ኩባንያችን ለሃገራችን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እድገት አስቻይ የሆኑ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ እንዲሁም ለማህበረሰባችን የዕለት ከዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ስትራቴጂያዊ እቅዶችን ነድፎ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለሃገራችን ፈርቀዳጅ የሆነውን ስማርት የመማሪያ ክፍል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ በመገንባት በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡

በመሆኑም ኩባንያችን አካታች እና ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የተያዘውን እቅድ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስማርት የመማሪያ ክፍል በመገንባት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት አስረክቧል፡፡

ኩባንያችን በትምህርት ዘርፉ ግንባር ቀደም ተዋናይ ከመሆኑም ባሻገር በሃገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ለማድረግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት፣ የመማር ማስተማሩ ሂደት በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ለማድረግ እንዲሁም እየተከናወኑ የሚገኙ ሁለገብ ሀገራዊ ጥረቶች ይበልጥ ፍሬ እንዲያፈሩ የበኩሉን ከፍተኛ ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

የስማርት የመማሪያ ክፍሉ የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት በመሆኑ የመማር ማስተማሩን ሂደት በቀላሉ ለማከናወን ያስችላል፡፡ በተለይም የትምህርት ተቋማት የትምህርት ዘርፍን  የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕውን ለማድረግ፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል፣ የማስተማሪያ ወጪዎችን ለመቀነስ በተለይም ለቤተሙከራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለመግዛት የሚውሉ ወጪዎችን ለመቀነስ፣ የትምህርት መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት እና የዲጂታል ቴክኖሎጂውን በሚጠቀሙ እና በማይጠቀሙ መካካል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሆን፣ ይህ በዛሬው እለት በይፋ ሥራ የጀመረው ስማርት የመማሪያ ክፍል ሌሎች ተመሳሳይ የስማርት መማሪያ ክፍሎችን በሃገራችን በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ለመገንባት እንደናሙና የሚያገለግል ይሆናል፡፡

በተጨማሪ የስማርት የመማሪያ ክፍሉ መምህራን በቀላሉ ማስተማር እንዲችሉ፣ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶችን በቴክኖሎጂ ቤተ-ሙከራ እንዲደገፉ፣ የትምህርት አሰጣጡን ከሁኔታዎች ጋር ለማጣጣም፣ የተማሪዎቹን ሁኔታ ለመከታተል፣ የምዘና ፈተናዎችን ለማረም እና ውጤቶችን ወዲያውኑ ለማሳወቅ እንዲሁም የተማሪዎችን የትምህርት መረጃዎች በቀላሉ ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ እንዲሁም ተማሪዎች ከልማዳዊ ትምህርት አንጻር በተግባራዊ ተሞክሮ የበለጸገ እና የተሻለ የትምህርት ተሞክሮ እንዲኖራቸው፣ በየትኛወም ጊዜና ቦታ እንዲማሩ በተለይም በአካል ተገኝተው መማር የማይችሉ ተማሪዎች በቀላሉ በቨርችዋል ክላስ ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

ኩባንያችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ያለንበት ዘመን የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ መጠን ለትምህርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የትምህርት ግብዓቶችን ከማቅረብ እና የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ከማድረግ ባሻገር በትምህርት ዘርፉ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ለአብነትም ባለፈው ዓመት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች 66 የዲጂታል መማሪያ ማዕከላትን (digital learning centers) በመገንባት እና ሙሉ ግብዓቶችን በማሟላት ማስረከብ ችሏል፡፡

ኩባንያችን እንደ አንድ ሀገራዊ ተቋም የትምህርት ዘርፉን በመደገፍ እና የተሻለ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲሁም በማህበረሰቡ ሁለንተናዊ የእድገት እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ሀገራዊ አለኝታነቱንና ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣል፡፡

                                                      ኢትዮ ቴሌኮም

                                    ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም.

Share This Post:

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin

Follow Us

Recent Posts

Archives