ይህ ሪፖርት ከሐምሌ 2016 እስከ ታህሳስ 2017 በጀት ዓመት ያለውን የሥራ አፈጻጸም የሚገልጽ ነው፡፡
ኩባንያችን በሀገራችን ኢኮኖሚና የማህበረሰባችንን ሁለንተናዊ እድገት እንዲሁም በዜጎች ኑሮ መሻሻል ላይ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ እንደመሆኑ ፈጣንና ተለዋዋጭ ከሆነው የቢዝነስ ፍላጎት ጋር በማጣጣም ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እየሰራ ሲሆን በዚህም የቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል እንዲሁም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፈ-ብዙ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያና ማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ፈጣን እና ተለዋዋጭ እንደመሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ለማሳካት እና የህብረተሰባችንን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋፆ እያበረከተ ይገኛል፡፡ ይህንንም ራእይ ለማሳካት የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ነድፎ እየተገበረ ሲሆን ይህ በጀት ዓመት የስትራቴጂ ዘመኑ ማጠናቀቂያ ዓመት ነው፡፡
ኩባንያችን የወጠናቸውን ግቦች ከማሳካት አንፃር በስድስት ወራቱ በትኩረት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የደንበኞችን ሁለንተናዊ ተሞክሮ ማሻሻል፣ የአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራትን ማሳደግ፣ የገቢ ምንጮችን ማበራከትና ማስፋፋት፣ የፋይናንስ አቅም ማጎልበት፣ የኦፕሬሽን ልህቀት ማምጣት፣ የኔትወርክ አቅምን ማሳደግ፣ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን አቅም ማሳደግና አገልግሎቶችን ማስፋት፣ ቴክኖሎጂ የደረሰባቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች ማምጣት፣ የሀብት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ አዳዲስ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎቶችን በማምጣትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ አካታች የፋይናንሻል አገልግሎቶች ማቅረብ፣ የመፈፀም እና የማስፈጸም አቅም ያለው የሰው ኃይል ማብቃትን ማጠናከር፣ በተለይም ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ለውጦችን ለማጣጣም የተለያዩ አማራጭ መፍትሄዎችንና እቅዶችን በመቅረጽ የመተግበር፣ የቴሌኮም ማጭበርበርን በተለያዩ ስልቶች የመከላከል እንዲሁም የተቋምን ደህንነት የማረጋገጡ ስራዎች ይገኙበታል፡፡
የደንበኛ ቁጥርን ማሳደግ
ኩባንያችን በበጀት አመቱ አጋማሽ 3.24 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች በማፍራት አጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ብዛት 80.5 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ከእቅድ አንጻር አፈጻጸሙ100% ሆኗል፡፡ እንዲሁም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ5.9 ሚሊዮን ወይም የ7.9% እድገት አሳይቷል፡፡
በአገልግሎት አይነት ሲታይ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች ብዛት 77.7 ሚሊዮን፣ የሞባይል ዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 43.5 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ብሮድባንድ 784.1 ሺ እንዲሁም የመደበኛ ስልክ የድምፅ ደንበኞች 765.6 ሺ ደርሷል፡፡ በዚህም የቴሌኮም ስርጸት (teledensity) መጠን 72.2% ማድረስ ተችሏል፡፡
የደንበኛን ቁጥር ለመጨመር ከተሰሩት ስራዎች መካከል ተጨማሪ የሞባይልና የመደበኛ ኔትዎርክ ማስፋፊያ ሥራዎች፣ ተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት የማቋቋምና የምርትና አገልግሎት አከፋፋይ አጋሮችን ወደ ስራ የማስገባት፣ በድምሩ 9.3 ሚሊዮን የአዳዲስ ሲም ካርድ ሽያጭ የተከናወነ ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ8% ጭማሪ እንዲሁም ከእቅድ ጋር ሲነጻጸር የ113% አፈጻጸም አለው፡፡
ከአፍሪካ ቀዳሚው (1ኛ) ኦፕሬተር
ኩባንያችን ኢትዮ ቴሌኮም ግዙፍ ዘመናዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት በመላ ሀገሪቱ በማስፋፋት የደንበኞች ቁጥርን በማሳደግ በሰራው መጠነሰፊ ሥራ ከአፍሪካ 1ኛ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 17ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን በቅርቡ በጂ.ኤስ.ኤም.ኤ (GSMA) ጥናት ተረጋግጧል። ይህ አስደናቂ ስኬት የኩባንያችንን ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ከማሳደጉም በላይ፣ የባለድርሻ አካላትን አመኔታ ያጎለብታል።
የሞባይል ኔትወርክ ሽፋንና አቅም
የደንበኞችን የአገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት ለማሳደግ በግማሽ አመቱ 202 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ በሞባይል ኔትዎርክ በተከናወኑ የፕሮጀክት ስራዎች ተጨማሪ የ4.6 ሚሊዮን የሞባይል ኔትዎርክ አቅም በመገንባት 86.1 ሚሊዮን የነበረውን የሞባይል ኔትወርክ አቅም ወደ 90.7 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡ የሞባይል ኔትዎርክ ማስፋፊያዎቹ የዘመናችን የመጨረሻ ፈጣኑን 5ጂ፣ ባለከፍተኛ አቅም ዘመናዊ (Massive MIMO)፣ 4ጂ LTE፣ በ3G እና በ2G አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህም መሠረት 67 ተጨማሪ ከተሞች በድምሩ 491 ከተሞች የ4ጂ እንዲሁም 10 ከተሞች የ5ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
የገጠር ሞባይል አገልግሎት
ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው የገጠር ቀበሌዎች እና መንደሮች የገጠር ሞባይል ሶሉሽኖች በመገንባት የአካባቢው ነዋሪዎችን ወደ ዲጂታሉ አለም ለመቀላቀል በትጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዜጎች መካከል ኢፍትሀዊ የዲጂታል አገልግሎት ስብጥርን በማጥበብ ዘላቂ ልማት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በግማሽ ዓመቱ በዘጠኝ ክልሎች በሚገኙ በ71 ወረዳዎች 81 የገጠር ሞባይል ኔትዎርክ ጣቢያዎች የተገነባ ሲሆን በአጠቃላይ በአስራ ሁለት ክልሎች በሚገኙ 231 ወረዳዎች 295 ጣቢያዎች ተገንብቷል፤ 327,290 የሞባይል አቅም መፍጠር ተችሏል፡፡
የጥገናና አገልግሎትን መልሶ ማስጀመር
በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከጸጥታ ጋር በተገናኘ ተቋርጠው የነበሩ አካባቢዎች ላይ የአገልግሎት መልሶ ማስጀመር ለማድረግ ሰፊ ርብርብ በማድረግ፣ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችሉ የተለያዩ የቴሌኮም መሳሪያዎች፣ የኮሜርሻልና ለአገልግሎት ማዕከላት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ከተለያዩ የኩባንያችን ጽ/ቤቶች በማሰባሰብ አገልግሎት ለማስቀጠል ተችሏል፡፡
በዚህም መጠነ ሰፊ የመልሶ ማስጀመር ሥራ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አፋር ብሄራዊ ክልሎች በሚገኙ 216 ከተሞች እና ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ 231 የሞባይል ጣቢያዎች በመጠገንና መልሶ በማቋቋም አገልግሎት ማስጀመር ተችሏል፡፡
የፊክስድ ኔትወርክ አቅምንና ጥራት
የኔትዎርክ ጥራት እና አቅምን ለማሳደግ 133,672 ደንበኛ ማስተናገድ የሚችል ኦፕቲካል ዲስትሪቢውሽን ኔትወርክ (ODN) የተገነባ ሲሆን በዚህም የODN አቅማችንን 769,932 ማድረስ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም የፋይበር ተደራሽነትን ለማስፋት በበጀት አመቱ የያዘውን “የኮፐር ስዊች ኦፍ ኢኒሼቲቭ” በማስቀጠል ከተያዘው 100 ሺ እቅድ ውስጥ በስድስት ወራቱ 18.3 ሺ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የኮፐር መሠረተ ልማትን ሙሉ በሙሉ ወደ ፋይበር የመቀየር ስራ ከመከናወኑ በተጨማሪ ኮሪደር ሥራ በሚከናወንባቸው ከተሞች የቀጣዩን የቴክኖሎጂ እድገት እና ፍላጎት ያማከለ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ማዘዋወር እና የማሻሻል ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዚህም ደንበኞቻችን ፈጣን የኢንተርኔትና ዳታ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ ከማድረጉም በላይ ለሀገራችን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ሀገራዊ ልማት መፋጠን ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን መገንባት እና ማዘመን
ሲስተሞች ማሳደግና ማሻሻል
ኩባንያችን ዘመኑ የደረሰባቸውንና አጠቃላይ ለማህበረሰቡ አኗኗር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሰፊው ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ለደንበኞች ፈጣንና ምቹ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችሉና አሰራርን በእጅጉ የሚያዘምኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ፡- የኢንተርፕራይዝ ሶሉሽንስ፣ የሞባይል መኒ እና የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ማስፋፊያ፣ የክላውድ አገልግሎት፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ የኦፕሬሽንስ ሰፖርት እና የኮርፖሬት ሶልዩሽንስ፣ የሴኩሪቲ ሶልዩሽንስ ይገኙበታል፡፡
የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት
በመንግስት የተያዘውን የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይን እውን ከማድረግ አንጻር በተሰሩ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሰረት በማድረግ በ2 ዳታ ማዕከሎቻችን 112 IT Rack/896kw IT Load አቅም ያለው የማስፋፊያ ስራ የተሰራ ሲሆን፤ በዚህም የዳታ ሴንተር አቅማችንን ወደ 4.2MW IT Load /512 IT Rack ማሳደግ ተችሏል። የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው እና ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ እንዲያደርጉ የሚያስችለው የክላውድ ኢንፍራስትራክቸር ማስፋፊያ ፕሮጀክት የተተገበረ ሲሆን በዚህም በግማሽ አመቱ፡- በelastic compute ከ3,072 vCPU ወደ 16,768 vCPU እንዲሁም storage ከ1.3 PB ወደ 4.58 PB ማሳደግ ተችሏል፡፡
ምርትና አገልግሎቶችን መጨመር
ኩባንያችን ለደንበኞቹ የሚያቀርባቸውን ምርትና አገልግሎት በማስፋት የደንበኞችን ህይወት የሚያቀሉ፣ የቴሌኮም ተጠቃሚነትና ሁለንተናዊ ተሞክሮ የሚያሻሽሉ፤ የድርጅት ደንበኞችን አሰራር ይበልጥ በማዘመን ቀልጣፋ እና ውጤታማ ለማድረግ፣ እንዲሁም ማህበረሰቡን የዲጂታል ኢኮኖሚው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ወቅታዊነትን የተላበሱ 62 አዳዲስ እና 109 ማሻሻያ በአጠቃላይ 171 የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶች ለደንበኞች ቀርበዋል፡፡
በግማሽ አመቱ የተደራሽነት ክፍተት ባለባቸው አካባቢዎች እና ከተሞች 68 ተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ስራ በማስጀመር አጠቃላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ብዛትን 1000 ማድረስ የተቻለ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 513 በፍራንቻይዝ፣ 487 በኩባንያችን ባለቤትነት የተያዙ ማዕከላት ናቸው። ኢትዮ ቴሌኮም በተገበረው ዲስትሪቢውሽን ስትራቴጂ መሰረት 64 ዋና ዋና አከፋፋዮች፣ 43 የቨርችዋል ቶፕአፕ አከፋፋዮች፤12.7 ሺ ንዑስ አከፋፋዮች፣ እንዲሁም 290.6 ሺ ቸርቻሪዎች በሽያጭ ስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም አጠቃላይ የአጋሮችን ቁጥር ወደ 303.4 ሺ ማሳደግ ተችሏል፡፡
የአለም ዓቀፍ ግንኙነት
በበጀት አመቱ አጋማሽ በሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ እና ሶማሌላንድ በኩል የምናደርገው የአለም ዓቀፍ ግንኙነት አቅም በ190 Gbps በመጨመር 1.83 (TB per second) ለማድረስ የተቻለ ከመሆኑ ባሻገር ከጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ቴሌኮሙኒኬሽን ግሩፕ ጋር ምሥራቅ አፍሪካን በዓለምአቀፍ ዲጂታል ሥነ-ምህዳር ውስጥ ቁልፍ ሚና እንድትጫወት የሚያስችላት የባለከፍተኛ አቅም ባለው (መልቲ-ቴራቢት) ሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ MOU ስምምነት አድርጓል፡፡
እንዲሁም ከጎግል እና ሜታ- ፌስቡክ በተጨማሪ በበጀቱ አጋማሽ ከኔትፍሊክስ ጋር በደንበኞቻችን በብዛት የሚጎበኙ ይዘቶችን ሀገር ውስጥ በማስቀመጥ ፍጥነትን ለማሻሻል የሚያስችል 40Gbps አቅም ያለው የcache አገልግሎት ተግባራዊ ተደርጓል።
ገቢን ማሳደግ
በግማሽ በጀት ዓመቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የኔትወርክ ጥራት እና ተደራሽነትን የሚያሳድጉ መሠረተ ልማቶች በማስፋፋት የሀገራችንን ሁለንተናዊ እድገት የሚያፋጥኑ፣ የማህበረሰባችንን ቁልፍ ችግሮች የሚፈቱ እና ህይወት የሚያዘምኑ፣ የደንበኞችን የቴሌኮም አጠቃቀምና ተሞክሯቸውን የሚያሻሽሉ፣ የድርጅት ደንበኞችን ውጤታማነት የሚያሳድጉ እንዲሁም በአጠቃላይ የሀገራችንን ተወዳዳሪነት የሚጨምሩ በርካታ ምርትና አገልግሎቶች አቅርበናል፡፡
በዚህም ኩባንያችን በግማሽ አመቱ በተሰራው ረቂቅ የሂሳብ ሪፖርት መሰረት አጠቃላይ ገቢ 61.9 ቢሊዮን ብር በማስገኘት የእቅዱን 90.7% እንዲሁም ከአለም አቀፍ አገልግሎት የተገኘ ገቢ 64.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማስገባት የእቅዱን 63.8% ማሳካት ችሏል፡፡
ለገቢው መጨመር የሞባይል ደንበኞች የዳታ አጠቃቀም ትራፊክ 642.2 ቢሊየን ሜ.ባ የደረሰ ሲሆን ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ48.8% እድገት እንዲሁም የሞባይል ድምጽ አገልግሎት በደቂቃ ወደ 83.6 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ12.7% ጭማሪ ማሳየቱ ለገቢው መጨመር ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
የውጭ ምንዛሪ
በግማሽ አመቱ የውጭ ምንዛሪ ከማመንጨት አንፃር በተከናወኑ ተግባራት 72.6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማግኘት የእቅዱን 58.7% ያሳካ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 67.36 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአለም አቀፍ አገልግሎት የተገኘ ገቢ ሲሆን 5.24 ሚሊዮን ዶላር በቴሌብር አለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር አማካኝነት ከውጪ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ነው፡፡
ቴሌብር ለዲጂታል ኢኮኖሚ
በግማሽ አመቱ 5 ሚሊዮን ደንበኞች በመመዝገብ አጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 51.5 ሚሊዮን በላይ ማድረስ የተቻለ ሲሆን የዕቅዱን 99.8% ማሳካት ተችሏል፡፡ በግማሽ አመቱ 1.03 ትሪሊዮን ብር የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር በቴሌብር የተከናወነ ሲሆን አገልግሎት ከተጀመረ ጀምሮ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ 3.58 ትሪሊየን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ተችሏል፡፡ ይህም የገንዘብ ዝውውሩን ዲጂታላይዝ በማድረግ የፋይናንስ አገልግሎቱን አካታችና ተደራሽ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡
የፋይናንስ መግለጫዎች (Unaudited statement)
ኩባንያችን ገቢን በማሳደግና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመከተል ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሰረት ያልተጣራ የትርፍ መጠን (EBITDA) 32.82 ቢሊዮን ብር ወይም ያልተጣራ ትርፍ ህዳግ መጠንን 55.6% በማድረስ የእቅዱን 179.9% ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በተጨማሪም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 23.74 ቢሊየን ብር ግብር ወይም ታክስ ለመንግስት ገቢ ከማድረግ ባሻገር 15,405,770.24 የአሜሪካን ዶላር ወይም 1,820,038,440.37 ብር የውጭ ብድር መልሶ ክፍያ መፈጸም ችሏል፡፡
በበጀት አመቱ መጀመሪያ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ከማድረጉ ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሪ ተመን ገበያ መር እንዲሆን መወሰኑን ተከትሎ ኩባንያችን አብዛኛውን ኢንቨስትመንት በውጪ ምንዛሬ የሚሸፍን እንደመሆኑ የብር ዋጋ መቀነስን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ገቢን ከማስፋፋት እና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን ከመተግበር በተጨማሪ የኩባንያውን አገልግሎት የመስጠት ቀጣይነት እና መልሶ ኢንቨስት በማድረግ ጥራት ያለው አገልግሎት ለደንበኞቹ በተገቢው ሁኔታ መስጠት የሚያስችለውን ሚዛናዊ የዋጋ ማስተካከያ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የዋጋ ማስተካከያው የደንበኞችን የመክፈል አቅም መሰረት ያደረገ እና ለውጡ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚያስከትለውን የወጪ ጭማሪ እንዲሁም የአገልግሎት ቀጣይነትን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን ጭማሬው ከተከሰተው ከፍተኛ የምንዛሪ ለውጥ አንጻር ጫናውን በመሸከም ጭማሬውን በተወሰኑ አገልግሎቶች ላይ ብቻ በማድረግ፣ የደንበኞችን የመክፈል አቅም፣ የኢኮኖሚ ጫና፣ እንዲሁም አካታችነትን መርህ ባደረገ መልኩ በማከናወን ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን እና በርካታ ደንበኞች የሚጠቀሙባቸው 43% የሚሆኑት ላይ የዋጋ ጭማሪ አልተደረገም::
የኦዲት ሪፖርት
ኩባንያችን የፋይናንሱን ጤንነት ለማረጋገጥ በዘረጋው የአሰራር ስርአት መሰረት እስከ 2016 በጀት አመት ያለው የሂሳብ ሪፖርቱን በአለም አቀፍ የሂሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት ስርአት (IFRS Based Financial report) መሰረት በማዘጋጀት፤በውጭ ኦዲተሮች ተመርምሮ እንከን አልባ (Unqualified) መሆኑ ተረጋግጧል።
የወጪ ቁጠባ ባህልን ማጎልበት
ኩባንያችን በግማሽ አመቱ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ የወጪ ቁጠባ በማድረግ የዕቅዱን 144% ማሳካት ችሏል፡፡ ለዚህ ስኬት አስተዋፆ ያበረከቱት ቁልፍ ጉዳዮች ውስጥ ውጤታማ የሀብት አጠቃቀም ስልቶችን መተግበር፣ ከአጋር አካላት ጋር መተባበር እንዲሁም የእለት ተእለት ተግባራትን ዲጂታላይዝ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው።
የሳይበር ደህንነት
በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የሳይበር ስጋትን በተጠናከረ መልኩ ለመከላከል እንዲቻል ኩባንያችን የሰው ሃይል አቅምን በመገንባት፣ የአሰራር ሂደትን በማዘመን እና እጅግ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅ በግማሽ አመቱ የተሞከሩበትን ጥቃቶች በመመከት የኩባንያችንን ዋና ዋና እሴቶች ሊገጥማቸው ከነበሩ የዳታ መመዝበር፤ የአገልግሎት መቋረጥ እና የገቢ ብክነትን መከላከል ተችሏል። በግማሽ አመቱ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ለመግታት አዳዲስ መቆጣጠሪያዎችን በመተግበር 266,162 በላይ ሙከራዎችን ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት ሙሉ በሙሉ መመከት ተችሏል።
የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ
ኢትዮ ቴሌኮም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተገበረ ያለውን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ለማፋጠን እና በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ ፕሮጀክት ቀርፆ እየተገበረ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግበራ የተገባ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ ተደራሽ በመሆን የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይ እውን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ እስካሁን 5.7 ሚሊዮን ደንበኞችን መመዝገብ የተቻለ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 5.1 ሚሊዮን ደንበኞች የፋይዳ ቁጥራቸው እንዲደርሳቸው እና እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ በ2017 በጀት የመጀመሪያው መንፈቅ አመት 4.2 ሚሊዮን ደንበኞችን መመዝገብ ተችሏል፡፡ በአማካይ 27 ሺህ ዜጎችን በየቀኑ የመመዝገብ አቅም የተፈጠረ ሲሆን በ12 ክልሎች፣ በ2 የከተማ አስተዳደሮች፣ ከ275 በላይ የክልል ከተሞች እና ወረዳዎች በ444 የሽያጭ ማዕከሎቻችን እንዲሁም በ304 ተንቀሳቃሽ ቡድን ምዝገባው እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የሰው ኃይል አቅም ግንባታ
የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ስራዎችና ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠር አንጻር የተሰሩ ስራዎች የኩባንያችንን የማስፈፀምና የመፈጸም አቅምን በማጎልበት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማረጋገጥ የሰው ኃይሉን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም የሥራ ባህል ከማነጽ አኳያ እንዲሁም ተቋማዊ ባህልን ለማሻሻል፣ የደንበኞች መስተንግዶ ባህልና ስነምግባርን ተቋሙ ከደረሰበት ደረጃ ጋር በማስተሳሰር ለማሻሻል የስልጠና ፕሮግራም በማዘጋጀት 26,505 ሰራተኞችን ማሰልጠን ተችሏል። በተጨማሪም 26 ሰራተኞች በሰርተፊኬሽን ዘርፎች ሰርቲፋይድ መሆን ሲችሉ 246 በሂደት ላይ ናቸው።
የስልጠና ውጤታማነት ዳሰሳ ተደርጎ የተሰጠው ስልጠና 93% ውጤታማና አላማውን ያማከለ መሆኑ ተረጋግጧል። በግማሽ ዓመቱ በኩባንያችን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የተመሩ እና ከፍተኛ የኩባንያው አመራሮች የተሳተፉበት ተከታታይ ስትራቴጂያዊ አውደ ጥናቶች የተካሄዱ ሲሆን እነዚህም የፕሮጀክት አፈጻጸምን በማሻሻል፣ በሀብት አጠቃቀም እና በአሰራር ሥርዓት ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የአውደ ጥናቶቹም አላማ የኩባንያችንን የፕሮጀክት አፈፃፀምን ቅልጥፍናን እና ልህቀትን ለማሻሻል፤ የሃብት አጠቃቀምን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ፣ የአሰራር ቅልጥፍናን ለማሳደግ እና በተቋሙ ውስጥ የአሰራር ልህቀትን ለማምጣት እንዲሁም የኩባንያችንን የአሰራር ስርዓት ለማሻሻል የሚያስችል ስትራቴጂዎችን ለመቅረፅ ያለመ ነው።
የሥራ ዕድል ፈጠራ
ኩባንያችን አጠቃላይ ለሀገራዊ እድገት የአስቻይነት ሚና በመጫወት ከሚያደርገው ሀገራዊ አስተዋጽዖ በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ እና የገቢ እድል ለመፍጠር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዚህም በቋሚና በጊዜያዊ ሰራተኝነት የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም በምርትና አገልግሎት አከፋፋይነት፣ በአጋርነትና በመሳሰሉ ሥራዎች ከተቋማችን ጋር በመሥራት ለበርካታ ዜጎች የሥራና የገቢ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በተቋሙ16,564 ሠራተኞች በቋሚነት የሚሰሩ ሲሆን 11,870 (72%) ወንዶችና 4,694 (28%) ሴቶች ናቸው፡ ፡ በተጨማሪም 23,173 ጊዜያዊ (የኮንትራት) ሠራተኞች ያሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሴኩሪቲ አባላት ናቸው፡፡ ከአጋር ተቋማት ጋር በተገናኘ አጠቃላይ 347 ሺ በላይ የተለያዩ የቢዝነስ አጋሮች ያሉን ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 303.3 ሺ የኩባንያችን ምርትና አገልግሎት የሚያከፋፍሉ ናቸው፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት
ኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያከናውናቸው በርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎች በተደራጀ ሁኔታ የታቀዱና የትኩረት አቅጣጫዎች በጥናት በመለየት የህብረተሰቡን የረጅም ጊዜ ልማት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢያዊ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማትና ማስዋብ በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡
በግማሽ አመቱ በዓይነት 131.3 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በገንዘብ 155.9 ሚሊዮን ብር በድምሩ 287.2 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽዖ የተደረገ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለሰብአዊ ድጋፍ፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ማስዋብ እንዲሁም ለሀገራዊ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ኩባንያችን የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲካሄድ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማሳየት የኩባንያችንን ሰራተኞችና አጋሮቻችንን በማሳተፍ በመላው አገሪቱ ችግኞች እንዲተከሉ የተደረገ ሲሆን በግማሽ አመቱም በ6ኛው ዙር በ105 ጣቢያዎች ከ446ሺ በላይ ችግኞች በመትከል ማህበራዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል።
ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየት የገንዘብ እና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታ እና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡
ኩባንያችን ያገኛቸው ዓለም አቀፍ የማረጋገጫ ሰርተፊኬቶች
በግማሽ አመቱ ኢትዮ ቴሌኮም ISO 27001:2022፣ PCI DSS እና Cloud Security Alliance (CSA) የቴሌብር እና የቴሌክላውድ አለም አቀፍ ሰርተፍኬቶችን በተሳካ ሁኔታ አግኝቷል። እነዚህ አለምአቀፍ እውቅና ማረጋገጫዎች ኩባንያችን የሚጠበቅበትን ሀላፊነት መወጣት መቻሉን ብቻ ሳይሆን መሪ ዲጂታል ሶልዩሽን አቅራቢ ለመሆን የሰነቅነውን ራዕይ እውን ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ እንደ ማዕዘን ድንጋይ ይመሰላሉ።
ይህም ደንበኞቻችን፣ አጋሮቻችን እና ባለድርሻ አካላት በአገልግሎታችን ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳድግ ነው፡፡ የኩባንያችን ትኩረት በጥራት እና አለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ማቅረብ ላይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን ይህም በዲጂታል ስነ-ምህዳር ግንባር ቀደም መሆናችንን ያሳያል።
በመጨረሻም ኩባንያችን ላስመዘገበው የላቀ ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጉ ሠራተኞቻችን፣ ደንበኞቻችን፣ የስራ አጋሮች፤ የምርትና አገልግሎቶቻችን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
ጥር 26 ቀን 2016 ዓ.ም
ኢትዮ ቴሌኮም