ኩባንያችን ከመደበኛ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባሻገር (beyond connectivity) የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ እና የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት በርካታ ሥራዎችን የመከወኑን ጉዞ አጠናክሮ እየገፋበት የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት በመፈራረም የኮሚሽኑ ደንበኞች የታክስና ቀረጥ ክፍያዎቻቸውን እጅግ ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹ እና አስተማማኝ የሆነውን ቴሌብርን በመጠቀም በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሆነው እንዲፈጽሙ የሚያስችላቸውን አሰራር ተግባራዊ አድርጓል፡፡

የአጋርነት ስምምነቱ በዋነኛነት ኮሚሽኑ በዲጂታል የታገዘ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት የታክስና ቀረጥ ክፍያዎችን በቀላሉ ለመሰብሰብ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ደንበኞቹ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የሚያደርገውን ጥረት ብሎም እንደሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡

በዛሬ ዕለት በተደረገው ስምምነት መሰረት ደንበኞች ካሉበት ሆነው በማንኛውም ሰዓት ክፍያቸውን በቴሌብር ሱፐርአፕ ወይም በአጭር ቁጥር (*127#) መፈጸም የሚያስችላቸው በመሆኑ አገልግሎት ለማግኘት የሚያወጡትን ወጪ እና የሚያባክኑትን ጊዜ ለመቆጠብ፣ ፈጣን የሆነ የክሊራንስ አገልግሎት ለማግኘት እንዲሁም የአሰራር ስርአታቸውን ለማዘመን ያስችላቸዋል፡፡

የጉምሩክ ታክስ እና ቀረጥ ክፍያዎችን ለመፈጸም የመጀመሪያው በሆነው አሰራር አማካኝነት ኮሚሽኑ በትጋት እያከናወነ የሚገኘውን የአሰራር ስርአት ዲጂታላይዝ የማድረግ ሂደቱን በእጅጉ የሚያግዝ ከመሆኑም በተጨማሪ ገቢውን በተሻለ ቅልጥፍና ለመሰብሰብ፣ የሥራ ማስኬጂያ ውጪን (operational cost) እና ጊዜን በመቆጠብ፣ ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናቀር እንዲሁም የሚጭበረበሩ የክፍያ ሲፒኦዎችን ለማስቀረት ያስችለዋል፡፡

በተጨማሪም የጉምሩክ ታክስ እና ቀረጥ ክፍያዎች በቴሌብር እንዲፈጸሙ መደረጉ ለሃገራችን በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ በተለይም የሎጂስቲክስ አፈጻጸም ጠቋሚ (logistics performance index) እንዲሻሻል፣ ለመጋዘንና የወደብ ኪራይ የሚከፈሉ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ ፈጣን የጉምሩክ ክሊራንስ አሰራር ለማስፈን፣ ዕቃዎችን ወደተፈለገው ቦታ በአጭር ጊዜ እንዲደርስ ለማድረግ፣ የውጭ መዋለ ንዋይን (investment) ለመሳብ፣ አምራቾችን ለማበረታታት እና የመሳሰሉት ፋይዳዎች ይኖሩታል፡፡

አገልግሎቱን ለማግኘት ደንበኞች ወደ ጉምሩክ ትሬድ ፖርታል www.customs.erca.gov.et/trade/ በመግባት እና አስፈላጊ ሂደቶችን እና ዝርዝር መረጃዎችን በመሙላት ከኮሚሽን መስሪያ ቤቱ የሚሰጣቸውን የመክፈያ ቁጥር (Payment order number) በመጠቀም በቴሌብር ሱፐርአፕ ወይም በአጭር ቁጥር (*127#) የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ በመፈጸም፣ የክፍያ ደረሰኞቻቸውን ከቴሌብር ሱፐርአፕ ላይ ማግኘት ይችላሉ፡፡

ቴሌብር ሁለት አመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ 31.2 ሚሊዮን ደንበኞችን በማፍራት የማህበረሰባችንን የዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ በዲጂታል የታገዘ በማድረግ ህይወትን በማቅለል ላይ ይገኛል፡፡ ቴሌብር እስከ አሁን ከ102 ሺ በላይ ወኪሎች፣ 34 ሺህ ነጋዴዎች እንዲሁም ከ19 ባንኮች ጋር ትስስር የፈጠረ ሲሆን፣ በቅርቡ ባስጀመረው የዲጂታል ፋይናንስ የብድርና የቁጠባ አገልግሎቱ በቴሌብር መላ የብድር አገልግሎት ለ1.63 ሚሊዮን ተጠቃሚዎቹ 2.24 ቢሊዮን ብር ያበደረ ሲሆን፣ 473ሺ የቴሌብር ሳንዱቅ የቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚዎቹ 2.11 ቢሊዮን ብር እንዲቆጥቡ ማድረግ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩልም ከበርካታ የግል እና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የክፍያ ስርዓታቸውን በማቀላጠፍ ለተቋማቱም ሆነ ደንበኞቻቸው ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን የቴሌብርን የጅምላ ክፍያ ዘዴን በመጠቀም እንደ ደመወዝ ያሉ የጅምላ ክፍያዎች ማስተናገድ፣ የትራፊክ ቅጣት ክፍያዎችን፣ እንደ ብሄራዊ የነዳጅ ድጎማ ያሉ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክቶች የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር እንዲያደርጉ አስችሏል፡፡

ቴሌብር ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶቹን በማስቀጠል በየጊዜው እያደገ የመጣውን የዲጂታል ፍላጎት ለማርካትና የዲጂታል የኑሮ ዘይቤን ለማሳለጥ፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን በአንድ አካቶ ደንበኞች ከቴሌብር መተግበሪያቸው ላይ ሆነው ሌሎች የተለያዩ መተግበሪያዎችን መጠቀም ወደሚችሉበትና “በአንድ መተግበሪያ እልፍ ጉዳይ” ወደሚያከናውኑበት ቴሌብር ሱፐርአፕ ወደተሰኘ መተግበሪያ በልጽጎ በቅርቡ ለደንበኞች ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡

በቀጣይ ጊዜያትም ኩባንያችን ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርዓታቸውን በቴሌብር የሚተገብሩበትን አሰራር በማመቻቸት ደንበኞቻቸው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እና የቴሌብር ደንበኞች በአንድ ስርዓት ሁሉንም ክፍያ ባሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ለማድረግ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ዕውን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እናረጋግጣለን፡፡

ሚያዝያ 12 ቀን 2015 .

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives