ኩባንያችን ከተቋቋመለት የቢዝነስ ዓላማ በተጨማሪ ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የበኩሉን መልካም አሻራ እያሳረፈ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይም የህብረተሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማጠናከር በሚችሉ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት እና ኢኮ-ቱሪዝም በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፍ፣ ደም ልገሳና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ በስፋት እና በንቃት የሚሳተፍባቸው አበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡

በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን የዚሁ ተግባር አካል የሆነ እና አንገብጋቢ ሰብዓዊ ድጋፎችን ሁሉም የሀገራችንን ዜጎች ባሳተፈ መልኩ እና በተጠናከረ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል “ዘላቂ የጋራ ማህበራዊ ሀላፊነት ለወገን ብሩህ ተስፋ! (Matching Fund for Sustainable Support!)” የተሰኘ የድጋፍ ስምምነት ከተመረጡ ስምንት የበጎ አድራጎት ተቋሟት ጋር አካሄዷል፡፡ እነዚህም የበጎ አድራጎት ተቋሟት ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ፣ ጌርጌሲኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማሕበር፣ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል፣ ኢትዮጵያ ካንሰር አሶሴሽን፣ ኸይር በጎ አድራጎት ድርጅት፣ መቄዶኒያ የአረጋዊያን መርጃ ማዕከል፣ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማሕበር እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ናቸው፡፡

ኩባንያችን በማህበራዊ እና ሰብዓዊ ሥራቸው ውጤታማ የሆኑ የበጎ አድራጎት ተቋማትን በጥናት በመለየት ከኩባንያችን የማህበራዊ የትኩረት አቅጣጫ አንፃር ውጤታማ በሆነ መንገድ ወደ ኅብረተሰቡ ለመድረስ የሚያስችሉ የተለያዩ አሰራሮችን በመንደፍ እና ከተቋማቱ ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህ የበጎ አድራጎት ተቋሟት ለዚህ የድጋፍ መርሃ ግብር የተመረጡት ለዜጎች በሚያደርጉት ውጤታማ የሰብዓዊ አስተዋፅዖ፣ በስራቸው የሚገኙ የተረጂዎች ብዛት እንዲሁም ኩባንያችን ለገቢ ማሰባሰቢያ የሰጣቸውን የአጭር ቁጥር እና የቴሌብር ተጠቅመው የተሻለ ገንዘብ ያሰባሰቡና ይህንኑ ገንዘብ ለሰብዓዊ ስራዎቻቸው በተገቢው መንገድ ማዋላቸውን በማረጋገጥ እና ከተቋሟችን ጋር ያላቸውን አመርቂ የትብብር ስራ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡

በዚሁ መሰረት ከህዳር 2016 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም ባሉት ስምንት ወራት የበጎ አስተዋፅኦ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ የሚደረግ ሲሆን፤ ወራቶቹን በበጎ አድራጎት ተቋሟቱ ስም በመሰየም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ መላው የኅብረተሰብ ክፍል   በተቋማችን ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎ መጠን ማለትም በሚገኘው አዲስ ደንበኝነት (New subscription) እና የተጋሩ ልጥፎች ብዛት (shares) እንዲሁም ተቋሙ በሰጣቸው የአጭር ቁጥር እና የቴሌብር ቁጥሮች የገቢ ማሰባሰቢያ በዘመቻ ጊዜው (campaign period) ውስጥ የሚሰበሰበው ገንዘብ ላይ ኩባንያችን የራሱን ድጋፍ (matching fund) ጨምሮበት ለታለመው ሰብዓዊ ዓላማ እንዲውል ለማስቻል የተቀረፀ መርሃ ግብር ነው፡፡

በዚህ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተሳትፎ እና የገቢ ማሰባሰቢያ ዘመቻ ወቅት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና አብሯቸው የሚሰሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚደረግ ሲሆን ከሕዳር እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም በሚካሄደው የዘመቻ ወቅት በሚያስገኙት የገቢ መጠን ታሳቢ በማድረግ ድጋፍ ለማድረግ ታቀዷል፡፡

ኩባንያችን በየጊዜው በተቋም ደረጃ የሚያደርጋቸው የሰብአዊ ድጋፎችን አድማስ በማስፋት እና ፈቃደኛ ዜጎች ለማህበረሰቡ የሚያደርጉት ድጋፍ እንዲበረታታና እንዲሻሻል፣ የለጋሾችን ተሳትፎ ለመሳብ፣ የበጎ አድራጊ ግለሰቦችም ሆኑ ማህበራት ቁጥርና ተሳትፎ እንዲጨምር ለማድረግ፣ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያገለግሉ እንደ አጭር ቁጥር፣ ቴሌብርና የማህበራዊ ትስስር ገጾች የመሳሰሉ መልቲ ቻናል ሚዲያዎቻችን በአግባቡ በመጠቀም ይህንን የድጋፍ ገንዘብ ማሰባሰቢያ (matching fund) ፕሮግራም ተግባራዊ አድርጓል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም

ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives