ኢትዮ ቴሌኮም ጌትፋክት ኢትዮጵያ ከተሰኘ ተቀማጭነቱ አሜሪካን ሀገር ከሆነ ድርጅት ጋር የዲጂታል መማሪያ ማዕከላትን በጋራ በመጠቀም የተለያዩ ስልጠናዎችን ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በትብብር ለመስጠት የሚያስችል ብሩህ ትውልድ (Brighter Generation) የተባለ የትምህርት ፕሮግራም በጋራ ለማካሄድ የትብብር ስምምነት ተፈራረመ።
ይህ የትብብር ስምምነት በኢትዮ ቴሌኮም እና በጌትፋክትኢቲ ኢዱኬሽን የጋራ ፍላጎትና ዓላማ ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አጋርነት በመፍጠር በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በማሳተፍ እና የእውቀት ሽግግርን በማምጣት ማዕከላቱ የተቋቋሙበትን አላማ ማሳካት እንዲችሉ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡
በዚህ የትብብር ስምምነት መሠረት ጌትፋክት ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ በሚያካሄደው የትምህርት ማትጊያ እና የሀገር ተረካቢ ወጣቶችን በእውቀት የማስታጠቅ ፕሮግራም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር የተለያዩ ጊዜያት የሚጠናቀቁ አጫጭር እና ለውጥ የሚያመጡ የተግባቦት/ኮሙንኬሽን፤ የቋንቋ፤ የጥልቅ አስተሳሰብና የአመራር እንዲሁም የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ስልጠናዎችን መስጠት ብሎም ሀገራቸውን የሚወዱና በታማኝነት የሚያገለግሉ ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል የሚያግዝ ይሆናል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ ከዚህ ቀደም ባቋቋማቸው የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት አማካኝነት ስልጠናውን በተገቢው መልኩ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ሙያዊ እና የቴክኖሎጂ እገዛ በማድረግ እንደአስፈላጊነቱ ስልጠናዎቹ በቨርቹዋል እና በአካል እንዲሰጡ ድጋፍ ያደርጋል፡፡
በቀጣይም በትብብር ስምምነቱ ለዲጂታል መማሪያ ማዕከላቱ የሚያስፈልጉ የዲጂታል የትምህርት ግብአቶች የማሟላት፣ የሀይል አቅርቦት አማራጮችን የማቅረብ እንዲሁም አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት ዙሪያ በትብብር መስራት የሚያስችል ይሆናል፡፡
ጌትፋክት ኢትዮጵያ ነዋሪነታቸው በውጪ ሀገራት የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት ድርጅት ሲሆን የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ እና በውጪው ዓለም ሚዲያዎች እና የተለያዩ መድረኮች በአሉታዊነት የሚነሱ ሀሳቦችን በመረጃ ተደግፎ ለማስተካከል፤ ስለሀገራችን በጎ አመለካከቶች እንዲዳብሩ ለማገዝ የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም
ታኅሣሥ 27 ቀን 2015 ዓ.ም