ነገን ዛሬ እንትከል በሚል መሪ ቃል በሃገር አቀፍ ደረጃ 500 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል በተያዘው ዕቅድ መሰረት ኩባንያችን በአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ እና ልማት ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት በመላው የሃገራችን ክፍሎች በሚገኙ የኩባንያው ጽ/ቤቶች የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሮችን በይፋ አስጀምሯል፡፡
በዚህም መሰረት ኩባንያችን በኮርፖሬት እና ዞን ደረጃ በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከወረዳ 04 ገላን ኮንደሚኒየም ጀምሮ እስከ ወረዳ 02 መንገድ አካፋይ እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ICT ፓርክ አለፍ ብሎ ልዩ ቦታው ፍልውኃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተዘጋጁ ቦታዎች የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያከናወነ ሲሆን፣ በተጨማሪም በኩባንያው 17 ሪጅኖች ላይ በተረከቧቸው ቦታዎች ላይ ችግኞችን ተክለዋል፡፡ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ከ6ሺህ አምስት መቶ በላይ የኩባንያው ሠራተኞች እንዲሁም ከ300 በላይ አጋሮቻችንም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ኩባንያችን በዚህ በአምስተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ከ400ሺህ በላይ ችግኞችን በመላው ኢትዮጵያ ለመትከል ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ለችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ በጀት በመያዝ አሻራውን ለትውድ ለማኖር አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 603 አካባቢዎች ከ3.4 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል አረንጓዴ አሻራውን ያኖረው ኩባንያችን በአማካኝ ከ81 በመቶ በላይ ችግኞችን በማፅደቅ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ በማልበስ በረሃማነትንና ድርቅን በልምላሜ ለመቀየር የበኩሉን ጥረት ከማድረጉም በላይ ከ17 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ እንዲሁም በለገዳዲ አካባቢ በሚገኘው የድሬ ግድብ የቨርቹዋል ችግኝ ተከላ እና እንክብካቤ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ዓለም የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለማህበረሰባችን ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግና በዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን የማድረጉን ጉዞ አጠናክሮ እየገፋበት ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን የማሕበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣትም በበካርታ ዘርፎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን ከኩባንያችን የማህበራዊ ሃላፊነት ፖሊሲ ዋና ዋና አምዶች (Pillars) መካከል አንዱ ለአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደመሆኑ መጠን ዘመን ተሻጋሪ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡:ለአብነትም ኩባንያችን በአራት ተከታታይ ዓመታት በተደረጉ የአረንጓዴ አሻራ እና የኢኮ ቱሩዝም ፕሮግራሞች ላይ ከ736.2 ሚሊዮን ብር በላይ መዋለ ንዋዩን አፍስሷል::
ሃገራችንን ለ129 ዓመታት በቁርጠኝነት በማገልገል ላይ የሚገኘው ኩባንያችን፣ የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት ለመደገፍና የአስቻይነት ሚናውን ለመጫወት በየጊዜው አዳዲስ አገልግሎቶችን እና ቴክኖሎጂዎችን ከማቅረብ ባሻገር ለማህበረሰባችን እና ለሃገራችን ፋይዳ ያላቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ፣ ሃገራዊና ማህበራዊ የጣምራ ሃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም