ኩባንያችን ከተቋቋመበት ከ1886 ዓ.ም ጀምሮ ማሕበረሰባችንን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር በማስተዋወቅ ኃላፊነቱን ሲወጣ የኖረ የሕዝብ ተቋም መሆኑ ይታወቃል፤ በአሁኑ ወቅትም የዘመናችንን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የዲጂታል ሶሉሽኖች በፍጥነት እያቀረበ የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ዕውን እያደረገና የማህበረሰባችን የዕለት ከዕለት የአኗኗር ዘይቤን እና የቢዝነስ እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ እና አዳማ በይፋ ለአገልግሎት ያበቃውን የዘመናችንን የመጨረሻ የ5ኛ ትውልድ የሞባይል አገልግሎት በምስራቅ ምስራቅ ሪጂን በጂግጂጋ ከተማ በመዘርጋት በይፋ ያስጀመረ መሆኑን በታላቅ ደስታ ይገልጻል፡፡

በዚህም መሰረት በሶማሌ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ቢሮ፣ ሆደሌይ (ቤተ-መንግስትና አየር መንገድ)፣ በሸህ አብዱሰላም ት/ቤት፣ በክልሉ ም/ቤት (ፓርላማ) አዳራሽ፣ በክልሉ ገቢዎች ቢሮ፣ በአሮጌው ታይዋን እና በኢትዮ ቴሌኮም የምስራቅ ምስራቅ ሪጂን ጽ/ቤት አካባቢዎች አገልግሎቱን ያስጀመረ ሲሆን፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ፣ በጅግጅጋ ሸህ ሐሰን ያባሬ ሪፈራል ሆስፒታል፣ በአዲሱ ታይዋን፣ ቀበሌ 06 (አህመድ ጉሬይ ት/ቤት) እና ጀላባ አካባቢዎች ደግሞ በቅርቡ አገልግሎቱን የሚያስጀምር ይሆናል፡፡

የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጊ.ባ በሰከንድ (Gbs) የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው፣ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ (Ultra-low latency) ወደ 1ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ሲሆን፣ በተጨማሪም በአንድ ካሬ ኪሎሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ዓለማችን የደረሰበት ዘመናዊ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

5ጂ አገልግሎት በተለይም ወሳኝ ተልዕኮ ላላቸው (Mission Critical) እና በተመሳሳይ ወቅት (real time) መከናወን የሚፈልጉ አገልግሎቶችን ለአብነትም የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ህክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ ያለው ሲሆን እንደ ሹፌር-አልባ ተሽከርካሪዎች (self-driving vehicles) ፣ Internet of Things የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች በተግባር እውን እንዲሆኑ የሚያስችል አስተማማኝ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ነው፡፡

የኩባንያችን 5ጂ አገልግሎት ስራ ላይ መዋል የቢዝነስ ደንበኞቻችን ምርታማነታቸውን እና የአሠራር ቅልጥፍናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ፣ በዘመናዊ መተግበሪያዎች አማካኝነት አዳዲስ ገቢዎችን እንዲያገኙ ለማስቻል፣ የቢዝነስ ትንታኔን በቀላሉ በማግኘት ከንግድ ለውጦች ጋር በፍጥነት እንዲላመዱ እገዛ ለማድረግ እንዲሁም ተለዋዋጭ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ለተልዕኮ-ወሳኝ የሆነ ፈጣን የዳታ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፣ የማሕበረሰባችንን ሕይወት በማቅለል በኩልም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡በተጨማሪም የ5ጂ የሞባይል አገልግሎት ለዘመናዊ ቤት (Smart home) ፣ ለስማርት የጤና አገልግሎት እና የሆስፒታል አስተዳደር፣ ለስማርት ግብርና፣ ትምህርት፣ ኢንደስትሪ/ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ለስማርት ኤርፖርትና የጉዞ አገልግሎት፣ ለስማርት ትራንስፖርት፣ ለብሮድካስቲንግና ለመዝናኛ እንዲሁም በክላውድ ላይ ለተመሰረቱ የ5ጂ ጌሞች ከፍተኛ ፋይዳ ያለው የዘመናችን የመጨረሻው ቴክኖሎጂ ነው፡፡ኩባንያችን ያስጀመረውን ይህን የ5ጂ አገልግሎት ለክቡራን ደንበኞቹ ያልተገደበ ዳታ፣ የመደበኛ የመኖሪያ ቤት እንዲሁም የተለያዩ የጥቅል አማራጮችን ያቀረበ ሲሆን፣ ደንበኞች የ5ጂ አገልግሎትን ለመጠቀም የሚያስችሉ መሳሪያዎችና ቀፎዎች ሊኖራቸው ይገባል፡፡                  

ኢትዮ ቴሌኮም

ህዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives