የኢትዮ ቴሌኮም የ2011 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም

ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2ዐ10 እስከ ሰኔ 2ዐ11 ያለውን የኢትዮ ቴሌኮም የአንድ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡

የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱ በተቋሙ አመራርና በሥራ አመራር ቦርድ የተገመገመና የጸደቀ ሲሆን የሥራ አፈጻጸም ግምገማው የተቋሙን የለውጥ ስራዎች እና የሥራ አፈፃፀም ከተቀመጠው አመታዊ እቅድ፣ ከባለፈው የበጀት ዓመት እና ከቴሌኮም ኢንዱስትሪ እድገትና ተሞክሮዎች አንፃር የተከናወነ ነው፡፡ በስራ አፈፃፀም ግምገማው የኩባንያው ጠንካራ ጎኖች፣ ውስንነቶች፣ ክፍተቶች እና ተግዳሮቶችን በመለየት እና በመወያየት የተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲሁም የመፍትሔ ሐሳቦች ተቀምጠዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮ በጀት ዓመት በአማካይ ከ40 እስከ 50 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ በማድረግ 36.3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን የእቅዱን 85 በመቶ አፈጻጸም እንዲሁም ካለፈው በጀት ዓመት አንፃር የ7 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ተቋሙ ያልተጣራ ትርፍ 24.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከታቀደው የ79 በመቶ አፈጻጸም እንዲሁም ካለፈው በጀት ዓመት የ5.6 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ 16.2 ቢሊዮን ብር ግብር የከፈለ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 4.7 ቢሊዮን ብር በቀደሙት ዓመታት ያልተከፈለ የግብር ክፍያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከአምናው አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ4ዐ በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ይህ የግብር መጠን በሃገራችን ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች በዘንድሮ ዓመት ከተሰበሰበው 85.9 ቢሊዮን ብር የ18.8 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በዘንድሮ ዓመት 7 ቢሊዮን ብር ዲቪደንድ የከፈለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1 ቢሊዮን ብር ቀድሞ የተከፈለ ዲቪደንድ ነው፡፡

የበጀት አመቱ አንዱ ስኬት የሆነው ባለፉት ሶስት ዓመታት ሳይከፈል የቆየ ብድር መክፈል መቻሉ ሲሆን በዚህ በጀት ዓመት 9.9 ቢሊዮን ብር ወይም 362 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት 43.6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከእቅዱ አንፃር የ95 በመቶ አፈፃፀም እና ከባለፈው የበጀት ዓመት የ15 በመቶ እድገት ያለው ሲሆን አጠቃላይ የቴሌኮም ስርጸት (tele density) መጠኑ 44.5 በመቶ ደርሷል፡፡ ከዚህም ውስጥ ሞባይል ድምፅ 41.92 ሚሊዮን፣ የዳታ እና የኢንተርኔት ተጠቃሚ 22.3 ሚሊዮን፣ እንዲሁም መደበኛ ስልክ 1.2 ሚሊዮን ደንበኞች ናቸው፡፡

በበጀት ዓመቱ 19 አዲስ እና 23 የተሻሻሉ የሃገር ውስጥ ምርት እና አገልግሎቶች የቀረቡ ሲሆን፤ 4 አዲስ እና 13 የተሻሻሉ አለም ዓቀፍ ምርት እና አገልግሎቶችም ለገበያ ቀርበዋል፡፡

የደንበኞችን የመግዛት አቅም በማገናዘብ የቴሌኮም አገልግሎትን አጠቃቀም ለማሻሻል እንዲሁም የደንበኞችን እርካታን ለመጨመር ያለመ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ በሁሉም ምርትና አገልግሎቶች ላይ ተደርጓል፡፡ በዚህም የታሪፍ ቅናሽ 19 በመቶ የድምፅ ትራፊክ እና 13ዐ በመቶ የዳታ ትራፊክ እድገት ተመዝግቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተከታታይ ሲቀንስ የነበረው የአለም ዓቀፍ ጥሪ የመቀነስ አዝማሚያውን ለመቀልበስ በበጀት ዓመቱ በተወሰዱ የቴክኒክና የቢዝነስ አማራጭ መፍትሔዎች ውጤታማ ሥራ ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው የትራፊክ መጠን የ5ዐ በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሹን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረውን ትራፊክ ማስተናገድ የተቻለው በመጠነኛ የኔትዎርክ አቅም በማሳደግ፣ ኔትዎርኩን በማትባት እና ሃብትን አዟዙሮ በመጠቀም ነው፡፡

የበጀት ዓመቱ የጀመረው የኩባንያውን የተለያዩ የስራ ክፍሎች ጠንካራ፣ ደካማ፣ ምቹ ሁኔታዎች እና ፈታኝ ጉዳዮችን በመለየት ሲሆን እነዚህን ጉዳዮች ከለየ በኋላ የኩባንያው አመራር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ጉዳዩች በመለየት የዓመቱን እቅዶች ለማሳካት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ የበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ግምገማ በተቋሙ ለተወሰዱ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎች እንደ መሰረት እና ግብዓትነት አገልግሏል፡፡

የአመራር እና የሰራተኛ አቅም ግንባታ የሰው ሐብት አስተዳደር፣ የአደረጃጀት ለውጥ፣ ከአጋር ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል፣ የስራ ከባቢን ማሻሻል፣ የንብረት አስተዳደር እና የሃብት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የስራ አፈፃፀምን እና የማኔጅመንት ስትራቴጂን የማስፈፀም ብቃት ከተቋሙ የለውጥ ሥራዎች መካከል ተጠቃሾቸ ናቸው፡፡

የአመራሩ የውሣኔ ሰጭነት ሚና ማሳደግ እና ኃላፊነት መውሰድ ለዚህም እንዲረዳ አመራሮች የተለያየ ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ፣ የምክር እና እውቀት ማካፈል ብሎም አመራሩ የቢዝነስ እይታ እንዲኖረው በማድረግ የተቋሙ ማኔጅመንት እና ሠራተኛ ለሚመጣው የቴሌኮም ገበያ ውድድር እንዲዘጋጅ የተወዳዳሪነት አቅሙ እንዲጎለብትና ዝግጁነት እንዲኖረው የማድረግ ስራዎችም ተከናውነዋል፡፡
በተቋሙ የሰው ተኮር አስተሳሰብ እንዲሰርፅ ለማድረግ በርካታ ተግባራት በትኩረት የተከናወኑ ሲሆን እነዚህም የሠራተኞች አቅም ግንባታ፣ የሙያ መሰላል ትግበራ፣ የስራ ከባቢን ማሻሻልና ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢ መፍጠር፣ ሠራተኞችን በተቋሙ በሚከናወኑና በሚወሰኑ ጉዳዮች ላይ ማሳተፍ፣ አንዳንድ የሥራ ክፍሎች ላይ የስራ ሰዓት ማስተካከያ ማድረግ፣ የሠራተኛ ጥቅማጥቅም ክፍያዎች ማሻሻል፣ የሥራ መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦትን ማሻሻል፣ ማህበራዊ ግንኙነትና የቅሬታ አፈታት ሥርዓቱና አተገባበሩ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ሠራተኛውን ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡

በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ቀጣይነት ላለው ስኬት እንደሚያበቃ በማመን ተቋሙ ከአጋር ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችሉ አሰራሮችን በመተግበርና ለሁለቱም ወገን ጠቃሚ አካሄድ መከተልን እንደስራ ባህል እንዲወሰድ በማድረግ ተቋሙ ከአጋሮቹ አመኔታን መልሶ ከማግኘቱም ባሻገር አጋሮቹ ለወደፊት አብሮ ለመስራት ላቅ ያለ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆነው በቻይና ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ጋር የተደረገው የስራ ግንኙነት ሲሆን እነዚሁ ተቋማት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በብድር ጉዳዮች ቀጥታ ለመደራደር እና ለወደፊት የስራ ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ ለመቀጠል ፍላጎት ማሳየታቸው ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ተቋሙ በተቀናጀ መልኩ ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በማህበራዊ አገልግሎቶች፣ ህጻናትን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አረጋዊያንን በማገዝ እና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ በድምሩ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በገንዘብ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በበጀት ዓመቱ የፋይበር መስመሮች መቆራረጥ፣የቴሌኮም ማጭበርበር፣የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዋናነት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

ማጠቃለያ

ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ አበረታች የስራ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን ተቋሙ ይህንን መልካም አፈፃፀም ያስመዘገበው የለውጥ ስራዎች እና ለረጅም ዓመታት ውሳኔ ሳይሰጥባቸው የቆዩ ጉዳዮች ላይ ጎን ለጎን መፍትሔ በመስጠት ጭምር ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ የተገኙ ውጤቶች እና የለውጥ ጉዞ ተቋሙን ለሚመጣው የቴሌኮም የውድድር ገበያ ዝግጁና ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ተቋሙ ባከናወናቸው ሰፊ እና ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስራዎች በበጀት አመቱ መጅመሪያ ከነበረበት የስጋት ደረጃ በመውጣት ውጤታማ ሊሆን ችሏል፡፡
የተቋሙ አመራር ሙሉ ኃይሉን በመጠቀምና በከፍተኛ የባለቤትነት ስሜት በፈታኝ የቢዝነስ ሁኔታዎች ተቋሙን ለተሻለ ደረጃ አብቅቷል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ለዚህ መልካም አፈጻጸም የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርዱን፣ ሰራተኞቹን፣ ደንበኞቹን እንዲሁም የሥራ አጋሮቹንና ባለድርሻ አካላትን እያመሰገነ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ በማድረግ እና ለረጅም ጊዜ ውሳኔ ያላገኙ ስራዎችን በማጥራት እንዲሁም ውዝፍ እዳዎችን እና የአገልግሎት ክፍያዎችን በመክፈል በበቂ የጥሬ ገንዘብ /Net Positive Cash Position/ የበጀት ዓመቱን በጥሩ አፈጻጸም ማጠናቀቁን ያበስራል፡፡

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives