ኢትዮ ቴሌኮም ከመሰረታዊ ኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስነምኅዳር የሚያሻሽሉ የተቋማትን አሰራሮች የሚያዘምኑ እና የዜጎችን የዕለት ተዕለት አኗኗር የሚያዘምኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ደንበኞች የዋሌት ቨርቹዋል የቪዛ ካርድ እንዲኖራቸው የሚያስችል እንዲሁም ነባሩን የሃዋላ አገልግሎት በእጅጉ የሚያዘምኑ ቪዛ ዳይሬክት እና ቴሌብር ሬሚት (VISA Direct and telebirr Remit services) የተሰኙ የአለም አቀፍ ገንዘብ ማስተላለፊያ ሀዋላ አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት ከዓለም አቀፉ አንጋፋ የቪዛ ኩባንያ ጋር ፈጽሟል፡፡
የቪዛ ዳይሬክት አገልግሎት በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖሩ የቪዛ ካርድ ተጠቃሚዎች የቴሌብር ቨርችዋል ካርድ ቁጥርን ብቻ በመጠቀም ገንዘብ ወደ ሀገርቤት ለማስተላለፍ የሚያስችላቸው ሲሆን ይህም ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ገንዘብ ከ190 በላይ ሀገሮች ወደ ሀገርቤት ከነባሩ የሀዋላ አገልግሎት እጅግ በላቀ ቅልጥፍና እና ዝቅተኛ የአገልግሎት ክፍያ እንዲልኩ ያስችላል፡፡ ደንበኞች በቪዛ ዳይሬክት አገልግሎት ገንዘብ ከባህር ማዶ ለመቀበል በቅድሚያ በቴሌብር ሱፐርአፕ ውስጥ በሚገኘው የቴሌብር ቨርችዋል ቪዛ አገልግሎት መመዝገብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ከተመዘገቡ ከአንድ ሰዓት በኋላ የሚደርሳቸውን ባለ16 አሀዝ የቨርችዋል ቪዛ ካርድ ቁጥር ለላኪው ማጋራት ይኖርባቸዋል፡፡
የቴሌብር ሬሚት አገልግሎት ደግሞ በውጭ አገር የሚኖሩ ተጠቃሚዎች ለዚሁ አላማ የበለጸገውን የቴሌብር ሬሚት መተግበሪያ በስልካቸው ላይ በመጫን በአቢሲኒያ ባንክ ሳይበር ሶርስ የክፍያ መግቢያ ቴክኖሎጂ ገንዘብ ለወዳጅ ዘመድ በቴሌብር ሞባይል ቁጥራቸው በቀጥታ ለመላክ የሚያስችል አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ደንበኞች የቴሌብር ሞባይል ቁጥራቸውን ብቻ በማጋራት ከዘጠኝ ሀገራት ማለትም አሜሪካ፣ ካናዳ፣ እስራኤል፣ ሳኡዲአረቢያ፣ ዩናይትድ አረብኢምሬትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጣሊያን እና ስዊድን ለዚሁ አገልግሎት በኩባንያችን የበለጸገውን ዘመናዊ የቴሌብር ሬሚት መተግበሪያ በመጫን ገንዘብ በሃዋላ መቀበል የሚችሉ ሲሆን በቀጣይም ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ተደራሽነቱ እየሰፋ የሚሄድ ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ስምምነት ደንበኞች የቨርችዋል ቪዛ ካርድ ቁጥር እንዲያገኙ እንዲሁም ከመደበኛው ሃዋላ የተሻለ አማራጮች በቪዛ ዳይሬክት እና ቴሌብር ሬሚት ለማቅረብ የሚያስችል ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ድንበር ተሻጋሪ ክፍያዎችን (ኢ-ኮሜርስን ጨምሮ) በኦንላይን በቀላሉ መፈጸም በማስቻል የዲጂታል ፋይናንስ ሥነምህዳር ተደራሽነትን በእጅጉ የሚያሰፉ፣ የዜጎች ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ፣ የሥራ ፈጠራን የሚያበረታቱ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲሁም ጥሬ ገንዘብ የማይጠቀም የሰለጠነ ዲጂታል ማህበረሰብ (cashless society) ለመፍጠር የጎላ ሚና ያበረክታል።
ኩባንያችን በ2016 በጀት ዓመት የቴሌብር ደንበኞቹን ቁጥር ብዛት 47.55 ሚሊዮን ከማድረሱ ባሻገር የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ እና የፋይናንሺያል አካታችነትን ለማረጋገጥ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ እንዲሁም የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽና አካታች ከማድረግ አኳያ ለማህበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው አነስተኛ የሞባይል ብድር፣ ቁጠባ እና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ከዳሸን ባንክ እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር በማቅረብ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ በይበልጥ በማፋጠን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮ ቴሌኮም
ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም