ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ብሎም የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጎችን በዕውቀት ለማነጽ የሚደረገውን ሁለገብ ሀገራዊ ጥረት ለማገዝና ሀገራዊ እና ተቋማዊ ማኅበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከሚያከናውናቸው በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው እና በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በተመረጡ 66 የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊ የሆኑ ኮምፒውተሮች፣ ልዩ ልዩ የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችን እና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መደበኛ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በማሟላት ያቋቋማቸውን የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት (digital learning centers) በዛሬው እለት አስመርቋል፡፡

ይህም ኩባንያችን የቴሌኮም አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ መሰረተ ልማቶችን ከማስፋፋት፣ ዘመኑ የደረሰባቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ከማድረግ እና በየጊዜው የቴሌኮም አገልግሎቶችን የማህበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ የአገልግሎት ክፍያ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ በማድረግ ሰፊው ማህበረሰብ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ከማስቻል ባሻገር በትምህርት ዘርፉ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ስትራቴጂያዊ እቅዶችን ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

በተለይም ያለንበት ዘመን የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ መጠን የዲጂታል መማሪያ ማዕከሎቹ መገንባት የቴክኖሎጂና አዲስ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር፣ ተማሪዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂው ጋር አብረው እንዲጓዙ ለመደገፍ፣ የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ የበጎ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ተሳትፎ በትምህርትና በሥልጠና በማጎልበት እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ለሚኖሩበት ማህበረሰብ እንዲያካፍሉ እንዲሁም ሙያዊ ትንታኔ እና ችግር ፈቺ ክህሎቶችን ለማዳበር ለትምህርት ቤቶች እና ለተማሪዎቻቸው ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም ተማሪዎች ከሌላ ት/ቤቶች ጋር መረጃ በቀላሉ መለዋወጥ እንዲችሉ፣ ማህበረሰባዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን፣ የመማር ማስተማሩን ሂደት ውጤታማ እና የተሻለ ለማድረግ፣ ተመርቀው ሲወጡ ለዲጂታል አለሙ ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂውን በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙት መካካል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በዚህ መሰረት ኩባንያችን በመላ አገሪቱ ለሚገኙ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ45.48 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 1,386 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችን፣1,386 ጠረጴዛዎችና ወንበሮችን፣ የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችን በማሟላት የዲጂታል የመማሪያ ማዕከሎቹን ያቋቋሙ ሲሆን በዚህም ከ140,596 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ከእነዚህ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 18 ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ፣ ቀሪዎቹ 48 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በክልሎች የሚገኙ ሲሆን የተጠቃሚ ትምህርት ቤቶቹ የተመረጡት በአዲስ አበባ እና ክልል ትምህርት ቢሮዎች ከኢትዮ ቴሌኮም የሪጅንና የዞን ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር ነው፡፡

የትምህርቱ ዘርፍ ለሀገራችን ሁለገብ የልማት እንቅስቃሴ ያለውን ፈርጀ-ብዙ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት ኩባንያው ከዚህ ቀደም የትምህርት ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈና ጥራት ያለው ትምህርት በቀጥታ ስርጭት እንዲያገኙ ለማድረግ፣ ከፍተኛ አቅም ባላቸው የገመድ እና የሳተላይት መገናኛ አማራጮችን በማገናኘት (ስኩል ኔት)፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በነጻ እንዲሁም እስከ 86 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ በማድረግ ከ4.8 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያን በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ በ665 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ተማሪዎች 16.5 ሚሊየን ብር የሚገመት 50,000 ደርዘን የመማሪያ ደብተሮችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች የለገሰ ሲሆን በ24 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 9,000 ተማሪዎች ለትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር 23.4 ሚሊየን ብር፣ በ45 ዩኒቨርሲቲዎች ለተመረጡ 5,500 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የኪስ ገንዘብ 22 ሚሊዮን ብር መድቦ ለእያንዳንዱ ተማሪ በወር 400 ብር ድጋፍ አድርጓል።

ከዚህም ባሻገር ሴቶች የመረጃ እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመደገፍ 54.4 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ 70 ሺህ የሞባይል ቀፎዎችን ከሲም ካርድ ጋር በአገራችን 846 ወረዳዎች ለሚገኙ ሴቶች በስጦታ ማበርከቱ እንዲሁም ሴት መምህራንን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ተደግፈው በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ለመደገፍ 50 ላፕቶና 200 ዘመናዊ የስልክ ቀፎ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሴት መምህራን ሽልማት መስጠቱ ለትምህርቱ ዘርፍ ልህቀት ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ ነው፡፡

ኩባንያችን በቅርቡ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ጦርነት ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመት የደረሰባቸውን የትምህርት ተቋማት መልሶ ለማቋቋም እና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ በአጭር የጽሁፍ መልእክት (9222) እና በቴሌብር መተግበሪያ አማካኝነት ድጋፍ ሰጪዎች አቅማቸው የፈቀደውን የገንዘብ መጠን ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን ዘዴ ማመቻቸቱ ይታወሳል፡፡

ኩባንያችን እንደ አንድ ሀገራዊ ተቋም የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ እና የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲሁም በማህበረሰቡ ሁለንተናዊ የእድገት እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ሀገራዊ አለኝታነቱንና ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

ግንቦት 25 ቀን 2014

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives