ኩባንያችን የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረግ ጉዞውን በማጠናከር በዛሬው ዕለት ከኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ጋር ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት በመፈጸም ደንበኞች የገቢ ግብር እና የቀረጥ ክፍያቸውን እጅግ ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ በሆነው ቴሌብር መፈጸም የሚያስችላቸውን አሠራር ተግባራዊ አድርጓል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት የኦሮሚያ ክልል የገቢዎች ቢሮ የግብር አሰባሰብ ስርአቱን በዲጂታል ሲስተም የተደገፈ በማድረግ የዘመነ የግብር እና የቀረጥ አሰባሰብ ስርዓት ለመዘርጋት፣ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የሥራ ማስኬጃ ወጪንና ጊዜ ለመቆጠብ፣ የክፍያ ደረሰኝ ማጭበርበርን ለማስወገድ፣ ኢንቨስትመንትን ወደ ክልሉ ለመሳብ እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችለው ይሆናል፡፡

ይህ አሰራር የግብር እና የቀረጥ ክፍያዎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ ከሚኖረው ጉልህ ሚና ባሻገር ዜጎች ጊዜ እና ገንዘባቸውን ቆጥበው ቀላል እና አስተማማኝ በሆነው የቴሌብር የሞባይል መተግበሪያ ወይም አጭር ቁጥርን *127# በመጠቀም ክፍያዎቻቸውን በቀላሉ ካለበት ሆነው በመፈጸም የክፍያ ማረጋገጫ ደረሰኝ ወዲያውኑ ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡

ኩባንያችን ከኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ጋር በመቀናጀት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፣ ለክልሉ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች የቴሌብር የአገልግሎት ክፍያ አሰባሰብ እና ተያያዥነት ስላላቸው ጉዳዮች አስፈላጊውን የስራ ላይ ስልጠና እንዲሁም ለደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩ ኮሚሽን ጋር በፈጸመው ስምምነት የከፍተኛ ግብር ከፋዮችን ግብር በወቅቱ ለመሰብሰብ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ ዕቃዎች የጉምሩክ ቀረጥ ክፍያን በቀላሉ መፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሌሎች ክልሎች ጋርም በተመሳሳይ የግብር ክፍያን በቴሌብር መፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ መሰል ተቋማት እና ድርጅቶች የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ስርዓት በማዘመን የዲጂታሉን አለም እንዲቀላቀሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡      

                           ሰኔ 15 ቀን 2015 .                   

                            ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives