታህሳስ 2016 በጀት ዓመት ያለውን የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡

ኩባንያችን በሀገራችን ኢኮኖሚና የማህበረሰባችንን ሁለንተናዊ እድገት እንዲሁም በዜጎች ኑሮ መሻሻል ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደመሆኑ ፈጣንና ተለዋዋጭ ከሆነው የቢዝነስ ፍላጎት ጋር በማጣጣም ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እየሰራ ሲሆን በዚህም የቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል እንዲሁም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፈ-ብዙ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ እና ማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ኩባንያችን በውድድር ገበያው ውስጥ ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም በመሆን በሁሉም መስክ የመሪነት ሚና መጫወት የሚያስችል የሦስት ዓመት መሪ የእድገት ስትራቴጂ ቀርፆ በመተግበር አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ይህ በጀት ዓመት የስትራቴጂ ዘመኑ አጋማሽ ሲሆን በመጀመሪያው መንፈቅ በአጠቃላይ ስትራቴጂካዊ ግቦቹን ከማሳካት፤ የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ከማሻሻልና እርካታን ታሳቢ ያደረገ የኦፕሬሽን ልህቀት ከማምጣት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ከማሳደግ፣ እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል የኔትወርክ አቅምን ከማሳደግ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችና አገልግሎቶችን ከማስፋት፣ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ መናበብ በመፍጠር አዳዲስ አገልግሎቶች ከማምጣት፣ የሀብት አጠቃቀምን ከማሻሻል አንጻር ሰፊ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በተጨማሪም የፋይናንስ አካታችነትን ከማረጋገጥ፣ አዳዲስ አገልግሎቶችና አመቺ አሰራሮችን ከማምጣትና ተቋማት የዲጂታል ክፍያ አማራጭን እንዲጠቀሙ ከማድረግ፣ የመንግስትና የኢንተርፕራይዝ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ከመደገፍና ትብብርን ከማጠናከር፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን በተለያዩ ስልቶች ከመከላከል እንዲሁም የተቋምን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

 

የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብዛት

በመንፈቅ አመቱ አጠቃላይ የደንበኞቻችን ብዛት 74.6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር በ4.7 ሚሊዮን ወይም የ6.7% እድገት እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ98.3% ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 71.7 ሚሊዮን፣ የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 36.4 ሚሊዮን ፣ የመደበኛ ብሮድባንድ 688.3 ሺህ እንዲሁም የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 834 ሺህ ናቸው፡፡ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 68.5% ማድረስ ተችሏል፡፡

ምርትና አገልግሎቶችን የማስፋት እንዲሁም የኔትወርክ አቅምና ሽፋንን የማሳደግ ስራዎች

የደንበኞችን ቁጥር ለማሳደግ የተቻለው፣ ተሞክሯቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ተደራሽነትን ለማስፋት፤ ተጨማሪ የሞባይልና የመደበኛ ኔትዎርክ ማስፋፊያ ሥራዎች በመሰራታቸው፣ ተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትና የምርትና አገልግሎት አጋሮች በማካተት አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ በመቅረባቸው፣ የ5ጂ አገልግሎት በአዲስ አበባና በተወሰኑ የክልል ከተሞች እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 114 (64 አዳዲስ እና 50 ነባር) የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች በመቅረባቸው ነው፡፡

የአገልግሎት ጥራትን እንዲሁም የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ከማሳደግ አንጻር የኔትወርክ ማስፋፊያ የፕሮጀክት ሥራዎች በመከናወን ላይ ሲሆኑ ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical)፣ በተመሳሳይ ወቅት (real time) መከናወን ለሚያስፈልጋቸው አገልግሎቶች እና internet of things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችለውን 5G የሞባይል ቴክኖሎጂ አገልግሎት በተወሰኑ ከተሞች ለገበያ ቀርቧል፡፡ በግማሽ ዓመቱ በተደረገ የኔትወርክ ማስፋፊያ በ3G 678.2 ሺህ፣ በ4G 1.1 ሚሊየን እና በ5G 148.2 ሺህ በድምሩ 1.9 ሚሊየን ተጨማሪ ደንበኛ የሚያስተናግድ አቅም የተፈጠረ ሲሆን በዚህም አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ደንበኛ ማስተናገድ አቅሙን 81 ሚሊየን ለማድረስ ተችሏል፡፡

የገጠር ቀበሌዎችን የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ አንጻር የተሰሩ ስራዎች

በመንፈቅ አመቱ ከተሰሩ የሞባይል ማስፋፊያዎች መካከል ለገጠር ቀበሌዎች የሚውል በ10 ክልሎች፣ ለ41 ወረዳዎች፣ 229 ሺህ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችሉ 41 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተተክለው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ በተጨማሪም በገጠር አካባቢ ባሉ 92 ነባር ጣቢያዎች ላይ የ3G ማስፋፊያ ስራዎች ተከናውነው አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

የገቢ አፈጻጸም

ኩባንያችን የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት፣ ቀጣይነት ያለው የደንበኞቹን አቅም ያገናዘበ አዳዲስና የተሻሻሉ ምርትና አገልግሎቶችን በማቅረብ እንዲሁም የተለያዩ የሞባይል ፋይናንስ እና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ በመንፈቅ ዓመቱ 42.86 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 98% ያሳካ ሲሆን ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በብር 8.86 ቢሊዮን ወይም የ26% ብልጫ አለው፡፡ የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 41.8% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 25.7%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 9.3%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች የ8.7%፣ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሳሪያዎች ሽያጭ 5%፣ ቴሌብር 2.5% የመሰረተ ልማት ኪራይ 1.1%፣ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 5.9% ድርሻ አላቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 84.7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም የእቅዱን 109% ያሳካ ነው፡፡

የገቢ እድገቱ የተመዘገበው፣ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ቁጥር እና የደንበኞች አጠቃቀም በመጨመሩ፣ 5Gን ጨምሮ አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶች ለገበያ በመቅረባቸው፣ እንዲሁም በነባር ምርት እና አገልግሎት ላይ ማሻሻያ በመደረጉ በሁሉም አገልግሎቶች ላይ የተስተናገደው የትራፊክ ፍሰት መጠን እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን የትራፊክ ፍሰት እድገቱ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የድምፅ ትራፊክ የ33.6%፣ ሞባይል ዳታ የ53.8%፣ አጭር የፅሁፍ መልእክት የ77.4% እና ዓለም አቀፍ ትራፊክ 30.1% እድገት አሳይቷል፡፡

ወጪን በአግባቡ ከመጠቀም እና ኩባንያውን ውጤታማና ምርታማ ከማድረግ አንጻር የወጪ ቁጠባ ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተተገበሩ ሲሆን በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የወጭ ቁጠባ በማድረግ የዕቅዱን 113% ማሳካት ችሏል፡፡ ይህም ኩባንያችን ትርፋማ እንዲሆን ለምናደርገው የጋራ ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ ነው፡፡

በኩባንያችን በውስጥ የፋይናንስ ሪፖርት አሰራር መሰረት (በውጪ ኦዲት ያልተመረመረ ሂሳብ ሪፖርት) የመጀመሪያ መንፈቅ አመት የፋይናንስ አፈጻጸም፣ ገቢን በማሳደግና ወጪ ቆጣቢ አሰራርና ባህልን በማሳደግ ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሠረት ያልተጣራ ትርፍ (EBITDA) 19.77 ቢሊዮን ብር ወይም ያልተጣራ ትርፍ መጠንን 46% በማስመዝገብ የእቅዱን 137% ማሳካት ችሏል፡፡ የተጣራ ትርፍ በተመለከተ በግማሽ ዓመቱ 11 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ የተመዘገበ ሲሆን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14% እድገት ሲኖረው የትርፋማነት መጠኑንም ወደ 26% ያደርሰዋል፡፡ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት እንዲሁም ከተያዘው እቅድ አንጻር የላቀ አፈጻጸም ያለው ሲሆን ወጭ ቆጣቢ አሰራርና ባህል ለማስረጽ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ያሳያል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 18.5 ቢሊዮን ብር ታክስ፣ 2.46 ቢሊዮን ብር (43.4 ሚሊዮን ዶላር) ብድር እንዲሁም የመንግስት የትርፍ ድርሻ ክፍያ (ዲቪደንድ) 4 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተከናውኗል፡፡ ኩባንያችን ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ተቋም እንደመሆኑ በተለያዩ ጊዚያት ዕውቅናና ሽልማት ሲሰጠው ቆይቷል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ሀገር ውስጥ ካሉ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች 21.9 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ግብር በመክፈል በገቢዎች ሚኒስትር መርሃ-ግብር ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በአንደኛነት የፕላቲኒየም ደረጃ ሽልማት አግኝቷል፡፡

ኩባንያችን የፋይናንስ ግልፅነትን ለማስፈን እና በተቆጣጣሪ አካላት የወጣውን ደንብ እና መመሪያ ለመተግበር የፋይናንስ ኦዲትን በወቅቱ እያስደረገ የመጣ ሲሆን የፋይናንስ ሪፖርቱን በዓለማቀፍ የሪፖርት አቀራረብ ስርአት (IFRS) እያወጣ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት የ2015 በጀት ዓመት የሂሳብ ሪፖርት በውጪ ኦዲተሮች ተመርምሮ ከትችት የፀዳ ወይም እንከንየለሽ (Unqualified) መሆኑ ተረገግጧል፡፡ በተጨማሪም የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ሂሳብ ኦዲት ተደርጎ የተጠናቀቀ ሲሆን የሁለተኛ ሩብ ዓመት ሂሳብ ኦዲት የማስደረግ ሥራ ተጀምሯል፡፡

ቴሌብር እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት አፈጻጸም

የቴሌብር አገልግሎት 41 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት የዕቅዱን 104% ያሳካ ሲሆን፣የግብይት መጠኑ (Transaction Value) 910.7 ቢሊዮን ብር በማድረስ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ የቴሌብር አገልግሎት ከተጀመረ ጀምሮ አጠቃላይ የግብይት መጠን 1.7 ትሪሊየን ብር በኢኮኖሚው ላይ እያንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡  ቴሌብር በሀገራችን የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ እና የፋይናንስ አካታችነትን ከማረጋገጥ አኳያ እያበረከተ ላለው ጉልህ ሚና በምርጥ የሞባይል ገንዘብ አቅርቦት ዘርፍ በ2023 እ.ኤ.አ የፊውቸር ዲጂታል እውቅና ሰጪ ተቋም የወርቅ ደረጃ አሸናፊ ሆኖ ተመርጧል፡፡

ቴሌብር አገልግሎት ለማህበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የቁጠባ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ከዳሸን ባንክ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ኩባንያችን ቴሌብር ሳንዱቅ፣ ቴሌብር እንደኪሴ፣ ቴሌብር መላ፣ ቴሌብር ስንቅ፣ ቴሌብር እንደራስ እና ቴሌብር አድራሽ የተሰኙ የቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ ያቀረበ ሲሆን እስካሁን 3.8 ሚሊየን ደንበኞች 8.3 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ያገኙ ሲሆን 1.5 ሚሊየን ደንበኞች ደግሞ 8.4 ቢሊዮን ብር መቆጠብ ችለዋል፡፡

የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያችን አጋሮችን በቁጥር ለማሳደግና ቴሌብርን ተጠቅመው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል በርካታ ስራዎች በመስራት 889 የሽያጭ ማዕከሎች፣ 148 ማስተር ኤጀንቶች፣ ከ145.9ሺህ በላይ ኤጀንቶችና ከ143.6 ሺህ በላይ ነጋዴዎች /Merchants/ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ከ25 ባንኮች ጋር የኢንቴግሬሽን ሥራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር እንዲቻል ተደርጓል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ከዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ ጋር በተያያዘ 602 መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የአገልግሎት የክፍያ ስርዓታቸውን ከቴሌብር ጋር እንዲያስተሳስሩ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ቢሮ፣ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ፤ የብሄራዊ ሎቶሪ፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ነዳጅ የግብይት ሰንሰለቱን ዲጂታላይዝ አድርጓል፡፡

ከባንክ ወደ ዋሌት እና ከዋሌት ወደ ባንክ ገንዘብ የማስተላለፍ አጋርነትን በማስፋት ለደንበኞች የገንዘብ ልውውጦች ምቹ ሁኔታዎችን ከማሳደግ በተጨማሪ የፍጆታ ክፍያ አገልግሎቶችን፣ ማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶችን እና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞች በማቅረብ ተደራሽነቱን የበለጠ በማሳደግ እና የደንበኞቹን ፍላጎት በማሟላት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በወር በአማካይ 1.13 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞችን መመዝገብ ችሏል፡፡

የሰው ኃይል የተቋም አቅም ግንባታ ስራዎችና ምቹ የስራ ከባቢን የመፍጠር ስራዎች

የኩባንያችንን የማስፈፀምና የመፈጸም አቅምን በማጎልበት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ ተከታታይነት ያለው ስልጠና በአካል ከ 6.2 ሺህ በላይ እና በዲጂታል አማራጭ ከ15,100 በላይ ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የሠራተኛውን ተነሳሽነትና የባለቤትነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል ሠራተኞችን በተቋሙ ስትራቴጂ ዝግጅትና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ግብዓት እንዲሰጡ የማድረግ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሻሻል፣ የሥራ ከባቢን አመቺና ደህነንቱን የማረጋገጥ እንዲሁም የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመተግበር የተሻለ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

የሠራተኞች ትጋት ለኩባንያው ተወዳዳሪነትና ስኬታማነት ወሳኝ እንደመሆኑ የሠራተኞችን የሥራ ላይ ተሳትፎ ወይም ትጋት የዳሰሳ ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ልምድ ባለው McLean & Company በተባለ የጥናት ድርጅት ተካሂዷል፡፡ በተገኙት የጥናት ወጤቶች ላይ ተጨማሪ ምልከታ በማድረግ የማሻሻያ እርምጃዎች የሚወሰዱ ይሆናል፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የተሰሩ ስራዎች

ኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው ተግባር የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ልማት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢያዊ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ በዓይነት እና በገንዘብ በድምሩ 449.6 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ የተደረገ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ለትምህርት ፣ለጤና፣ ለሰብአዊ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ እና ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲካሄድ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያለው ሲሆን በዚህም መሰረት ባለፉት አመታት ሰራተኞችን በማሳተፍ በበርካታ ጣቢያዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡ ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች 5.2 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

በበጀት አመቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች

ኩባንያችን በግማሽ ዓመቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ በኔትዎርክ ሀብት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ ቴሌኮም ማጭበርበር፣ የግንባታ ስራ ግብአቶች እጥረት፣ የገበያ አለመረጋጋት፣ የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

ኩባንያችን በግማሽ ዓመቱ ያስመዘገበው ከፍተኛ አፈጻጸም አበረታችና ለበለጠ ጥረትና ስኬት የሚያነሳሳ ሲሆን በተለይም ውጤቱ የተመዘገበው ኩባንያችን በውደድር ገበያ ውስጥ ሆኖ መሆኑ አፈጻጸሙን እጅግ አመርቂ ያደርገዋል፡፡

በአጠቃላይ ኩባንያችን ላስመዘገበው አበረታች ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ ደንበኞቻችን፣ የኩባንያችን የስራ አጋሮች፤ የምርትና አገልግሎቶቻችን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮቻችን እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችን ይድረሳችሁ፡፡

ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives