ኩባንያችን ከኮኔክቲቪቲ አገልግሎት ባሻገር በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ እንዲሁም የደንበኞቻችንን የቢዝነስ አሰራር ስርዓትን ለማዘመንና የዜጎችንን የዕለት ከዕለት የኑሮ ዘይቤ የሚያሻሽሉ የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እና የዲጂታል ሶሉሽኖችን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የፋይናንስ አካታችነትን እና አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን የማከወኑን ጉዞ አጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል፡፡

በዛሬው ዕለትም ኩባንያችን ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን እና የኢትጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በመተባበር የነዳጅ አቅርቦት የአሰራር ስርዓትን እና የነዳጅ ኩፖንን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሁም ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ከመንገድ ደህንነት እና ኢንሹራንስ ፈንድ አገልግሎት ጋር የተሽከርካሪ አደጋ የሶስተኛ ወገን መድን አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የሚያደርጉ ሶሉሽኖችን በይፋ አስጀምሯል፡፡

ኩባንያችን በዛሬው ዕለት የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን በተማከለ የዲጂታል ሥርዓት ለማከናወን የሚያስችል የነዳጅ አቅርቦት ትስስር አስተዳደር ሶሉሽን /Fuel Supply Chain Management System/ በማበልጸግ ተግባራዊ አድርግል፡፡ ይህም ሶሉሽን በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ዘልማዳዊ የአሰራር ሂደቶችንና በወረቀት ላይ የተመሰረቱ አሰራሮችን ለማዘመን፣ ግልጽነት ያለው የነዳጅ አቅርቦትና ግብይትን ለማስፈን፣ ትክክለኛ ዳታ በወቅቱ ለማግኘት እንዲሁም በሂደቱ ውስጥ ለሚያስፈልጉ መሳሪያዎች ግዢ የሚውል የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም የዘርፉ ተዋናዮች ማለትም የነዳጅ ጣቢያዎችና ቀጥተኛ ተጠቃሚ ደንበኞች፣ የነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች፣ የኢትዮጵያ የፔትሮሊየም አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን አጠቃላይ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል፣ የነዳጅ አቅርቦት ትዕዛዝን በዲጂታል መላ ለመስጠት/ለማቅረብ፣ ትዕዛዝ ለመቀበል እንዲሁም አስፈላጊውን ዳታ በወቅቱ ለማግኘት (real-time data access) ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኩባንያችን የማንዋል የነዳጅ ኩፖን ሽያጭ አገልግሎት አሰራርን ወደ ወረቀት-አልባ የዲጂታል ኩፖን በመቀየር አዲሰ አሰራር ያስተዋወቀ ሲሆን ይህም ዘመናዊ አሰራር የነዳጅ ኩባንያዎች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን፣ የነዳጅ ማደያዎችን የአገልግሎት አማራጭ ለማሳደግ፣ ግብይቶችን ለማሳለጥ፣ የገንዘብ ፍሰትን ለማሻሻል፣ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የተጠቃሚዎችን መጠን ለመጨመር እና ሽያጭ ለማሳደግ፣ የዲጂታል ኩፖን ዳታዎችን ለመቆጣጠር እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት ለማካሄድ የሚያስችል የዲጂታል ሶሉሽን አስተዋቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ኩባንያችን የሶስተኛ ወገን የመድን አገልግሎት በዲጂታል ስርአት አማካኝነት ለመስጠት የሚያስችል ሶሉሽን ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ከመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ ጋር በመተባበር ይፋ አድርጓል። ይህም የኢንሹራንስ አገልግሎት አሰጣጥ ተግዳሮቶችን በማስቀረት በተለይም የተማከለ መረጃ እንዲኖር ለማስቻል፣ ክፍያን በወቅቱና በዲጂታል መንገድ ለማከናወን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል፣ የተሟላ ሪፖርት በወቅቱ ለማግኘት እና ወረቀት-አልባ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በተጨማሪም ይህ የዲጂታል ሶሉሽን ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ ተገልጋዮች የሚያደርጉትን ምልልስና ውጣ ውረድ በማስቀረት ባሉበት ሆነው በቀጥታ (online) እንዲስተናገዱ ለማድረግ በኢንሹራንስ ሂደቶች ውስጥ የሚከሰቱን ተግዳሮቶች ለመቀነስ እንዲሁም የእድሳትና ባለቤትነት ለውጥ አሰራርን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
                                                    ኢትዮ ቴሌኮም
                                              ኀዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives