ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2014 እስከ ሰኔ 2015 ያለውን የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ፣ የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል እንዲሁም በቴሌኮም ውድድር ገበያው የመሪነት ሚናውን እያጠናከረ ለማስቀጠል የሚያስችለውን የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ነድፎ የትኩረት አቅጣጫና የስትራቴጂ መስኮችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝርዝር ስትራቴጂያዊ ግቦችን ቀርፆ ግቦቹን ሊያሳኩ የሚችሉ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎችና ተግባራት በማቀድ ከ2015 በጀት ዓመት ጀምሮ ትግበራውን መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ኩባንያችን በሦስት ዓመቱ መሪ የእድገት ስትራቴጂ (LEAD Growth Strategy) ላይ በትኩረት እንደተመለከተው የሀገራችንን ዲጅታል ኢኮኖሚ ለማሳደግና ከመሠረታዊ ቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር ያሉትን ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ /ዲጂታል/ መፍትሔዎችና አገልግሎቶችን ለውድ ደንበኞቹ ማቅረብ፣ የኢንተርፕራይዝ ደንበኞቹን ቢዝነስ ለማቀላጠፍና ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም አጠቃላይ የደንበኞቹን ህይወት ለማቅለል የሚያስችሉ አገልግሎቶቹን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ አጠቃላይ በኩባንያችን እያደገ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ ደንበኞቹን በማርካት ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነው የቴሌኮም ገበያ ብቁና ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ለመሆን በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡
ስትራቴጂካዊ ግቦችን ለማሳካት፤ የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ማሻሻልና እርካታን ታሳቢ ያደረገ የኦፕሬሽን ልህቀት ማምጣት፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ማሳደግ፣ እያደገ የመጣውን ከፍተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት ማስተናገድ የሚያስችል የኔትወርክ እና የሲስተም አቅም ማሳደግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለገበያ በማቅረብ፣ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ መናበብ በመፍጠር አዳዲስ አገልግሎቶች ማምጣት፣ የሀብት አጠቃቀምን ማሻሻልና ስትራቴጂያዊ የወጭ ቁጠባን ተግባራዊ ማድረግ፣ የገቢ ምንጭ ማስፋት፣ የዓለም አቀፍ ቢዝነስን በማጠናከር የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማስፋት ገበያው በሚጠይቀው መሠረት አዳዲስ አሰራሮችን መከተል፣ የቴሌኮም ማጭበርበርንና የሳይበር ጥቃቶችን በተደራጀና በተሟላ የቴክኖሎጂና የክህሎት ብቃትን በማሳደግ መከላከል እና የተቋም ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የሰው ኃይልና የአመራር ብቃትና አቅምን ማሳደግ የመሳሰሉ ዋና ዋና ስትራቴጂያዊ እቅዶችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
የገቢ አፈጻጸም
በበጀት አመቱ ኩባንያችን የገቢ ምንጮችን በማስፋት በዋናነት ከመሠረታዊ ቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር ያሉ በርካታ ተቋማትና አጠቃላይ ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ የዲጂታል መፍትሔዎች፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብ እንዲሁም የኔትወርክና የሲስተም አቅም በማሳደግ 75.8 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ በማግኘት የእቅዱን 101% አሳክቷል፡፡ ይህ ገቢ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ23.5% ብልጫ አለው፡፡ የተገኘው ገቢ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የድምጽ አገልግሎት 43.7% ድርሻ ሲኖረው ዳታና ኢንተርኔት 26.6%፣ ዓለም አቀፍ ገቢ 9%፣ እሴት የሚጨምሩ አገልግሎቶች 6.9%፣ የቴሌኮም መጠቀሚያ መሣሪያዎች (ቀፎ፣ ዶንግል፣ ሞደም) 4.7% እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች 7.2% ድርሻ አላቸው፡፡
የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች (ዓለም አቀፍ ኢንተርኮኔክት፣ ሮሚንግ፣ ከመሠረተ ልማት ኪራይ እና ከሀዋላ አገልግሎት) አጠቃላይ 164.1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘት የተቻለ ሲሆን አፈጻጸሙም 107.8% ነው፡፡ የገቢ እድገቱ የተመዘገበው በሁሉም አገልግሎቶች ላይ የተስተናገደው የትራፊክ መጠን በመጨመሩ ሲሆን፡ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በድምጽ ትራፊክ የ34.5% እና በዳታ ትራፊክ የ94.5% እድገት ተመዝግቧል፡፡
ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ ገቢን በማሳደግ፣ ወጪ ቆጣቢ አሰራርና ባህል በማስረጽ እንዲሁም ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሠረት ያልተጣራ ትርፍ (Earnings Before Interest, Tax, Depreciation and Amortization) 51.2% ያስመዘገበ ሲሆን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ያልተጣራ ትርፍ መጠን በ24% ያደገ እንዲሁም ከተያዘው እቅድ አንጻር 135% የላቀ አፈጻጸም አስመዝግቧል፡፡ የተጣራ ትርፍ መጠን 22 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 25% ሲሆን የትርፍ መጠኑ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ109% እድገት ያሳያል፡፡
ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ የገቢ አማራጮችን ለማስፋትና አጠቃላይ ገቢውን ለማሳደግ ካደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት በተጨማሪ ወጭን የመቀነስና ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም እንዲሁም አላስፈላጊ ወጭዎችን ለማስወገድ እና በአጠቃላይ ኩባንያውን ውጤታማና ምርታማ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ በመቅረጽ ተግባራዊ በማድረግ ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበበት ሲሆን በዚህ በጀት ዓመትም ዘርፈ ብዙ የወጪ ቅነሳ ስትራቴጂዎችን በመተግበርና የተለያዩ የወጪ ቅነሳ ዘዴዎችን በመጠቀም ከ6.47 ቢሊዮን ብር በላይ የወጭ ቅነሳ በማድረግ የዕቅዱን 106% ማሳካት ችሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ ውስጥ ለተለያዩ ወጭዎች 82.2 ቢሊዮን ብር የከፈለ ሲሆን ለታክስ ብር 20.8 ቢሊዮን ብር፣ ለብድር ክፍያ 4.23 ቢሊዮን ብር (78.4 ሚሊዮን ዶላር) ለዲቪደንድ 2.5 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለመደበኛ እና ለካፒታል በጀት ወጪ እና ለሌሎች ወጪዎች 54.6 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተከናውኗል፡፡
የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች
በበጀት አመቱ የአገልግሎቶቻችን ተጠቃሚ ደንበኞች ብዛት 72 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን አፈፃፀሙ ካለፈው በጀት ማጠናቀቂያ ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር የ8% እድገት፣ እንዲሁም ከእቅድ አንጻር የ98% አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡ በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 69.5 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ (Fixed Broadband) 618.3 ሺህ፣ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች 853.6 ሺህ እንዲሁም የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 33.9 ሚሊዮን ናቸው፡፡ የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 66.8% ሆኗል፡፡ ዓለም ላይ ካሉ 774 ኦፕሬተሮች መካከል በሞባይል ደንበኛ ቁጥር በአፍሪካ 2ኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን በዓለም 21ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የተመዘገበው የገቢና የተጠቃሚ ደንበኛ አፈጻጸም እጅግ የላቀ ሲሆን የተመዘገበው ውጤት የደንበኞችን ቁጥርና አጠቃቀምን ለማሳደግ፣ ተሞክሯቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ደንበኞችን ለማቆየት የሚያስችሉ የኔትወርክ ማስፋፊያ፣ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እንዲሁም የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 203 (116 አዳዲስ እና 87 ነባር) የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶችን በማሻሻል ለደንበኞች በማቅረቡ ነው፡፡
ምርትና አገልግሎቶቻችንን ከማስፋትና ከማሻሻል አንጻር ከመደበኛ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ያለፉ (beyond connectivity) አገልግሎቶቸች፡ ቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎት፣ ክላውድ፣ ዲጂታል ኮንታክት ሴንተር፣ ቴሌድራይቭ፣ ስማርት ኤዱኬሽን፣ ስማርት አግሪካልቸር፣ ጊጋ ቢትስ ኮምዩኒኬሽን፣ ኢንተርፕራይዝ ሶሉሽንስ ወዘተ…በማቅረብ የድርጅት ደንበኞች ስራቸውን በተሳለጠ ሁኔታ እንዲከውኑ የማስቻል ስራዎች ተከናውኗል፡፡
የደንበኞቻችንን ተሞክሮ እና የአገልግሎት እርካታ ለመፍጠር በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን የሠራናቸው የማሻሻያ ሥራዎችና ያቀርብናቸው አገልግሎት አስመልክቶ በተከናወነው ጥናት የተገኘው ውጤት 7.64 ሲሆን ይህም ከታቀደው አንጻር የ90 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ በተገኙ የጥናት ውጤቶችና ግብዓቶች ላይ ተከታታይ የማሻሻያ ሥራዎች በመሥራት የደንበኛን ተሞክሮና እርካታን ለማሳደግ እየሰራን እንገኛለን፡፡
የአገልግሎት ጥራትን፣ የኔትወርክ ሽፋንና አቅምን እንዲሁም የሲስተም አቅምን ከማሳደግ አንጻር በርካታ የፕሮጀክት ሥራዎች እየተከናወነኑ ሲሆን ለሞባይል ኔትወርክ ማሻሻያ የነባር ጣቢያዎች አቅም ማሳደግና አዳዲስ ጣቢያ በመገንባት በድምሩ በ3,251 ጣቢያዎች ላይ የተከናወኑ 9.5 ሚሊዮን ተጨማሪ የሞባይል ኔትወርክ አቅም በመገንባት ተጨማሪ ደንበኛ ማስተናገድ የሚችል ኔትወርክ አቅም መፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህም የኔትዎርክ የህዝብ ሽፋን (Wireless Network Population Coverage) በ2G 99.19%፣ በ3G 98.4%፣ በ4G/LTE 33% ሽፋን የደረሰ ሲሆን 440ሺህ ደንበኛ የሚያስተናግድ የ5G አቅም ተፈጥሯል፡፡ በመደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎት 228 ሺህ ተጨማሪ ደንበኞች ማስተናገድ የሚያስችል አቅም በበጀት ዓመቱ ተገንብቷል፡፡
የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት አፈጻጸም
የሀገራችንን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካትና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ታስቦ የተጀመረው “የቴሌብር” አገልግሎት 34.3 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራትና አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ የግብይት መጠኑም (Transaction Value) 679.2 ቢሊዮን ብር ማንቀሳቀስ ተችሏል፡፡ የቴሌብር የዲጂታል ስርዓት የፋይናንስ አካታችነትን እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቴሌብር ሳንዱቅ፣ ቴሌብር እንደኪሴ፣ ቴሌብር መላ የተሰኙ የቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከዳሽን ባንክ ጋር በመሆን እ.አ.አ ከነሀሴ ወር 2022 ጀምሮ ለደንበኞቹ በማቅረብ ለ2.4 ሚሊዮን ደንበኞች በቴሌብር መላ እና እንደኪሴ ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከ768 ሺህ በላይ ደንበኞች በቴሌብር ሰንዱቅ (ቁጠባ) ከ3.6 ቢሊዮን ብር በላይ ቆጥበዋል፡፡ በተጨማሪም ቴሌብር ስንቅ፣ ቴሌብር እንደራስ፣ ቴሌብር አድራሽ እና ቴሌብር ድልድይ የተሰኙ የቴሌብር የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በአጋርነት እ.አ.አ ከሰኔ ወር 2023 ጀምሮ ለደንበኞቹ ለወኪሎቹና ለአጋር ነጋዴዎች በማቅረብ በ13 ቀናት ውስጥ 25,666 ደንበኞች 155.3 ሚሊዮን ብር ብድር ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን 2,564 ደንበኞች 14.2 ሚሊዮን ብር መቆጠብ ችለዋል፡፡
የቴሌብር አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግና የኩባንያችን አጋሮችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እስካሁን ድረስ 615 የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ማዕከላት፣ 136 ዋና ወኪሎች፣ ከ107.3 ሺህ በላይ ወኪሎች ከ58.4 ሺህ በላይ ነጋዴዎች /Merchants/ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም ከ23 ባንኮች ጋር የኢንቴግሬሽን ሥራ ተጠናቆ ከባንክ ወደ ቴሌብር ገንዘብ ማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን 21 ባንኮች ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር እንዲቻል ተደርጓል፡፡
የሰው ኃይል ካፒታል ሥራዎች
ኩባንያችን የነደፈውን ስትራቴጂና ዓመታዊ እቅድ በብቃት ለመፈጸም እና ግቡን ለማሳካት በአመለካከት፣ በክህሎትና በብቃት የተገነባ አመራርና ሠራተኛ መኖር ቅድሚያ የሚሰጠውና ቀጣይነት ባለው መልኩ በትኩረት እየሰራበት ያለ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የኩባንያችንን የማስፈፀምና የመፈጸም አቅምን በማጎልበት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ ተከታታይነት ያለው ስልጠና በአካል ከ17.8 ሺህ በላይ እና በዲጂታል አማራጭ ከ22.8 ሺህ በላይ ሠራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡
በሌላ በኩል ሠራተኛውን ተቀራራቢ ብቃት ወደሚጠይቅ የሥራ መደብ በማዟዟር፣ በሚፈጠሩ ክፍት የሥራ መደቦች ላይ አቅምና ልምድን ያማከለ ምደባ በማከናወን ምርታማነትን የማሳደግ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን በሌላ በኩል በየወቅቱ የሠራተኛ እርካታ መጠን የዳሰሳ ጥናት በማከናወን በተለዩ ክፍተቶችና በተገኙ ግብዓቶች መሠረት የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የሠራተኛውን ተነሳሽነትና የባለቤትነት መንፈስ የሚያሳድጉ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን ለአብነት ያህል ሠራተኞችን በተቋሙ ስትራቴጂ ዝግጅትና የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና ግብዓት እንዲሰጡ የማድረግ፣ የሥራ መገልገያ መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሻሻል፣ የሥራ ከባቢን አመቺና ደህነንቱን የማረጋገጥ እንዲሁም የተለያዩ የማበረታቻ ሥርዓቶችን በመተግበር የተሻለ የሥራ ከባቢን የሚፈጥሩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
የሳይበር ሴኩሪቲ ጥቃትና የቴሌኮም ማጭበርበርን መከላከል ሥራዎች
የሀገራችን ዲጂታላይዜሽን እድገት ተከትሎ እያደገና እየተወሳሰበ የሚመጣውን በመሠረተ ልማትና በወሳኝ ሲስተሞች ላይ የሚደረገውን የሳይበር ጥቃት ለመመከት እንዲሁም አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ በርካታ የሳይበር ሴኩሪቲ ሲስተሞች ተግባራዊ በማድረግ አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የኩባንያችን መሠረተ ልማቶች፣ የሲስተሞችና የደንበኞቻችን መረጃዎች ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ የማጭበርበር ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችል የሰው ኃይል፣ የአደረጃጀት፣ የሲስተምና የቅንጅት ሥራዎችን በማከናወን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር የተቻለ ሲሆን ስጋቱ ቀጣይነት ያለው እንደመሆኑ በሁሉም ዘርፍ በትኩረትና በትጋት በቀጣይነት የበለጠ የሚሠራበት ይሆናል፡፡
የቢዝነስ አጋርነት፣ የሥራና የገቢ እድል ፈጠራ ሥራዎች
ኢትዮ ቴሌኮም በአገልግሎቱ የአስቻይነት ሚና ከመጫወቱ ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል እና የገቢ ምንጭ ለመፍጠር የበኩሉን አስተዋፅዖ ለማበርከት እየሰራ ሲሆን በዚህም በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ መደቦች የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም በምርትና አገልግሎት አከፋፋይነት፣ በአጋርነትና በመሳሰሉ ሥራዎች ከተቋማችን ጋር በመሥራት ለበርካታ ዜጎች የሥራና የገቢ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡ በኩባንያችን 17,202 ሠራተኞች በቋሚነት የሚሰሩ ሲሆን 12,317 (72%) ወንዶችና 4,890 (28%) ሴቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም 22,792 ጊዜያዊ (የኮንትራት) ሠራተኞች ያሉ ሲሆን በአብዛኛው የተቋሙን መሰረተ ልማትና የሥራ ማዕከላትን የሚጠብቁ የሴኩሪቲ አባላት ናቸው፡፡ ከኩባንያችን ጋር በቢዝነስ አጋርነት የሚሠሩ 297ሺህ ተቋማት ሥር የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎችን ጨምሮ ኢትዮ ቴሌኮም ለበርካታ ዜጎች የሥራና የገቢ እድል መፍጠር ችሏል፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነት
ኩባንያችን ከተቋቋመለት የቢዝነስ ዓላማ በተጨማሪ ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፈ ብዙ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን መልካም አሻራ እያሳረፈ ሲሆን በተለይም የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ልማት ተጠቃሚነት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢያዊ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት እና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ እና ለመንግስት ፕሮጀክቶች በበጀት አመቱ በድምሩ 439.9 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ የተደረገ ሲሆን በዓይነትና በአገልግሎት (200.6 ሚሊዮን ብር) እና በገንዘብ (239.3 ሚሊዮን ብር) ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች 7.5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡
ከአገልግሎት ውጭ የነበሩ አካባቢዎች ላይ አገልግሎቱን መልሶ ማስጀመር
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልና በተለያዩ አካባቢዎች ከጸጥታ ጋር በተገናኘ ተቋርጦ የነበረውን አገልግሎት መልሶ ከማስጀመር አኳያ ከሰላም ስምምነቱ ጊዜ ጀምሮ ሰፊ ርብርብ በማድረግ፣ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ የቴሌኮም መሳሪያዎች፣ የኮመርሻልና ለአገልግሎት ማዕከላት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ከተለያዩ የኩባንያችን ጽ/ቤቶች በማሰባሰብ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎቱን ማስቀጠል ተችሏል፡፡ በዚህም በ186 ከተሞችና ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 943 የሞባይል ጣቢያዎች እንዲሁም 1,886 ኪ.ሜ የፋይበር መስመር በመጠገንና መልሶ በማቋቋም አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡ በ20 ከተሞች የሚገኙ 22 የኩባንያችን የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት አስፈላጊውን ጥገና በማድረግና የተጓደሉ መሳሪያዎችን በማሟላት ወደ አገልግሎት መመለስ የተቻለ ሲሆን በ86 ከተሞችና ወረዳዎች የሚገኙ 38 የፋይናንስ ተቋማት የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በአፋጣኝ መልሶ በማስቀጠል አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል፡፡
ተግዳሮቶችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች
ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ በወቅቱ የጥገናና የማስፋፊያ ወይም የማሻሻያ ሥራዎች ማከናወን አለመቻል፣ የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት፣ በኔትዎርክ ሀብትና በተቋም ንብረት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ የመሬት አቅርቦት መዘግየት፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የነዳጅ እጥረት፣ የግንባታ ስራ ግብአቶች እጥረት፣ የገበያ አለመረጋጋት እንዲሁም የኮንትራክተሮች በውላቸው መሠረት የመፈጸም አቅም ውስንነት በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች ሲሆኑ ችግሮቹን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ እንዲሁም የተለያዩ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመውሰድ የሚያስከትሉትን ተጽዕኖ መቀነስ ተችሏል፡፡
ለተመዘገበው ስኬት ቁልፍ ሚና የነበራቸው ጉዳዮች
ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበው የላቀ አፈጻጸም በተለይም በውድድር ገበያና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ በማለፍ በዋና ዋና የአፈጻጸም መለኪያዎች የተመዘገበው ውጤት ለበለጠ ስኬት የሚያነሳሳና የኩባንያችን የመፈጸም አቅምና የገበያው እምቅ አቅም ሰፊ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ የላቀ ውጤት የተመዘገበው የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ከኩባንያው አመራር ጋር በመናበብና በመደጋገፍ፣ የኩባንያችን አመራርና ሠራተኞች ለኩባንያቸው ያላቸው የባለቤትነት ስሜትና በውድድር ገበያው በሁሉም መስክ የመሪነት ሚናውን ለማስቀጠል ካላቸው ህልምና ለውጤታማነቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት እንዲሁም በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናትና በአግባቡ በመወጣት ላቀዷቸው ግቦች መሳካት ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረትና ሰፊ ርብርብ ነው፡፡
በተጨማሪም ኩባንያችን ለውድድርና ለእድገት የሚያበቃውን ግልጽ የሆነ ራዕይና ተልዕኮ በመቅረጽና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ በመንደፍ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላትን የዓላማው ተጋሪ ማድረጉ፣ የወጭ ቁጠባን አሰራርና ባህል በማዳበሩ፣ ፈጣንና ውጤትን ያማከለ በጥናት የተደገፈ ውሳኔ የመውሰድ ባህል ማዳበሩ፣ ሐብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋሉ፣ ከቢዝነስ አጋሮችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተናቦ በትብብር መስሥቱ፣ ኩባንያው ያለውን የተለያዩ እምቅ አቅሞችን (ሰፊ የኔትወርክና የሲስተም መሠረተ ልማት፣ የአገልግሎት ተደራሽነት፣ ሰፊ የቢዝነስ አጋሮችና የአገልግሎት ማዕከላት፣ የአሠራር ሥርዓት፣ ሠፊ ልምድና ክህሎት ያለው ሠራተኛ እንዲሁም ታማኝ ደንበኞቻችን ለተመዘገበው ውጤት ዋና ምክንያቶች ናቸው፡፡
ኩባንያችን ላስመዘገበው የላቀ ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጉ የኩባንያችን የሥራ አመራር ቦርድ፣ ሠራተኞቻችን፣ ደንበኞቻችን፣ የኩባንያችን የስራ አጋሮች፤ የምርትና አገልግሎቶቻችን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም