ኩባንያችን የ2016 በጀት አመት እቅዱን በስኬት አጠናቋል!

መሪ (LEAD GROWTH STRATEGY) የሶስት አመት የእድገት ስትራቴጂያችን ኢላማውን ለመምታቱ፤ ውጤቶቻችን ይናገራሉ!

ባጠናቀቅነው የ2016 በጀት አመት መሪ የሶስት አመት የእድገት ስትራቴጂያችንን ሁለተኛ አመት አጠናቀናል፡፡ በውጤቱም የቴሌኮም ደንበኞቻችን ቁጥር ከአምና ተመሳሳይ ወቅት በ8.9% በማሳደግ 78.3 ሚሊዮን አድርሰን የእቅዳችንን 100.4% አሳክተናል፡፡ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢያችንን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በ21.7% ወይም በ16.7 ቢሊዮን ብር በማሳደግ 93.7 ቢሊዮን ብር አስገኝተን የእቅዳችንን 103.6% አሳክተናል፡፡

የውጭ ምንዛሪ የማመንጨት አቅማችንን አስፍተን ከአምናው የ20.7 በመቶ አሳድገን አጠቃላይ 198.02 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማስገባት የእቅዳችንን 117.5% አሳክተናል፡፡ 

ኩባንያችን የገቢ ምንጩን በማስፋትና በማሳደግ እንዲሁም ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በመከተል ትርፋማነቱን ለማጠናከር ባቀደው መሠረት DO2SAVE በተሰኘ ስትራቴጂ የተደገፈ ኩባንያ- አቀፍ የወጭ ቁጠባ (cost optimization) በመተግበር በበጀት ዓመቱ ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በመቆጠብ የእቅዳችንን 134% ለማሳካት ተችሏል፡፡ በመሆኑም በውጪ ኦዲተር ባልተረጋገጠ ጊዜያዊ የኩባንያችን የውስጥ ፋይናንስ ሪፖርት መሰረት ያልተጣራ ትርፍ (EBITDA) 42.44 ቢሊዮን ብር ወይም ያልተጣራ ትርፍ ህዳግ መጠንን 47% በማስመዝገብ የእቅዳችንን 102.4% ማሳካት ችለናል፡፡ እንዲሁም የኩባንያችን የተጣራ የትርፍ መጠን 21.79 ቢሊዮን በማድረስ የእቅዳችንን 108.7% ያሳካን ሲሆን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 20.9% (የ3.76 ቢሊየን ብር) እድገት አሳይቷል፡፡

የቴሌብር ደንበኞቻችንን ብዛት 47.55 ሚሊዮን በማድረስ የእቅዳችንን 107.8% ያሳካን ሲሆን ይህም በብሔራዊ ባንክ የመጋቢት 2016 ዓ.ም ሪፖርት መሰረት ቴሌብር በደንበኛ ብዛት ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የሞባይል መኒ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የ45.7% ድርሻ መያዙ ተረጋግጧል፡፡

የገንዘብ ዝውውርን በቴሌብር ዲጂታላይዝ በማድረግና የፋይናንስ ተደራሽነትን እና አካታችነትን በመጨመር በበጀት አመቱ 1.81 ትሪሊዮን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር በቴሌብር የተከናወነ ሲሆን አገልግሎት ከተጀመረ (May 11, 2021) ጀምሮ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ 2.55 ትሪሊየን የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ተችሏል፡፡ 

ደንበኞቻችንስ ስለእኛ ምን አሉ?

ኩባንያችን የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካትና ደንበኛ ተኮር የሆኑ አገልግሎቶችን ለገበያ ለማቅረብ የደንበኞች እርካታ ዳሰሳ ጥናት በማድረግ ደንበኞቹ ስለ ኢትዮ ቴሌኮም ያላቸውን ምልከታ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ያደረገ ሲሆን በበጀት አመቱ ሁለት ጊዜ የደንበኛ እርካታ ዳሰሳ ጥናት (Customer Satisfaction Survey) በሶስተኛ ወገን አማካኝነት አከናውኗል፡፡ በውጤቱም የግለሰብ ደንበኞቻችን የእርካታ መጠን ከአስር 8.4 ሲሆን ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ13% እድገት  አሳይቷል፡፡ በሌላ በኩል የድርጅት ደንበኞቻችን እርካታ መጠን ከአስር 7.9 ሲሆን ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ15% እድገት አሳይቷል፡፡

 ሻምፒዮናችን፤ ተከታታይ እድገታችን!

በበጀት አመቱ በሁሉም ዋና ዋና መለኪያዎች እቅዶቻችንን ከመቶ ፐርሰንት በላይ አሳክተናል!

ኩባንያችን እያደገ ያለውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ደንበኞቹን በማርካት ፣ ፈጣንና ተለዋዋጭ በሆነው የቴሌኮም ገበያ ብቁና ተመራጭ አገልግሎት ሰጪ ተቋም በመሆን የመሪነት ሚናውን ለማጠናከር በትጋት በመስራት ባለፉት ስድስት አመታት የተጣራ ትርፍ በአራት እጥፍ ማሳደግ ችለናል፡፡

በተጨማሪም ባለፉት ስድስት አመታት በሀገራችን ካሉ የግልና የመንግስት የልማት ደርጅቶች ቀዳሚ ፣ የፕላቲኒየም ታክስ ከፋይ ተቋም በመሆን ተሻላሚ ሆኖ የቆየ ሲሆን በ2016 በጀት አመትም 29.76 ቢሊየን ብር ታክስ፣ 9.97 ቢሊየን ብር የመንግስት የትርፍ ድርሻ እንዲሁም ቀደም ሲል በቬንደር ፋይናንሲንግ ለተከናወኑ የማስፋፊያ ስራዎች የውጭ ብድር 3.4 ቢሊየን ብር (58.45 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር) ክፍያ ፈጽሟል።

የስኬቶቻችን ሚስጥር

ከስኬቶቻችን ጀርባ የኩባንያችን አመራርና ሠራተኞች ለኩባንያቸው ካላቸው የባለቤትነት ስሜት የሚመነጭ ቁርጠኝነት እና ያልተቆጠበ ጥረት ዋነኛው ምክንያት ሲሆን በበጀት አመቱ የተተገበሩ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማት አቅም እና ሽፋንን የሚያሳድጉ ስራዎች፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያረጋግጡ ተከታታይ የኔትወርክ ማትባት ስራዎች፣ ለደንበኞች አገልግሎት የሚሰጥባቸውንና ኩባንያው ቢዝነሱን የሚመራበትን ሲስተሞች የማሳደግና የማሻሻል ስራዎች፣ የደንበኞች አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እና እርካታን ለመጨመር በበርካታ የአገልግሎት መስጫ ማእከላት እና ዲጂታል ቻነሎች የተሰሩ የተደራሽነት ስራዎች፣ ምርትና አገልግሎቶችን የማስፋትና የማሻሻል ስራዎች፣ የኮሚዩኒኬሽን፣ የማስታወቂያ እና የመልካም ገጽታ ግንባታ ስራዎች፣ የDO2SAVE የወጭ ቁጠባ (cost optimization) ስትራቴጂ ትግበራ፣ የኦፕሬሽን ልህቀትን ለማምጣት የተተገበሩ የአሰራር ስርዓቶች እንዲሁም የሰው ኃይል እና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሰራተኞቻችን ምርታማነት 

ከስኬቶቻችን ጀርባ የኩባንያችን አመራርና ሠራተኞች ለኩባንያቸው ካላቸው የባለቤትነት ስሜት የሚመነጭ ቁርጠኝነት እና ያልተቆጠበ ጥረት ዋነኛው ምክንያት ሲሆን በበጀት አመቱ የሰራተኞቻችን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ22% እድገት ማስመዝገብ ችለናል፡፡

የሞባይል ኔትወርክ ሽፋንና አቅምን ማሳደጋችን

በበጀት አመቱ በተተገበሩ የፕሮጀክት ስራዎች ተጨማሪ 7 ሚሊዮን የሞባይል ኔትወርክ አቅም በመገንባት አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ አቅማችንን 86.1 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡ 

የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተልማት አቅም እና ሽፋንን የሚያሳድጉ ስራዎች፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያረጋግጡ ተከታታይ የኔትወርክ ማትባት ስራዎችን በመስራት በሞባይል ኔትወርክ የ4G ማስፋፊያ በ966 ጣቢያዎች ላይ እንዲሁም የ3G ማስፋፊያ ስራዎች በ682 ሳይቶች ላይ የተሰሩ ሲሆን የኔትወርክ ሽፋን ክፍተት ባለባቸው እና መጨናነቅ በሚታይባቸው አካባቢዎች 462 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች መገንባት ተችሏል፡፡ በዚህ ሂደት የ4G ኔትወርክ አገልግሎትን ወደ 124  ተጨማሪ ከተሞች እና ወረዳዎች በማስፋፋት በአጠቃላይ 4G ተደራሽ የሆነባቸውን ከተሞች ቁጥር ከ300 ወደ 424 ማሳደግ ተችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ በ79 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የ5G የኔትወርክ ማስፋፊያ ስራ በማከናወን የ5ጂ ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ 189 ማድረስ የተቻለ ሲሆን፤ አዲስ አበባን ጨምሮ 5 የክልል ዋና ከተሞችን የ5G ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ ተጨማሪ 4 ከተሞችን የ5G ተጠቃሚ ለማድረግ የትግበራ ስራ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ የምርትና አገልግሎቶቻችን መስፋት እና መሻሻል

የኩባንያችንን ምርትና አገልግሎቶች ከማስፋትና ከማሻሻል እንዲሁም የደንበኞችን የቴሌኮም አጠቃቀም ከማሳደግና ተሞክሯቸውን ከማሻሻል አንጻር የማህበረሰቡን ህይወት ይበልጥ የሚያዘምኑ፣ የደንበኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ እንዲሁም የድርጅት ደንበኞች ውጤታማነት የሚያሳድጉ፣ ስራቸውን በተሳለጠ ሁኔታ እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ እና ወቅታዊነትን የተላበሱ  127 አዳዲስ እና 143 ነባር በአጠቃላይ 270 የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ምርትና አገልግሎቶች ተሻሽለው ለደንበኞች ቀርበዋል፡፡ 

የምርትና አገልግሎቶቻችን ተደራሽነት መጨመር

በየጊዜው ባደረግነው ማሻሻያዎች በ2010 ዓ.ም. ደንበኞቻችን የቴሌኮም አገልግሎትን ለማግኘት ይጓዙ የነበረውን ረዥም ርቀት ወደ 4.5 ኪሎ ሜትር በማሳጠር ለዜጎቻችን ይበልጥ ተደራሽ ከመሆናችን በላይ ይብሱን ዘምነን በዲጂታል ቻናሎች ቀርበናል፤ በዌብ ቻት፣ በአርዲ ቻት ቦት፣ በኢሜይል፣ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በሁሉም ተደራሽ ሆነናል!

ምርትና አገልግሎቶቻችንን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በበጀት አመቱ 127 ተጨማሪ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመክፈት አጠቃላይ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ብዛትን 976 ማድረስ የተቻለ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 472 በፍራንቻይዝ እንዲሁም 496 በኩባንያችን ባለቤትነት ስር የተያዙ ማዕከላት ናቸው። በበጀት አመቱ የቴሌኮም ምርት እና አገልግሎትን ለደንበኖች የሚያቀርቡ 9,815 ቸርቻሪዎችን ማፍራት የተቻለ ሲሆን በዚህም አጠቃላይ የአጋሮችን ቁጥር ወደ 303,018 ማሳደግ ተችሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የደንበኞች ተሞክሮን በእጅጉ ለማሻሻልና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተሻለ ቅልጥፍና ማምጣትን ታሳቢ በማድረግ የደንበኞች አገልግሎትን እንደዌብ ቻት፣ አርዲ ቻት ቦት፣ ኢሜል እና ማህበራዊ ትስስር ገጾች ያሉ የዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ አብዛኛው ደንበኛ ራስ አገዝ የዲጂታል ቻናሎችን እንዲጠቀም ለማድረግ በርካታ ስራዎች የተሰሩ ሲሆነ በዚህም አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ተችሏል፡፡

ለደንበኞቻችን አስተያየት ትኩረት መስጠታችን

ኩባንያችን ለደንበኞቹ ቅርብ ብቻ ሳይሆን አድማጭ ጭምር ነው!

ኩባንያችን ለሚያቀርባቸው ምርት እና አገልግሎቶች አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመዳሰስና የደንበኞችን ፍላጎት በማጥናት አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለገበያ ከማቅረቡ ባሻገር ከደንበኞቻችን የተገኙ ግብአቶችን በመውሰድ  የዳታ አገልግሎት ጥራት፤ ዋጋ ክለሳ፤ እና የድህረ ሽያጭ ድጋፍ አገልግሎትና ሌሎችንም ማሻሻያዎች አድርጓል፡፡

ያልተገናኙትን በማገናኘት ላይ ፤ የገጠር ተደራሽነት  

ትጋታችን የትኛውም የማህበረሰባችን ክፍል ከኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች እንዳይጎድል ነው!

አካታችነትን መርሁ ያደረገው ኩባንያችን የሞባይል አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖረውን ማህበረሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ ፕሮጀክት ቀርፆ በ100 ጣቢያዎች የመሠረተ ልማት እና የመገናኛ ዕቃዎች በአስቸጋሪ እና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በማጓጓዝ ወደ የጣቢያዎች ማድረስ የተቻለ ሲሆን በ59 ጣቢያዎች ተከላ ተጠናቆ  አገልግሎት ማስጀመር ተችሏል። ቀሪ ጣቢያዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ210 በላይ ቀበሌዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

በበጀት ዓመቱ በትግበራ ላይ ካለው Rural Solution ባሻገር በ12 ክልሎች እና በአንድ የከተማ መስተዳድር ስር ባሉ 81 ወረዳዎች ውስጥ 91 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ባጠቃላይ 150 አዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት ላይ የዋሉ ሲሆን፤ ተጨማሪ 63 የሞባይል ጣቢያዎች በተለያዩ የግንባታ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም በ7 ክልል መስተዳደር በ132 ነባር የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የ2G/3G የማስፋፊያ ስራ የተሰራ ሲሆን በዚህም 104 ወረዳዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡  

የቴሌኮም መሰረተ ልማት እና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን መልሶ ማቋቋም 

(Restoration)

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባጋጠመው አለመረጋጋት እና የጸጥታ መደፍረስ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ከመድረሱም በተጨማሪ፤ በነበረው ክፍተት ንብረቶች ለስርቆት በመጋለጣቸው፣ መደበኛ የኔትወርክ ኦፕሬሽንና ጥገና ማድረግ እንዲሁም በአገልግሎት ማዕከላት ላይ የሽያጭና ደንበኞች አገልግሎት ስራዎችን ማከናወን ባለመቻሉ በየአካባቢዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜያት የቴሌኮም አገልግሎት ሳያገኙ ቆይተዋል።

የሰላምና ደህንነት ሁኔታዎች መሻሻል ማሳየቱን ተከትሎ፤ ክፕሮጀክትና መደበኛ ኦፕሬሽን ስራዎች በተጨማሪ ኩባንያችን በ2016 በጀት ዓመት የተቀናጀ የመልሶ ማቋቋም እቅድ በማዘጋጀት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በመጠገን እና በአዲስ በመተካት እንዲሁም የአገልግሎት ማዕከላትን መልሶ ስራ በማስጀመር ውጤታማ ስራዎችን ማከናወን ተችሏል።

በዚህም በአምስት የተለያዩ ቦታዎች 570 ኪ.ሜ የሚረዝም የባክቦን ፋይበር መስመር በመጠገን ያልተቆራረጠ የቴሌኮም አገልግሎት ለማስጀመር ትልቅ እገዛ አድርጓል። በተጨማሪም በኔትወርክ ጣቢያዎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ  ጥገናዎችን በማከናወን 179 የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማስቻል በ6 ክልሎች የሚገኙ 61 ከተሞችና ወረዳዎችን ዳግም የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን  16 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ጥገና ተከናውኖላቸው ስራ ጀምረዋል። በአራት የኦሮሚያ ክልል ከተሞች 374 አዳዲስ የፊክስድ ብሮድ ባንድ ደንበኞች ስራ የጀመሩ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 14 የፋይናንስ ተቋማት 62 የድርጅት ደንበኞች ይገኙበታል፡፡

ሚናችን አስቻይነታችን!

ከልብ በመነጨ ተነሳሽነትና ስሜት ቴክኖሎጂን ለመፍትሔነት የሚጠቀመው ኩባንያችን ከመሰረታዊ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር በሚያቀርባቸው የተለያዩ ችግር ፈቺ የዲጂታል አገልግሎቶቹ ተቋማትን ቀልጣፋና ምርታማ፣ የማህበረሰቡን ህይወት ዘመናዊ እና ቀላል፣ ሀገርን ተወዳዳሪ እንድትሆን ለማድረግ እየተጋ ይገኛል::

ለሀገራችን አካታች ሁለንተናዊ እድገት እና ተወዳዳሪነት የቴሌኮም ኢንዱስትሪው ሚና  አይተኬ ነው፡፡ ሀገራችንን ለ130 ዓመታት ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ እያገለገለ የዘለቀው የዘለቀው ኩባንያችን ባለንበት የዲጂታል ዘመን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውነታ በሀገራችን ለማረጋገጥ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡

በመንግስት የተያዘውን የዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይን እውን ከማድረግ አንጻር በተሰሩ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የዳታ ሴንተር እና የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሰረት በማድረግ በ2 ዳታ ማዕከሎቻችን 112 ITRack/896kw IT Load አቅም ያለው የማስፋፊያ ስራ የተሰራ ሲሆን፤ በዚህም የዳታ ሴንተር አቅማችንን ወደ 4.2MW IT Load /480 IT Rack ማሳደግ ተችሏል።

የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው እና ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ እንዲያደርጉ የሚያስችለው የክላውድ ኢንፍራስትራክቸር ማስፋፊያ ፕሮጀክት የተተገበረ ሲሆን  በዚህም በበጀት አመቱ፡-

በelastic compute ከ3,072 vCPU ወደ 10,752 vCPU
በbare metal server ከ12 ሰርቨር ወደ 94 ሰርቨር
እንዲሁም storage ከ1.3 PB ወደ 5.1 PB ማሳደግ ተችሏል፡፡
በአጠቃላይ ከ250% (በvCPU) እስከ 800% በstorage ማሳደግ ተችሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከመሰረታዊ የቴሌኮም አገልግሎቶች ባሻገር (Beyond Connectivity) ባቀረብናቸው የዲጂታል ሶሉሽኖች ከ667 በላይ ለሚሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤት እና ባንኮችን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የተለያዩ ሴክተሮችን ዲጂታላይዝ በማድረግ የአሰራር ስርዓታቸውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለደንበኞቻቸው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እና ምርታማ እንዲሆኑ ከማስቻላችንም በላይ እንደ ሀገር የሀብት ብክነትን ከመቀነስ እንዲሁም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ከማስቻል አንፃር ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ 

የአገልግሎት ክፍያ ስርአትን ከማዘመን አንጻር የ129 መንግስታዊ ተቋማት ምርት እና አገልግሎት ክፍያዎችን በቴሌብር በማስተሳሰር የነዳጅ ክፍያን ሳይጨምር 63.9 ቢሊዮን ብር ክፍያ በቴሌብር በኩል የተፈጸመ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 51 ቢሊዮን ብር በዚህ በጀት ዓመት የተከናወነ ክፍያ ነው፡፡ ከአጠቃላይ በቴሌብር ከተከናወነው ክፍያ ውስጥ 36.8 ቢሊዮን ብር በመንግስት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት አሰጣጥ /E-Government/ በኩል የተፈጸመ ሲሆን 30.5 ቢሊዮን ብር በበጀት አመቱ የተከናወነ ነው። በተጨማሪም 233 ቢሊዮን ብር የነዳጅ ክፍያ በቴሌብር ተፈጽሟል፡፡

ቴሌብር፤ ለአካታች የዲጂታል ፋይናንስ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ

ኩባንያችን የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽና አካታች ከማድረግ አኳያ ለማህበረሰባችን ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸው አነስተኛ የሞባይል ብድር፣ ቁጠባ እና ተያያዥ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ከዳሸን ባንክ እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር እየሰጠ ይገኛል፡፡ በዚህም ኩባንያችን አነስተኛ የሞባይል ብድር፣ ቁጠባ እና ኦቨር ድራፍት አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ በማቅረብ በበጀት አመቱ ለ2.9 ሚሊየን ደንበኞች 9.35 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንዲሁም 1.3 ሚሊየን ደንበኞች ደግሞ 9.72 ቢሊዮን ብር መቆጠብ የቻሉ ሲሆን አገልግሎቱ ከጀመረበት ከነሀሴ 2014 ዓ.ም አንስቶ 5.3 ሚሊየን ደንበኞች 12.88 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት እንዲሁም 2.1 ሚሊየን ደንበኞች ደግሞ 13.35 ቢሊዮን ብር መቆጠብ ችለዋል፡፡

የቴሌብር አገልግሎትን ለማህበረሰባችን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ከተያዙ እቅዶች ውስጥ ቴሌብርን ተጠቅመው አገልግሎት የሚሰጡ አጋሮችን ቁጥር ማሳደግ አንዱ ሲሆን በበጀት አመቱ 107 ሺህ ወኪሎችን በመመዝገብ አጠቃላይ የወኪሎችን  ቁጥር 216 ሺህ ማድረስ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ከ196 ሺህ በላይ ነጋዴዎች /Merchants/ በማሳተፍ በአጠቃላይ የቴሌብር አጋሮች ቁጥር 342.6 ሺህ የደረሰ ሲሆን እነዚህ አጋሮች ደንበኛ መመዝገብ፣ ገንዘብ ወጪ እና ገቢ ማድረግ፣ የአየር ሰዓት መሸጥ እና የቢል ክፍያዎችን መፈጸም እንዲችሉ ተደርጓል፡፡ ይህም እንደ ሀገር ለታቀደዉ የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ከፍተኛ መደላድልን ፈጥሯል፡፡ 

ቴሌብር አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት እ.ኤ.አ ግንቦት 2013 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ 325 ቢሊዮን ጥሬ ገንዘብ ወደ ኤሌክትሮኒክ ገንዘብ በወኪሎች አማካኝነት ተቀይሯል፡፡ ከዚህም ውስጥ 210.2 ቢሊዮን ብር በዚህ በጀት አመት የተቀየረ ነው፡፡ 

በተጨማሪም በበጀት አመቱ 4 ተጨማሪ ባንኮች ጋር የኢንቴግሬሽን ስራ ተጠናቆ ባጠቃላይ ከ28 ባንኮች ጋር በቀላሉ ከባንክ ወደ ቴሌብር ከቴሌብር ወደ ባንክ ዝውውር እንዲቻል የተደረገ ሲሆን በበጀት አመቱ ብቻ 240 ቢሊየን ብር ከባንክ ወደ ቴሌብር የገንዘብ ዝውውር የተደረገ ሲሆን አጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ከተጀመረበት ጀምሮ 368 ቢሊየን ብር ከባንክ ወደ ቴሌብር ተዘዋውሯል፡፡ በበጀት አመቱ ከቴሌብር ወደ ባንክ የተዘዋወረው 196 ቢሊየን ብር ሲሆን አጠቃላይ አገልግሎቱ ከጀመረበት ጀምሮ 397 ቢሊየን ብር ተዘዋውሯል፡፡ በበጀት አመቱ አጠቃላይ ከባንኮች ጋር የተደረገው የገንዘብ ዝውውር መጠን 436 ቢሊየን ብር ሲሆን ይህም አጠቃላይ የቴሌብር አገልግሎት ከጀመረበት አንስቶ ያለውን ከባንኮች ጋር የተደረገውን የገንዘብ ዝውውር መጠን 765  ቢሊዮን ብር ያደርሰዋል፡፡ 

በተጨማሪም ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር በተደረሰ ስምምነት የቴሌብር ደንበኞች ያለካርድ ከኤቲኤም ገንዘብ ወጪ ማድረግ እንዲችሉ የተደረገ ሲሆን እስከ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በአጠቃላይ 2.6 ቢሊዮን ብር ከኤቲኤም ያለካርድ ወጪ ማድረግ ተችሏል። ከዚህ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር በዚህ በጀት ዓመት ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህም አሁናዊ የዲጂታል ገንዘብ ዝዉዉር ተግባራዊ እንዲሆን አስችሏል፡፡

 አንድ ሚሊዮን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አከናውነናል!

በሌላ በኩል የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ከተቀመጡት 4 ዋና ዋና ምሶሶዎች ውስጥ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አንዱ ነው፡፡ ይህን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ በተቀናጀ እና ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማከናወን ተቋማችን በቀጣይ ሁለት ዓመት ውስጥ 32 ሚልዮን ዜጎችን ለመመዝገብ ዝርዝር የአፈፃፀም እቅድ በማውጣት፣ 1000 የባዮሜትሪክ መመዝገቢያ ማሽኖችን ግዢ በማከናወን፣ ለሰራተኞች አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት ሚያዚያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በእቅዱ መሰረት ከተገዙት 1000 የባዮሜትሪክ መመዝገቢያ ማሽኖች ውስጥ 434 በመላ ሀገሪቱ 91 ከተሞች ማለትም 291 የባዮሜትሪክ መመዝገቢያ ማሽኖች በ197 የኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ማዕከላት ውስጥ እና 143 የባዮሜትሪክ መመዝገቢያ ማሽኖችን  ተንቀሳቃሽ ቡድኖችን (mobile team) በማዋቀር በ96 ጊዚያዊ የመመዝገቢያ ማእከላት ምዝገባውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት እስከ አሁን ድረስ 1,001,886 ደንበኞች የተመዘገቡ ሲሆን ፤ይሄንን ምዝገባ  በ2017 ዓ.ም በሰፊው አጠናክሮ ለማስቀጠል አስፈላጊውን የሰው ሃይል ቅጥር እና የእቅድ ዝግጅት  ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል ፡፡

ከ300ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራና የገቢ እድሎችን ፈጥረናል፡፡

ኩባንያችን በአገልግሎቱ የአስቻይነት ሚና ከመጫወቱ ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል እና የገቢ ምንጭ በመፍጠር የበኩሉን አስተዋፅዖ እያበረከተ ሲሆን በዚህም በቋሚና በጊዜያዊ የሥራ መደቦች የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም  በመደበኛ እና በቴሌብር ምርትና አገልግሎት አከፋፋይነት፣ በአጋርነትና በመሳሰሉ ሥራዎች ከተቋማችን ጋር በመሥራት ለ300ሺ ዜጎች የሥራና የገቢ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

አስተማማኝ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ

በዲጂታል ዘመን ዋና ስጋት ሆኖ የሚገኘውን የሳይበር ስጋት በተጠናከረ መልኩ ለመከላከል እንዲቻል ኩባንያችን የሰው ሃይል አቅምን በመገንባት፣ የአሰራር ሂደቱን በማዘመን እና ከፍተኛ በጀት በመመደብ እጅግ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን እና ምህዳሩ የሚፈልጋቸውን አዳዲስ ሶሎሽኖች በመታጠቅ በበጀት አመቱ የተሞከሩበትን ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ በመመከት የኩባንያችን ሀብቶች ሊገጥማቸው ከነበሩ የዳታ መመዝበር፤ የአገልግሎት መቋረጥ እና የገቢ ብክነት መከላከል ተችሏል። 

በበጀት አመቱ የተሞከሩ የሳይበር ጥቃቶች ለመግታት ከ4ሺ በላይ አዳዲስ እና ከ1ሺ በላይ ያሉትን የመቆጣጠሪያ ቀመሮች በመተግበር ከ732 ሺ በላይ ሙከራዎችን ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት ሙሉ በሙሉ መመከት ችለናል፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነታችን ፤ የአብሮነት መገለጫችን 

ከማህበረሰባችን ለማህበረሰባችን ማካፈልን ልምዱ ያደረገው ኩባንያችን ከሚያስገኘው ገቢ ተቋማዊ ግዴታውን ከመወጣቱ ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱንም የሚወጣ ተቋም ነው፡፡ ኩባንያችን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው ተግባር የህብረተሰቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ሊያጠናክሩ በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢያዊ  ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት፣ በሰብአዊ ተግባራት እንዲሁም የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ  ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በእነዚህ ዘርፎች ውስጥ ህፃናት፣ ወጣቶች፣ አረጋዊያንና አቅመደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች እና እናቶች እንዲሁም በጦርነት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖች በዋነኝነት በድጋፍ ስራው ውስጥ ልዩ ትኩረት የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ በበጀት አመቱ በዓይነት 207.4 ሚሊዮን እንዲሁም በገንዘብ 486.8 ሚሊዮን በድምሩ 694.2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ 

በ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ለተማሪዎች የትምህርት ግብዓት በማሟላት ረገድ በኢኮኖሚ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች 900ሺ የመማሪያ ደብተር ልገሳ፣ በመላው ሀገሪቱ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ላቋቋማቸው 66 የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት ነፃ የኢንተርኔት እና ያልተቋረጠ ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን በተለያዩ የአገራችን ክልሎች በጦርነት ለተጎዱ የትምህርት ተቋሟት የአይነት ድጋፍ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም በ2016 የትምህርት ዘመን “የእናት መቀነት” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እና በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 42 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ 6000 ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ለመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በወር ለእያንዳንዳቸው 500 ብር የኪስ ገንዘብ ለ10 ወራት ድጋፍ አድርጓል፡፡ 

ኩባንያችን ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ሠራተኞቻችን በበጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ አስተዋፅኦ በማድረግ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች  በመለየት የ7.6 ሚሊዮን ብር የገንዘብ እና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ደም በመለገስና የመልካም ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት እጅግ የሚበረታታና አርአያነት ያለው ተግባር አከናውነዋል፡፡

ኩባንያችን የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ እና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲካሄድ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያለው ሲሆን በዚህም መሰረት ዘንድሮን ጨምሮ ላለፉት አምስት አመታት የኩባንያችንን ሰራተኞችና አጋሮቻችንን በማሳተፍ በ700 ጣቢያዎች ወደ 3.8 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች በመላው አገሪቱ እንዲተከሉ የተደረገ ሲሆን ከ361 ሺ በላይ ችግኞች በበጀት ዓመቱ የተተከሉ ናችው። በድህረ ተከላ ተገቢውን እንክብካቤ እና ልዩ ጥበቃ በማድረግ የችግኞቹ የጽድቀት መጠን በአማካኝ 82% ማድረስ ተችሏል፡፡

 ፅናታችን መገለጫችን!

ኩባንያችን ምንም እንኳ እንደ ሀገር እየገጠመ ባለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት ፣ በተለያዩ የሀገራችን ክፍል ባጋጠመ የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ በኔትዎርክ ሀብት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የኮፐር መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ የግብአት አቅርቦት እጥረት እንዲሁም በውድድር  ገበያና ሌሎችም ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈ ቢሆንም ለውድድርና ለእድገት የሚያበቃውን ግልጽ የሆነ ራዕይና ተልዕኮ በመቅረጽና ከመደበኛ የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር የዲጂታል ሶሉሽን ለደንበኞቹና ለማህበረሰቡ ለማቅረብ የሚያስችለው ማስፈጸሚያ የሶስት አመት ስትራቴጂ በመንደፍ የውስጥና የውጭ ባለድርሻ አካላትን የዓላማችን ተጋሪ ማድረጋችን ለስኬታችን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አሰራር ስርዓታችንን አውቶሜት በማድረግ፣ በማዘመንና ቀልጣፋ በማድረግ፣ አዳዲስ የገቢ አማራጮችን ማስፋታችን፣ የወጭ ቁጠባን አሰራርና ባህል በማዳበሩ፣ ፈጣንና ውጤትን ያማከለ በሲስተምና በጥናት የተደገፈ የዕለት ተዕለት ክትትልና ውሳኔ የመውሰድ ባህል ማዳበሩ፣ ሐብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋሉ፣ ከቢዝነስ አጋሮችና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተናቦ በትብብር በመስራቱ፣ ኩባንያችን ያካበታቸው የተለያዩ እምቅ አቅሞች (ሰፊ ልምድና ክህሎት ያለው ሠራተኛ፣ ሰፊ የኔትወርክና የሲስተም መሠረተ ልማት፣የአገልግሎት ተደራሽነት፣ ሰፊ የቢዝነስ አጋሮችና የአገልግሎት ማዕከላት፣ የአሠራር ሥርዓት፣ እንዲሁም ታማኝ ደንበኞቻችን)  በዋና ዋና የአፈጻጸም መለኪያዎች የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግብ ምክንያት ሆነውናል፡፡

ኩባንያችንያገኛቸውእውቅናእናሽልማቶች

ኩባንያችን በበጀት ዓመቱ በርካታ ስኬቶችን እና እውቅናዎችን ያገኘ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል “የኢትዮጵያ ተቋማት ስኬት ሽልማት” መርሃ-ግብር ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስጠራት ላስመዘገበው የላቀ ውጤት ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሽልማት መበርከቱ፣ በ2015 በጀት ዓመት ኩባንያችን 21.9 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ግብር በመክፈል በ1ኛ ደረጃ የፕላቲኒየም እውቅና እንዲሁም ለተከታታይ 5 አመታት ግብርን በታማኝነትና በግንባር ቀደምነት በመክፈል ልዩ ተሸላሚ መሆኑ፣ ቴሌብር በምርጥ የሞባይል ገንዘብ አቅርቦት ዘርፍ (Best Mobile Money Offering) የ2023 የፊውቸር ዲጂታል እውቅና Juniper Research በተሰኘው ተቋም የወርቅ ደረጃ አሸናፊ ሆኖ መመረጡ፣  ቴሌብር በዲጂታል ሥነምህዳሩ ላይ በነበረው የላቀ አበርክቶ የስትራይድ አዋርድ 2024 ኢኮሲስተም ሻምፒዮን ተደርጎ (Stride Award 2024 Ecosystem Champion) በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መመረጡ እንዲሁም ዋና ስራ አስፈጻሚያችን የአፍሪካ መሪዎችን በመለየት እውቅና በሚሰጠው እና መቀመጫውን በፈረንሳይ ሀገር ባደረገ ተቋም  በ#Choiseul100Africa በአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ትልቅ ሚና ከሚጫወቱ 100 ወጣት አፍሪካዊ መሪዎች መካከል በቀዳሚነት ደረጃ መመረጣቸው ይጠቀሳሉ፡፡

ኩባንያችን በበጀት አመቱ ላስመዘገበው የላቀ ውጤት አስተዋጽኦ ላደረጋችሁ ሰራተኞቻችን፣ ውድ ደንበኞቻችን፣ የስራ አጋሮቻችን፤ የምርትና አገልግሎቶቻችን አከፋፋይ ወኪሎች፣ አቅራቢዎች፣ ቬንደሮች፣ የሚዲያ አጋሮቻችን እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

                                   ሐምሌ 03 ቀን 2016 ዓ.ም

                                        ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives