ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር ያሉ የዲጂታል ሶሉሽኖች ላይ ትኩረት በማድረግ ግለሰቦችና ድርጅቶች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውንና ቢዝነሶቻቸውን የበለጠ ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተለይም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችና ሥራ ፈጠራን ለማበረታታትና ለመደገፍ  ያለመ ኢትዮቴል ኢኖቬሽን ፕሮግራም የሚል ኢኒሼቲቭ (initiative) በመቅረጽ ለሀገራችን ጀማሪ የዲጂታል እና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ቢዝነሶችና ባለሙያዎች ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም በክላውድ ላይ የተመሰረተ ዲጂታል ሶሉሽን እና በሞባይል ፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ የፈጠራ ሀሳብ አመንጪዎች በሦስት ምዕራፎች በመከፋፈል የፈጠራ ውድድሮችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በዛሬው ዕለትም በመጨረሻው ዙር የፈጠራ ውድድር የተሸጋገሩ 10 ተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን በዝርዝር አቅርበው በዳኞች ተገምግመው ደረጃ የተሰጣቸው እና የተለዩ ሦስት ምርጥ የፈጠራ ሀሳብ አሸናፊዎችን ጨምሮ ለአስር ተወዳዳሪዎች እንደቅደም ተከተላቸው የተዘጋጀላቸውን ሽልማት እና ድጋፍ ተረክበዋል፡፡ ለዚህ የፈጠራ ውድድር አመልክተው ከነበሩ 439 ተወዳዳሪዎች መካከል ብቁ ሆነው ለተገኙ 44 ተወዳዳሪዎች ጥሪ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 21 ተወዳዳሪዎች ተገኝተው ኩባንያችን ያዘጋጀውን ስልጠና ወስደዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የተሸጋገሩት 21 ተወዳዳሪዎች የፈጠራ ሃሳቦቻቸውን በዝርዝር አቅርበው በዳኞች የተገመገመ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ለ10 ምርጥ የፈጠራ ሃሳቦች በዛሬው ዕለት ኩባንያችን ቃል በገባው መሰረት ዕውቅና ድጋፎችን አበርክቶላቸዋል፡፡

ኢትዮቴል ኢኖቬሽን ፕሮግራም ማንኛውም ጀማሪ ቢዝነስ ሊገጥመው የሚችለውን ወደ ገበያ ዘልቆ የመግባት፣ ደንበኛን የመሳብና የመያዝ እንዲሁም የባለሙያና የገንዘብ እጥረት ተግዳሮቶችን በመፍታት ጅምር የቢዝነስ ሀሳቦችን ወደ ስራ እንዲገቡ ለማብቃት፣ ለማበረታታትና የተጀመሩ ቢዝነሶችን ለማሳደግ ታልሞ በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎ የተቀረጸ ፕሮግራም ነው፡፡ የፕሮግራሙ መሰረታዊ ዓላማውም የሀገር በቀል ችግር-ፈቺ ተግባራትን ለማበረታታት፣ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶች ለመሳብ፣ ለማነሳሳትና አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ለማገዝ፣ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የፈጠራ ሀሳቦችን እንዲያጎለብቱና አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶችን ወደ ገበያ እንዲያመጡ ለመደገፍ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያ፣ ለቴክኖሎጂ አጋሮች እና ለዘርፉ ተዋንያን የትብብር ከባቢያዊ ሁኔታን በመፍጠር ጥረታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን የማድረግ ጉዞውን ማጠናከር ነው፡፡

በቀጣይም ኩባንያችን መሰል ፕሮግራሞችን በመቅረጽ እና በማዘጋጀት ከዘርፉ ስነምህዳር ቁልፍ ተዋናይ አጋሮች ጋር በመተባበር ተወዳዳሪ የሆነ አገርአቀፍ አቅምን ለመገንባት፣ ፈጠራ እና ቅንጅታዊ ስራን ለማጎልበት፣ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች የተለያዩ ፋሲሊቲዎችን በማቅረብ፣ የስልጠና እና ሌሎች አቅም ማጎልበቻ ድጋፎችን በማድረግ፣ በሀገራችን የዲጂታል ስነምህዳር ዕድገት ላይ መልካም አሻራ በማሳረፍ እና የማህበረሰቡ ችግሮችን የሚቀርፉ ምርትና አገልግሎቶችን በማልማት በአህጉሪቱ የጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የስበት ማዕከል ለማድረግ በቁርጠኝነት የሚሰራ ይሆናል፡፡

 

ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ቴሌኮም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives