በአፍሪካ የቴሌኮም አገልግሎትን በማቅረብ ፈር ቀዳጅ የሆነው ኩባንያችን ላለፉት 130 ዓመታት ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለማሕበረሰባችን በሰፊው ተደራሽ በማድረግ የልዩ ልዩ ተቋማትንና የድርጅት ደንበኞችን አሠራር ሥርዓት በማዘመን፣ የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸውን በማሳለጥ እንዲሁም የዜጎችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ በማሻሻል በሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ኩባንያችን በተለይም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኘውን የደንበኞቻችንን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እና የደንበኛ እርካታን የሚያሳድጉ፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽሉ እንዲሁም ዘመኑ ያፈራቸውን አስተማማኝና ጥራት ያላቸውን አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችሉ የቴሌኮም እና ዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በስፋትና በቁርጠኝነት በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡
ኩባንያችን የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የሚያስችለውን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥቂት ሀገሮች ብቻ ተግባራዊ የተደረገውን የዓለማችን የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የሆነውን የአምስተኛውን ትውልድ የሞባይል አገልግሎት ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂግጂጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር ከተሞች እና አካባቢያቸው ተግባራዊ አድርጓል፡፡
በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን በሰሜን ምዕራብ ሪጂን ባህርዳር ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የ5ኛው ትውልድ የሞባይል አገልግሎት ጣቢያዎችን በመገንባት የ5ኛው ትውልድ አገልግሎትን በይፋ ያስጀመረ መሆኑን ለህዝባችን ሲያበስር ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፡፡
በዚህ መሠረት ኩባንያችን በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 4 ቴሌ እና ጣና አካባቢ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ (ፖሊ)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና መ/ቤት እና ድብ አንበሳ ሆቴል አካባቢ፣ ባህር ዳር ዋና የገበያ ማዕከል፣ አቫንቲ፣ ጃካራንዳና ኩሪፍቱ ሆቴሎች እንዲሁም አሮጌው አውቶቢስ መናኸሪያ አካባቢዎች የሚገኙ የድርጅት እና ግለሰብ ደንበኞቻችን የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ትሩፋት ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ አድርጓል፡፡
የ5ኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ እስከ 10 ጊ.ባ በሰከንድ (Gbs) የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ዓለማችን የደረሰበት ዘመናዊ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ (Ultra-low latency) ረገድ ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ አገልግሎቱ በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ተግባራዊ መሆን በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የደንበኞች የዳታ እና ኢንተርኔት ፍላጎት ለማርካት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል፡፡
የ5ኛው ትውልድ ኔትወርክ ተግባራዊ መሆን የኔትዎርክ መጨናነቅን በእጅጉ በመቀነስ ደንበኞች ጥራት ያለውና ፈጣን የኮሙኒኬሽን፣ ዲጂታል ሶሉሽኖች እና ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ህይወታቸውን እንዲያቀሉ ያደርጋል፡፡ ዜጎች የኦንላይን ትምህርት፣ ስልጠና፣ መረጃ እና የመዝናኛ አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ እንዲሁም የይዘት ፈጠራ (content creation)፣ ኢኖቬሽን እና የሥራ ፈጠራን በማበረታታት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያሳድጋል፡፡ እንዲሁም እንደ ሀገር የስማርት ስልክ ስርጸትን በመጨመር የዲጂታል ሊትሬሲን በማሳደግ እና የዲጂታል ክፍተትን (digital-divide) በማጥበብ ብቁ ዜጋ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ 5ጂ ለስማርት የጤና አገልግሎት እና ለሆስፒታል አስተዳደር፣ ለስማርት ግብርና፣ ለስማርት ትምህርት፣ ለስማርት ማዕድን፣ ለስማርት ማኑፋክቸሪንግ፣ ለስማርት ኤርፖርትና የጉዞ አገልግሎት፣ ለስማርት ትራንስፖርት፣ ለዘመናዊ የመኖሪያ ቤት (Smart home)፣ ለብሮድካስቲንግና ለመዝናኛ፣ ጌምን ጨምሮ በክላውድ ላይ ለተመሰረቱ የዲጂታል አገልግሎቶች እንዲሁም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ትሩፋቶች ለመጠቀም የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፡፡ አገልግሎቱ የቢዝነስ እና ተቋማት አሠራር በማዘመን ቅልጥፍና ለማምጣት፣ ምርታማነትን በመጨመር ገቢን ለማሳደግ፣ ብክነትን በመቀነስ ትርፋማነት ለማሳደግ፣ ምርትና አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ እንዲሁም መረጃን መሰረት ያደረገ (data-driven) መሰረት ያደረገ አስተማማኝ እና ለተልዕኮ-ወሳኝ የሆነ ፈጣን IOTን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያገኙ በማስቻል ተወዳዳሪነትን በመጨመር ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ በመጨረሻም ክቡራን ደንበኞቻችን ተግባራዊ ባደረግነው ፈጣኑ ኔትወርክ አማካይነት የ5ጂ ሞባይል ያልተገደበ ዳታ፣ የመደበኛ የመኖሪያ ቤት አገልግሎት እንዲሁም የተለያዩ የጥቅል አማራጮችን መጠቀም የሚችሉ ሲሆን ደንበኞች አገልግሎቱን ለመጠቀም የሚያስችሉ የቴሌኮም መሳሪያዎችና ቀፎዎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡
ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም